ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር ያደረገችው ወታደራዊ ትብብር በማንም ላይ ስጋት የሚፈጥር አለመሆኑን በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ አስታወቀ።
ኤምባሲው ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር እያደረገችው ያለው የወታደራዊ ቴክኒክ ትብብር ከሕዳሴ ግድብ ጋር እንደሚያያዝ ተደርጎ የሚሰራጩ ዘጋባዎችን በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ ላይ አስተባብሏል።
የሁለቱ ሀገሮች ወታደራዊ ትብብር በማንም ላይ ስጋት የሚፈጥር እንዳልሆነ የገለፀው መግለጫው ሩሲያ ከሱዳን እና ግብጽ ጋር ጭምር ተመሳሳይ ወታደራዊ የትብብር ስምምነቶች እንዳሏት አስታውቋል።
የግድቡ ዙሪያ የተፈጠረው ውዝግብ የሚፈታው በሦስትዮሹ የመርሆዎች መግለጫ እና በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ እንደሆነም አስታውቋል።
በሕብረቱ ማዕቀፍ ስር አስማሚ መፍትሄ የመገኘት እድሉም ገና እንዳልተሟጠጠ እና የግድቡን ግንባታ ፖለቲካዊ ገጽታ መስጠት ምንም ፋይዳ እንደማይኖረው ኢምባሲው ገልጿል።




