ሕጻናትን ለጦርነት መጠቀሚያ ከማድረግ እንቆጠብ!

0
802

በየትኛውም ወገን ቢሆን ሕጻናትን ወደ ጦር ሜዳ መውሰድ የተወገዘ ሊሆን ይገባል። ውጊያ ውስጥ መማገድ ብቻ ሳይሆን ለሥነ-ልቦና ጦርነት በሚል ምስላቸውን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እያዘዋወሩ ለወደፊት ሰላማዊ ኑሮን መግፋት እንዳይችሉ ማድረግ ከአንድ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ አይደለም።

“ምርጥ ምርጡን ለሕጻናት” ብለው ያሳደጉ የቀድሞ ትውልድ ልጆች የሆንንና ቡድንንም ሆነ ሕዝብን የምናስተዳድር፣ ለሕጻናት ብለን እንጂ በሕጻናት ጉልበት መኖር እንደሌለብን ልንገነዘብ ግድ ይላል። ጉልበታቸውን አላግባብ አትበዝብዙ በሚባልበት ዘመን፣ ሕይወታቸውን አሳልፈን መጠቀሚያ ለማድረግ የሚያስችል ምንም አይነት የሞራል ልዕልና አይኖረንም። ሕጻናት ጊዜያቸው ሲደርስ አገር እንዲረከቡ የሚያስችላቸውን ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ እንጂ፣ ሊወልዷቸው ከሚችሉ ከሠለጠኑ ታላላቆቻቸው ጋር ለጦርነት በማጋፈጥ እንዲረግፉ ማድረጉ ትውልድን ከማሳጣት በላይ የማይሽር ቂም እንደሚፈጥር አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በጦርነት ወቅት የተዋጊ እጥረት እንደሚኖር ግልጽ ቢሆንም፣ ለውጊያ ጥንካሬ ሲባል ወዶ ዘማቾች ቢሆኑ በቅድሚያ ይመረጣል። ይህ ባይሆንና በምልመላ መልክ በግድ ቢደረግ እንኳን፣ አዋቂ ምስጢር ጠባቂና የበሰሉ ተዋጊዎችን መርጦ ማሰለፉ እንደሚጠቅም አይካድም። የጦር አዋቂዎች እንደሚያስተምሩት “ለምን?” ብሎ ሳይጠይቅ በታዘዘው መንገድ ሊዋጋ የሚችለው እድሜው ከ22 ባይበልጥ ይመረጣል። ይህ ቢሆንም ተቀባይነት የሌላቸው አማጽያን፣ በተለይ አፍሪካ ጫካ ውስጥ በመሸመቅ የሚታወቁ ቡድኖች፣ እንቦቀቅላ ሕጻናትን እያካተቱ ያደረሱትን ግፍ ዓለም ያውቀዋል። ሕጻናቱን በአደንዛዥ ዕፅ አስገድደው ለማሰብም የሚዘገንን ግፍ ቢያሠሯቸውም፣ ነፍሳቸውን እያወቁ ሲሄዱ ይጠፉባቸዋል። አማራጭ ካጡም ዕርቀው ስለማያመዛዝኑ አዛዦቻቸውን ጨምሮ ጓዶቻቸው ላይ አፈሙዝ አዙረው የሚጨርሱበትም አጋጣሚ አለ።

ሕጻናትን መመልመል ወይም አማራጭ አጥተው ሲመጡ እንዲዋጉ ፈቅዶ ማስታጠቁ በየትኛውም ሕግ ከማስጠየቁ ባሻገር፣ በየትኛውም ኃይማኖት የሚፈቀድ አይደለም። ኋላ ቀር የምንላቸው የድሮ ዘመን ጦረኞች እንኳን ሕጻናትን ሊያዋጉ ቀርቶ፣ ከጠላቶቻቸው ወገን የሚያገለግሉትን እንኳን አይነኩም ነበር ይባላል። ልጅ ከጦር ሜዳ እንዲርቅ ግፍን በልጅነቱ እንዳያይ ያደርጋሉ እንጂ አያቀርቡም ነበር።

