የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በ2014 በጀት ዓመት የሀብት ምዝገባ መረጃ ትክክለኛነት የማረጋገጥ ተግባርን በሶስት እጥፍ ለማሳደግና 150 ሺህ የሀብት ምዝገባ መረጃዎችን ወደ ዘመናዊ የመረጃ ቋት ለማስገባት ማቀዱን በኮሚሽኑ የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ዳይሬክተር አቶ መስፍን በላይነህ ገለፁ፡፡
በ2014 በጀት ዓመት የ300 ሀብት አስመዝጋቢዎችን መረጃ ትክክለኛነት የማረጋገጥ ተግባራትን በሦስት እጥፍ አሳድጎ ለማከናወን ዕቅድ መያዙን አቶ መስፍን ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል፡፡
የተመዘገበን ሀብት መረጃ ትክክለኛነትን በማጣራት ሀብት አስመዝጋቢዎች ከህጋዊ ገቢያቸው ብቻ ተጠቃሚ መሆናቸውን የመለየትና ያልተገባ የገንዘብ ልውውጥ መኖሩን ከማረጋገጥ አኳያ በ2013 በጀት ዓመት የ100 ሀብት አስመዝጋቢዎችን መረጃ (ከነቤተሰቦቻቸው 386 ሰዎች) ትክክለኛነት በማረጋገጥ 10 ሀብት አስመዝጋቢዎች በሕግ እንዲጠየቁ መደረጉ ይታወቃል፡፡
የተመዘገበን ሀብት ትክክለኛነት የማረጋገጥ ሥራ በአዋጅ ቁጥር 668/2002 አንቀፅ 11 መሠረት በተሿሚ፣ በተመራጭ ወይም በመንግሥት ሠራተኛ በተሞላ መረጃ ያልተሟላ፣ ትክክል ያልሆነ ወይም የሀሰት መረጃ የያዘ መሆኑን ለመጠርጠር ኮሚሽኑ በቂ ምክንያት ሲኖረው ወይም ሀብቱ በትክክል አልተመዘገበም የሚል ጥቆማ ሲቀርብ ወይም በተፈጸመ ወንጀል ምክንያት ምርመራ ሲጀመር የምዝገባውን ትክክለኛነት በማጣራት በተገኘው ውጤት ላይ እርምጃ የማስወሰድ ተግባር እንሚያከናውን ይታወቃል፡፡
በሌላ በኩል በአዲሱ በጀት ዓመት 150 ሺህ የተመዘገበ የሀብት ምዝገባ መረጃዎችን ወደ ዘመናዊ መረጃ ስርዓት በማስገባት ለተደራሽነት ዝግጁ የማድረግ ሥራን ለማከናወን መታቀዱን የገለፁት ዳይሬክተሩ ሌሎች የሀብት ምዝገባና እድሳት እንዲሁም መረጃዎችን ተደራሽ የማድረግ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ማሳወቃቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡



