የዓለም የምግብ ድርጅት አውሮፕላን አደጋን ለመመርመር የኢትዮጵያ የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ ቡድን አደጋው ወደ ተከሰተበት ስፍራ ማቅናቱ ተገለፀ፡፡
ሐምሌ 20 ቀን ምስራቅ ሀረርጌ አደጋ የደረሰበትን ሴስና ካራቫን የዓለም ምግብ ድርጅት አውሮፕላን የአደጋ መንስኤ ለማጣራት የኢትዮጲያ የአውሮፕላን አደጋ መርማሪ ቢሮ ያዋቀረው ቡድን በዛሬው እለት አደጋው ወደ ደረሰበት ስፍራ አቅንቷል፡፡
የቢሮው ሀላፊ ኮሎኔል አምድዬ አያሌው ለኢትዮ የንግድ እና ኢንቨስትመንት መድረክ እንደገለጹት ንብረትነቷ የአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎት የሆነችው እና በአለም የምግብ ድርጅት በኪራይ የሚጠቀምባት ሴስና ካራቫን የምዝገባ ኮድ ET-AMI አውሮፕላን ሁለት አብራሪዎች እና ሁለት መንገደኞች አሳፍራ ከጂጂጋ የተነሳችው ከቀኑ 7 ሰአት ከ13 ደቂቃ ነበር፡፡
ወደ ድሬደዋ 33 ደቂቃ ከበረረች በኋላ 7 ሰአት ከ46 ደቂቃ ላይ ምስራቅ ሀረርጌ ሀሮማያ ኮምቦልቻ ወረዳ ከመለስተኛ አቀበት ጋር ተጋጭታ መውደቋ ተገልጿል፡፡
ሁለት አብራሪዎችና ሁለት መንገደኞች ጉዳት ሳይደርስባቸው ከአውሮፕላኗ እንደወጡም ታውቋል፡፡
አውሮፕላኗ ከአቀበቱ ጋር ልትጋጭ የቻለችው በወቅቱ በነበረው አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ እንደሆነ ይገመታል ሲሉም የቢሮው ሀላፊ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጲያ የአውሮፕላን አደጋ ምርመራ ቢሮ ያዋቀረው ቡድን በዛሬው እለት ወደ ድሬደዋ መንቀሳቀሱን የገለጹት ኮሎኔል አምድዬ ቡድኑ አደጋው በደረሰበት ስፍራ ተገኝቶ አስፈላጊውን መረጃ ሰብስቦ እንደሚመለስም ተናግረዋል፡፡
የአደጋ ምርመራ ስራው ሲጠናቀቅ ሪፖርቱ ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
የአውሮፕላኗ የበረራ መስመር አዲስ አበባ – ዋርዴር – ጂጂጋ – ድሬደዋ እንደነበር ታውቋል፡፡