በዚህ ዘመን ያለው ጦርነት እንደድሮው ጎራዴ መወርወርና በጋሻ መመከትን የመሳሰለ ጉልበትን አይጠይቅም። ቃታ ለመሳብ ቀላል ነው በሚል ክፉ ደጉን ሳያውቁ ሕጻናጽ ነፍስ እንዲያጠፉ ማድረጉ በሰማይ ቤት እንደሚያስጠይቅ የኹሉም ኃይማኖት መምህራን ይስማሙበታል። ሕጻናት መጫወት፣ መማርና መዝናናት እንጂ ለአዋቂዎች ብለው መሞት እንደሌለባቸው ለማንም ግልጽ መሆን እንዳለበት አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።

ዓለም ዐቀፉ ማሕበረሰብ በየትኛውም ወገን ፕሮፓጋንዳ ሳይመራ ዓለም ዐቀፍ መርህ የሆነውን የሕጻናት መብት ጉዳይን ሊከታተል ይገባዋል። ለፖለቲካዊ ድል ሲባል ሕዝብ እንዲያውቅ ሲባል የሕጻናቱን ምስል በተለያዩ ሚዲያዎች እያዘዋወሩ ነጥብ ማስቆጠሪያ ማድረጉም ሊቆም ይገባል። አስከሬንን ማሳየት የማይፈቀድበትን ምክንያት በማጤን የተዋጊዎችን ቦታና ማንነት እንደማናስተዋውቀው ሁሉ ስለሕጻናቱም አስቀድመን ልናስብ ይገባናል።

የጦር ቀጠና ነው በሚል ሥርዓት አልበኝነት እንዲነግስ የሚያደርጉ አካላት ችግሩ እነሱ ጋር ደርሶ ሊመልሱት የማይችሉት መከራ ውስጥ ከመግባታቸውና ሕዝብንም ለስቃይ ከመዳረጋቸው በፊት ቢያንስ ቢያማክሩና ቢወያዩበት መልካም ይሆናል። ሕጻናት ጠመንጃ ጨብጠው ፍላጎታቸውን ማሳካት የጀመሩ ዕለት ለበላዮቻቸውም እንደማይመለሱ፣ ወላጆቻቸውንም እንደማይሰሙ ሊታወቅ ይገባል። ስሜታቸውን በማይቆጣጠሩበት በዚህ ዕድሜያቸው እንዲህ አይነት ሞገደኝነትን ከተማሩ የራሴ በሚሉት ላይም የፈለጉትን ከማድረግ የሚመልሳቸው አይኖርም።

እንደ ዓለም ዐቀፍ ጥናቶች በዓለም ላይ ካሉ ታጣቂ ቡድኖች 40 በመቶዎቹ ሕጻናት ወታደሮችን በጦራቸው ውስጥ ያካትታሉ። አብዛኞቹ በችግር ሳቢያ የሚቀላቀሉ ሲሆኑ፣ ለደህንነታቸው በመስጋትም አንዱን ጎራ እንደሚቀላቀሉ ይነገራል። ቤተሰብ እያስገደደ ወይም እየተገደደ ለተዋጊዎች የሚሰጣቸውም ልጆች አሉ። መቼ እንደጀመረ ባይታወቅም፣ አንዳንድ አካባቢ ሕጻናትን ሲመለምሉ ተመልሰው እንዳይሄዱባቸው የቤተሰባቸውን አባል ወይም ጎረቤትን እንዲገድሉ እንደሚያስገድዷቸውም ይነገራል።

አብዛኞቹ ሕጻናትን፣ ተዋጊዎች በግንባር ፊትለፊት እንዲሰለፉ በማድረግ የመጀመሪያ ጥቃት ቀማሾች እንዲሆኑ ይደረጋል። ኬላና ምሽግ እንዲጠብቁ በማድረግም እንደ አብሪ በሕይወታቸው ላይ ይወስኑባቸዋል። ከኹሉም የሚያሳዝኑት ሴት ሕጻናት ሲሆኑ፣ የአዛዦቹ ወሲባዊ ጥማት ማርኪያ ይሆናሉ። እነዚህ ሕጻናት ከውጊያ ቢርቁም ቤተሰብ ጋር መመለስም ሆነ ራሳቸውን ችለው መኖር ስለሚያዳግታቸው መልሰው ወደ ውጊያ ለመግባት ይገደዳሉ። በወታደርነት የሚመለምሉ የጦር መሪዎች ምንም ነገር እንዲደረግላቸው ስለማይጠይቁ ሕጻናቱን ይመርጧቸዋል።

