በፓስተር ዮናታን አክሊሉ ተገዝቷል የተባለውና ገርጂ ኮርያ ሆስፒታል አካባቢ የሚገኘው እንቡጥ ትምርት ቤት በአካባቢው የሚገኙ የግለሰብ እና ቀበሌ ቤቶችን ለማስፋፊያ ይሆን ዘንድ ሊወሰድ መሆኑ ቅሬታን አስነሳ።
ፓስተር ዮናታን ትምህርት ቤቱ ካረፈበት ይዞታ አልፎ፣ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችን ያለነዋሪዎቹ ፈቃድ ልውሰድ ማለታቸው ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ አቅርበዋል።
ዮናታን ገዝተውታል የተባለው ይህ ትምህርት ቤት በ60 ሚሊዮን ብር የተሸጠ ሲሆን፣ ከዓመት በፊት ተዘግቶ በአሁኑ ሰዓት በኃይማኖት ተቋምነት እያገለገለ ይገኛል።
የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ሚያዝያ 5/2013 የማስፋፊያ ቦታውን ያለባለቤቶቹ ፈቃድ እንዲሰጥ መወሰኑን አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለገዢው አናስረክብም ያሉት በአዲስ አበባ ከተማ በቦሌ ክፍለ ከተማ በወረዳ 13 ክልል አለምነህ ጋራዥ አካባቢ በአጠቃላይ 2900 ካ.ሜ. የሚሸፍን ቦታ ሲሆን፣ ባለቤቶቹ በቦታው ላይ ለረጅም ዓመታት የኖሩ ናቸው።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ስለውሳኔው ባላወቁበት ሁኔታ የክፍለ ከተማው የመሬት ልማት ጽሕፈት ቤት እና የወረዳው ባለሥልጣናት ሰኔ 30/2013 ይዞታቸው ለኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስትያን ሕብረት አዲስ ኪዳን ካሕናት ዓለም ዐቀፍ ቤተክርሥቲያን በመሰጠቱ ቦታውን አስረክበው እንዲለቁ መነገራቸውን አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።
ከቦታው እንዲለቁ ከተነገራቸው መካከል ከ6 በላይ የግለሰብ ቤቶች፣ የመረዳጃ ዕድር፣ ለይዞታው የባለሀብትነት ማረጋገጫ ሰነድ ካርታ ያለው ትልቅ ጋራዥ እና በርካታ የቀበሌ ቤቶች ይገኙበታል።
የግለሰብ ቤቶቹ የቅርብ ጊዜ የአየር ላይ ካርታ ያላቸው ሲሆን፣ የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ማስፋፊያውን የፈቀደው ቀድሞ 80ዎቹ ላይ በነበረው የአየር ላይ ካርታ ነው።
ይህንን መሰረት በማድረግ እና ሌሎች ጥያቄዎችን ይዘው ነዋሪዎቹ ባሳለፍነው ሳምንት ከከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር ቀርበው አቤቱታቸውን አሰምተው ነበር።
በአዋጅ 1161/2012 መሬት ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ ሊለቀቅ የሚችለው የልማት ሥራው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማጎልበት በጸደቀ በመሬት አጠቃቀም እና ልማት ዕቅድ፣ በመሰረተ ልማት መሪ ፕላን መሰረት (Structural Plan) ለሕዝብ የተሻለ የጋራ ጥቅም እና እድገት ያመጣል ተብሎ የተወሰነ ከሆነ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
ለከተማ አስተዳደሩ ካቀረቡ ቅሬታዎች መካከል፣ “ሕጉ የሚለው የልማት ተነሺዎች አካባቢውን የማልማት አቅም ከሌላቸው ለሌላ ማስተላለፍ እንዳለባቸው ነው” የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ አካባቢውን ባላቸው አቅም እና ከተማዋ በሚያስፈልጋት የልማት ደረጃ ለማልማት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
በተጨማሪም በደንብ ቁጥር 472/2012 አንቀጽ 3 እና 8 እንደሚለው የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ልማት እና ማኔጅመንት ቢሮ የውሳኔ ሐሳቡን ከማቅረቡ በፊት በይዞታው ላይ መብት ያላቸው አካላት እንዲወያዩ ማድረግ ግዴታ መሆኑ እየታወቀ አለማወያየቱ ተገቢ እንዳልነበር ነው ያነሱት።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ አያይዘውም አዋጅ ቁጥር 1161/2011 እና ደንብ ቁጥር 472/2012 የልማት ተነሽ ከይዞታው ላይ ከመነሳቱ በፊት ሊፈጸሙ ስለሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች እና ስለካሳ አከፋፈል፣ እንዲሁም ምትክ ቦታ አሰጣጥ በቀድሞ ሕግ ውስጥ ያልነበሩ አዳዲስ ሐሳቦችን በማካተት የተነሺዎችን መብት ለማስከበር የሚቻልበትን ሥርዓት የዘረጉ ሕጎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ነገር ግን አዋጅ ቁጥር 1161/2011 በግልጽ አዋጅ ቁጥር 455/1997ን ሽሮታል። እንዲሁም ደንብ ቁጥር 472/2012 በግልጽ ደንብ ቁጥር 135/1999ን ሽሮታል።
በመሆኑም የክፍለ ከተማው አስተዳደር አዲስ ለወጡት አዋጅ ቁጥር 1161/2011 እና ደንብ ቁጥር 472/2012 መመርያ እንዲወጣ በማድረግ ሊያስፈጽም ሲገባው በተሻረ መመርያ እያስተናገደን መሆኑ ፍትሐዊ አይደለም ብለዋል።
የቅሬታ አቅራቢዎቹ ዋነኛ ጥያቄም ለካቢኔ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ አሁን በተግባር በይዞታው ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ፣ ይልቁንም ካቢኔው ፍትሐዊ ያልሆነ ውሳኔ እንዲሰጥ ባደረገው መልኩ በተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሰረተ ነው የሚል መሆኑን አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች።
በቀን 15/2013 ቅሬታ አቅራቢዎቹ የመሬት ልማት ማኔጅመንት በመሄድ በምን መስፈረት ማስፋፊያውን እንደፈቀደ መጠየቃቸውም ታውቋል።
አዲስ ማለዳ ትምህርት ቤቱን ለገዙት ፓስተር ዮናታን አክሊሉ እንዲሁም ባለቤታቸውን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ስልክ ብትደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻለችም።
ቅጽ 3 ቁጥር 142 ሐምሌ 17 2013



