በሱማሌ ክልል ለሕወሐት ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ 28 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

0
527

የሱማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ለሕወሓት ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ 28 ግለሰቦችና ንብረቶቻቸው በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ::
በክልሉ የሚገኙ የሕወሓት ተላላኪዎች ለቡድኑ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን የገለጹት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ረ/ኮሚሽነር መሐመድ አሊ ሐሰን፣ 28 ግለሰቦች 10 የሲኖትራክ መኪና እና ሌሎች ንብረቶቻቸው በሕብረተሰቡ ጥቆማና በፖሊስ በተደረገ ከፍተኛ ክትትል መያዛቸውን ገልጸዋል።
ግለሰቦቹ በክልሉ ብጥብጥ ለማስነሳት አቅደው ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውንም ነው ረዳት ኮሚሽነሩ የገለጹት።
ለዚህ ተግባር እንዲያብሩ ከዚህ ቀደም የነበረው አመራር አባላትና ደጋፊዎች የሆኑ የክልሉ ተወላጆችን በማስተባበር ሲሰሩ ቆይተዋልም ብለዋል ረዳት ኮሚሽነሩ።
በተለይ የሱማሌ ክልል ልዩ ኃይል ፖሊስ ለአገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ወደ ግዳጅ ማምራቱን ተከትሎ በክልሉ የሚገኙ የጁንታው ተላላኪዎች ይህንን አገራዊ ኃላፊነት ሌላ ቅጥያ ስም በመስጠትና በማኅበራዊ ሚዲያ ለፕሮፖጋንዳነት በመጠቀም ሂደቱን ለማስተጓጎል ሲጥሩ ነበርም ብለዋል።
የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ የአገሪቷን ሉዓላዊነት እና ሕገ-መንግሥት ለመጠበቅ የገባውን ቃለ መሀላ ለመተግበር ዛሬም ሆነ ነገ ዝግጁ ነው ያሉት ረ/ኮሚሽነሩ፣ ጁንታው ስርዓተ ቀብሩ እስኪፈፀም ድረስም ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በመሆኑም በእንደዚህ አይነት ተግባር ውስጥ እጃቸውን በማስገባት ለጁንታው ድጋፍ እያደረጉ የሚገኙ ግለሰቦችና በማኅበራዊ ሚዲያ የተለያዩ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨትና ንብረቶቻቸውን በመሸሸግ እየተባበሩ የሚገኙ የክልሉ ተወላጆች ከዚህ ተግባራቸው እንዲቆጠቡ ሲሉ ረ/ኮሚሽነሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።


ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here