ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የሙስና ወንጀል መፈጸሙን ጸረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ

የሥነ-ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን በርካታ የሙስና ወንጀሎችን በምርመራ አግኝቻለሁ ማለቱ ተገለጸ። በነዚህም የሙስና ወንጀሎች የተገኘ 67 ሚሊዮን 642ሺሕ 635 ብርና ኹለት መኪና፣ እንዲሁም 521ሺሕ 415 ካ.ሜ. ቦታ ማገዱን አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪ 16 ሚሊዮን 927ሺሕ 462 ብር እና 889ሺሕ 640 ካ.ሜ. ቦታ ለመንግሥት ማስመለሱንም ገልጿል።

የሙስና ወንጀል ሥራዎችን በተመለከተ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና ከፖሊስ በመጣ መረጃ 22 ሚሊዮን 643ሺ 986 ብር ፣216 ካ.ሜ. ቦታ፣ 5 ኩንታል ስንዴ እና 11 ቪላ ቤት መታገዱም ታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪ 40ሚሊዮን 762ሺሕ 853 ብር፣ 6601 ካ.ሜ. ቦታ፣ 685 ቆርቆሮ፣ 3 ፓኬት ሚስማር እና 5 ላፕቶፕ ለመንግሥት ተመላሽ መደረጉን ኮሚሽኑ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ሙስናን ለመከላከል ከሚወሰዱ ተግባራት መካከል አንዱ ጥቆማ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ በዚህም 109 ጥቆማዎች ደርሰው በሕግ እንዲታዩ ማድረግ መቻሉን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ከነዚህም ውስጥ 71 የሚሆኑት ጥቆማዎች በዝርዝር ታይተው ለተጨማሪ ምርመራ ለፌደራል፣ ለአዲስ አበባ እና ለድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽኖች የተላኩ ሲሆን፣ 9 ጉዳዮች ደግሞ ለአማራ፣ ለኦሮሚያ እና ለደቡብ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤያን ሕጎች ተላልፈዋል ተብሏል።

በተጨማሪም ኹለት ከለላና አቤቱታ ሆነው በመገኘታቸው ለፌደራል ፖሊስና ለፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ኹለት ጉዳዮች በተወሰነው ውሳኔ መሰረት በተቋማት የአስቸኳይ የሙስና መከላከል በኩል እንዲሠራ ለሥነ-ምግባርና የሙስና መከላከል ዳይሬክቶሬት የተላኩ ሲሆን፣ አንድ ጉዳይ ደግሞ በተወሰነው ውሳኔ መሰረት ተቋሙ አጣርቶ እንዲገልጽ ለኢትዮጰያ የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም መላኩ ተገልጿል።

በዓለም ዐቀፍ ጸረ-ሙስና ኮንቬንሽን አማካይነት የሚከናወነውን ኹለተኛውን ዙር ሙስናን ለመከላከለል እና የተመዘበረ ንብረት ለማስመለስ፣ መረጃዎችን እና ቅድመ ዝግጅቶችን በማካሄድ ከፌደራል እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መረጃ የተሰበሰበ ሲሆን፣ ቀሪውንም መረጃ ለማሰባሰብ አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ ማወቅ ተችሏል።
የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍል አሠራሮችን ለማሻሻል የሚጠቅም መመሪያ ወጥቶ በሥራ ላይ እንደሚገኝም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ይህ መመሪያ የተቋማትን የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍሎችን ዝርዝር መረጃ (ፕሮፋይል) ለመያዝ፣ ወቅታዊ ለማድረግ የሚያስችል ሲሆን፣ በዚህም የ 31ሺሕ 599 የመንግሥት ተቋማትንና የልማት ድርጅቶችን መረጃ ማደራጀት እንደተቻለ ኮሚሽኑ ጠቅሷል። ከእነዚህም ውስጥ አራት ሺ 667 የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍሎች ማደራጀት መቻሉን በሪፖርቱ ጠቅሷል።

ኮሚሽኑ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል አንዱ የሀብት ምዝገባ ሲሆን፣ ተመራጮች፣ የመንግሥት ተሿሚዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች እና የመንግሥት የልማት ድርጅት ሠራተኞች ሀብትና ንብረት እንዲያስመዝገቡ በማድረግ በአጠቃላይ በአገር ዐቀፍ ደረጃ የ 1.5 ሚሊዮን 31ሺሕ 57 ግለሰቦችን ሀብት ማስመዝገብ መቻሉ ታውቋል።

ኮሚሽኑ ሙስናን ለመከላከል የሚያስችለውን የስምምነት ሰነድ በማዘጋጀት ከፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ለመስራት ያሰበ መሆኑን በላከው ሪፖርት ማወቅ ተችሏል።
እንደ ኮሚሽኑ ሪፖርት ከሆነ በሕግ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት ሀብታቸውን ያላሳወቁና ያላስመዘገቡ 3ሺሕ 355 አመራሮችና ሠራተኞች እያንዳንዳቸው አንድ ሺሕ ብር ቅጣት ተቀጥተው ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ መደረጉን አስታውቋል። በዚህም 3 ሚሊዮን 355ሺሕ ብር ለመንግሥት ገቢ መደረጉ ታውቋል።

የ620 ሀብት አስመዝጋቢዎችን መረጃዎች ትክክለኛነት ለማረጋገጥ፣ በተገኘው ውጤት ላይ እርምጃዎችን ለማስወሰድ ታቅዶ በ346 ሀብት አስመዝጋቢዎች ላይ የሀብት ምዝገባ መረጃ ትክክለኛነት የተረጋገጠ ሲሆን፣ በዚህም 10 ሀብት አስመዝጋቢዎች በተጨባጭ ባስመዘገቡትና በተረጋገጠው መረጃ መካከል ከፍተኛ የመረጃ ልዩነት መገኘቱንና በግኝቱ መሠረት የምርመራ እና ክስ ተግባር እንዲከናወን አስፈላጊው መረጃ ተጠናቅሮ ለፌደራል ፖሊስ እና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መላኩን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here