የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ኦፓል፣ ኤመራልድና ሳፋየር ማዕድናትን ሊያገበያይ መሆኑን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከዚህ ቀደም የማዕድን ምርቶችን ወደ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለማስገባት ከማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙ ይታወሳል።
በዚህም የማዕድን ምርቶችን ለማገበያየት በሁለቱ ተቋማት በተዘጋጀው የምርት ኮንትራት ላይ ከአቅራቢዎች፤ አምራቾችና የክልሎች ተወካዮች ጋር ምክክር አካሂዷል።
መድረኩን የከፈቱት የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወንድምአገኘሁ ነገራ ፤ የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ የዝግጅት ሥራ በማከናወን የኮንትራት ዝግጅትና የግብይት ሞዳሊቲ ተዘጋጅቷል ብለዋል።
አገራችን ከማዕድን ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም በተሻለ መልኩ እንድታገኝ ለማስቻል የማዕድን ዘርፉ ያሉበትን ባህላዊና ኋላቀር የግብይት ስርዓት በማስወገድ ዘመናዊ፥ ግልፅና ተጠያቂነት የተላበሰ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከፍተኛ እምቅ አቅም ያለው ይህ ሴክተር በዘመናዊ፣ ግልፅና ተገማች የግብይት ስርዓት በመፍጠር አምራቹን ብሎም ኢትዮጵያ ከዘርፉ ተጠቃሚ የምትሆንበት ዕድል ለመፍጠር ማእድናቱ ወደ ዘመናዊ ግብይት ሥርዓቱ መቀላቀላቸው የጎላ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።
ሁሉም ባለድርሻ አካላት የነቃ ውይይትና ተሳትፎ በማድረግ የማዕድን ግብይት ኮንትራቱን በተሻለ ለማዳበር የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የማዕድን ዘርፍ በርካታ ዕድሎችና አቅሞች ያሉት በመሆኑ የግብይት ስርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግ መታሰቡ ተገቢ መሆኑን በማወደስ ነገርግን በዘርፉ ከጥራት አወሳሰንና አመዳደብ ጋር የሚታዩ ነገሮችን ከወዲሁ ማጤን እንደሚገባ ገልጸዋል ሲል ኢ.ፕ.ድ ዘግቧል።
የአቅራቢውንና አምራቹን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አሁንም ተገቢውን ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና የግብይት ስርዓቱ የበለጠ በተሳካ ሁኔታ ለመተግበር እታች ካሉ አምራቾች ጋር ሰፊና በቂ ምክክር ሊደረግ እንደሚገባም መጠቆማቸውን ምርት ገበያው ማስታወቁም በዘገባው ተመላክቷል።






