የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ‹ኮርነር ስቶን ሀውሲንግ ደቨሎፕመንት ግሩፕ› ከተሰኘ ድርጅት ጋር በሐዋሳ ኢንዱስተሪያል ፓርክ ለ ስድስት ሺሕ 500 የፋብሪካ ሠራተኞች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ለመፈጸም የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈራረመ።
በሐዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በፋብሪካ ውስጥ ለሚሠሩ ሠራተኞች ያለባቸውን የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ የሚያስችል የመኖሪያ ቤቶች ግንባትን ለማካሄድ ኮርፖሬሽኑ የውል ስምምነትን ፈጽሟል።
የመኖሪያ ቤት ግንባታውን ለማካሄድ የሚያስችለውን የውል ስምምነት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሳንዶካን ደበበ እና የኮርነር ስቶን ሀውሲንግ ደቨሎፕመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲራክ አምባዬ ተፈራርመዋል።
ለሐዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ለስድስት ሺህ 500 የፋብሪካ ሰራተኞች የመኖሪያ ቤት ለማቅረብ ኮርነር ስቶን ሀውሲንግ ደቨሎፕመንት ግሩፕ ከተባለ ኩባንያ ጋር የውል ስምምነት የተካሄደ ሲሆን ፕሮጀክቱም በ 2.08 ሄክታር ላይ የሚያርፍ ይሆናል ተብሏል።
የመኖሪያ ቤት ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት ላይ ሲውል በውስጡም ከሠራተኞች መኖሪያነት ባሻገር የሠራተኞች መመገቢያ አዳራሾች፣ ሱቆች፣መዝናኛ ቦታዎች፣ባንክ፣ የሠራተኞች ሥልጠና መስጫዎች፣ አረንጓዴ ስፍራ፣ክሊኒክ እና ቢሮዎችን ያካተተ እንደሆነ ተገልጿል።
በሐዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የሚገነባው ይህ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 13 ሕንጻዎችን ያካተተ ሲሆን የሕንፃዎቹ ዲዛይንም የዓለም ዐቀፍ የሠራተኞችን የመኖሪያ ደረጃ ያሟላ እንደሆነ ታውቋል።
የሕንጻዎቹን ግንባታ ለማጠናቀቅ 18 ወራት ይፈጃል የተባለ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባ በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያለውን የቤት አቅርቦት ችግር ያቃልላል ተብሎ ይጠበቃል።
ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013


