በሩሲያ በሙስና ወንጀል ደልበዋል ተብለው በተጠረጠሩ የትራፊክ ፖሊሶች ቤት ሲፈተሽ የወርቅ ሸንት ቤትና ሌሎች በቅንጦት የተሞሉ ቁሳቁሶች መገኘታቸውን የሀገሪቱ መርማሪዎች አስታወቁ።
መርማሪዎቹ ቅንጡ የሆነው ቤት ላይ ባደረጉት ድንገተኛ ፍተሻ በሙስና ወንጀል ደልበዋል ተብለው የተጠረጠሩ የትራፊክ ፖሊሶች ቡድን መያዛቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ቅንጡ የሆነው ቤት በጣም ትልቅ፣ ማዕድ ቤቱም በወርቅ የተንቆጠቆጠና ለየት ባሉ ቁሶች የተሞላ መሆኑን ቢቢሲ መርማሪዎቹን ዋቢ አድርገው የፃፈው ዘገባ ያስረዳል።
በሩሲያ የደቡብ ስታቭሮፖል ግዛት የትራፊክ ፖሊስ ኃላፊ ኮሎኔል አሌክሴ ሳፎኖቭን ጨምሮ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ስድስት የትራፊክ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር መዋለቸውም ተገልጿል።
የተለያዩ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ከሆነ የትራፊክ ፖሊሶቹ የንግድ እቃዎችን ለሚያመላልሱ አሽከርካሪዎች ሃሰተኛ ፈቃድ እየሰጡ በምላሹም ጉቦ ተቀብለዋል ተብሏል።
አሽከርካሪዎቹ የትራፊክ ፖሊሶቹ የሚሰጧቸውን ፈቃድ ተጠቅመው ያልተፈቀዱ የእህል ጭነቶች እና የግንባታ ቁሳቁሶችን ይዘው በፖሊስ ኬላዎች እንዲያልፉ መደረጉም በዘገባው ተገልጿል።



