ከ5 ሚሊየን በላይ ወጣቶች ይሳተፉበታል ተብሎ የተገመተው የሀምሌ 16ቱ ህዝባዊ ሰልፍ ተራዘመ

0
681

የህዳሴ ግድብ ሙሌትን ለመደገፍና የውጪ ጫናን ለመቃወም በሚል ከ5 ሚሊየን በላይ ወጣቶች ይሳተፉበታል ተብሎ የተገመተውና ለሀምሌ 16 ታቅዶ የነበረው ህዝባዊ ሰልፍ ወደ ሀምሌ 25 መራዘሙ ተገለጸ።

የዩዝ ኔትወርክ ሰስቴኔብል ዴቨሎፕመንት ዋና ዳይሬክተር ኢሳያስ አለማየሁ አዘጋጆቹ ይህንን ውሳኔ ያሳለፉት ከመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ምክክር በመግባባታቸው እንደሆነ ገልፀዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ5 ሚሊየን በላይ ወጣቶች ይሳተፉበታል ተብሎ የተገመተው ትዕይንተ ህዝብ ሀምሌ 16 አመሻሽ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፤ በተለያዩ ምክንያቶች ሰልፉ እንዲራዘም መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም ሀምሌ 15 በአዲስ አበባ ለሀገር መከላከያ ሰራዊትና ለህዳሴ ግድብ የድጋፍ ሰልፍ መካሄዱን አስታውሰው፣ ፕሮግራሞች በቀዳሚው ሰልፍ በመዋጥ መተላለፍ የሚገባው መልዕክት ሳይተላለፍ እንዳይቀር በሚል ሰልፉ እንደተራዘመም በምክንያታዊነት ጠቁመዋል፡፡

ወጣቱን በተከታታይ ቀን ስራ አስትቶ ለሰልፍ ማስወጣቱ መሰላቸት እንዳይፈጥርና እንዲሁም የፀጥታ አካላት የሚኖረውን የስራ መደራረብ ለመቀነስ ሲባል ማራዘሙ አስፈላጊ መሆኑንም አክለዋል።

በመሆኑም ለህዳሴ ግድብ የሚደረገው የድጋፍ ሰልፍ በመጪው ሀምሌ 25 ከጠዋቱ 2:30 እስከ 5:00 ሰዓት እንዲካሄድ ተወስኗል ሲሉ ዳይሬክተሩ ለዋልታ ተናግረዋል።

ሰላማዊ ሰልፉ በዩዝ ኔትወርክ ሰስቴኔብል ዴቬሎፕመንት፣ በሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኤጀንሲ፣ በሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር እንዲሁም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት የሚዘጋጅ መሆኑንም ዘገባው አመላክቷል።

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here