እንደተባበሩት መንግሥታት ጥናት፣ ዕድሜያቸው ከ7 እስከ 18 የሚሆናቸው ተዋጊዎች ቁጥር 300 ሺሕ ይደርሳል። ወጥ ቤት፣ ቦንብ አምካኝና አፈንጅ፣ ተላላኪና ሰላይ በማድረግ ልጅነታቸው የሚበዘበዝባቸው ሕጻናት ወደ ሕብረተሰቡ እንዲመለሱ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት የጀመሩት እንቅስቃሴ ጥሩ ቢሆንም አሁንም ቢያንስ በ14 አገራት በይፋ በጦረነት እየተዋጉ መሆኑ ይታወቃል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከ5 ወራት በፊት ባወጣው ሪፖርት የኮሮና ቫይረስ ባስከተለው የኢኮኖሚ መዋዠቅ ሳቢያ በርካታ ሕጻናት በተዋጊነት ሊመለመሉ ይችላሉ ሲል ስጋቱን አስቀምጦ ነበር። ለበርካታ አመታት ከአውደ ውጊያ የወጡ ሕጻናት እንዲያገግሙ ሲጥር የቆው ይህ ተቋም፣ ነገሩ እየተባባሰ ከሄደ ለማቆም አስቸጋሪ እንደሚሆን ደጋግሞ ሲያሳውቅ ቆይቷል።

ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በቀዳሚነት፣ ሱዳንና ሱማሊያም በዚህ ተግባራቸው ዓለም የሚያውቃቸው ቢሆንም፣ ሂደቱ ድንበር እየተሻገረ ኢትዮጵያም በዚህ ተግባር እየተጠቀሰች መጥታለች። ሶሪያና የመንም ብዙ ሕጻናት ውጊያ ውስጥ እንደሆኑ ይታወቃል። እንደተቋሙ ጥናት ከሆነ በፈረንጆቹ 2019 ብቻ አዳዲስ 7 ሺሕ 740 ሕጻናት ወታደር እንዲሆኑ ተፈርዶባቸዋል።

ሕጻናትን መንከባከብና ከጦርነት ማራቅ የሁሉም ግዴታ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች። እንኳን ጦርነት ውስጥ የተማገደ ሕጻን ይቅርና፣ ሩቅ ያለም ስለጦርነት ሲሰማ ምን እንደሚያስብ ግልጽ ነው። “ልጅ ያቦካው ለእራት አይበቃም” በሚባልባት አገር፣ ትልልቁ ከኋላ ተደብቆ ሕጻናትን ማጋፈጡ ተገቢ ስለማይሆን በየትኛውም በኩል ሕጻናትን በአውደ ውጊያ ከማሳተፍ መቆጠብ ያስፈልጋል። በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ጥፋተኛው ተለይቶ እስኪቀጣ ኹሉም ወገን ድርጊቱን በማውገዝ ለሚታዘዛቸው መልዕክት ማስተላለፍ ይጠበቅበታል።

ውጊያ ባይልኳቸውም መሳሪያ አንግተው ሕዝብ እንዲያያቸውና ሌሎችም ፈለጋቸውን እንዲከተል ጫና ማሳደሩም ተገቢ አይደለም። ከታዋቂ ሰው ጋር የተነሱ ይመስል ነፍስ ማጥፊያ የጦር መሳሪያን አስነግቶ ፎቶ ማስነሳትና በልጅነት ሥነ-ልቦናቸው ስለመግደል ማስተማር ለማንም አይጠቅምም። ወላጆች ልጆቻቸው ወደእንዲህ አይነት አመለካከት እንዳያዘነብሉ ቀድመው ማስተማር ይጠበቅባቸዋል። ይህ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተወገዘ ድርጊት፣ በኹሉም የሕብረተሰብ ክፍል፣ በተለይ በኃይማኖት መሪዎች ሊወገዝ ይገባል። “ከልጅ ልጅ ቢለዩ አመትም አይቆዩ” እንደሚባለው የራስን ልጅ በእንክብካቤ እያሳደጉ የሌላውን ሕጻን ልጅ ለመማገድ የሚቀሰቅሱትም በተመሳሳይ ሊኮነኑ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here