በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ ዕሮብ በ21/11/13 የተከሰተን የግለሰቦች ግጭት ምክንያት በማድረግ ወደ ከተማ በገቡ ታጣቂዎች ሳቢያ የሦስት ሰው ሕይወት ማለፉን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልጸዋል።
ወደ ከተማ የገቡት ታጣቂዎች ሕዝብ ላይ ጥቃት ማድረስ ሲጀምሩ መከላከያ ወደ ቦታው ሒዶ ወደ ላይ በመተኮስ ነገሮችን ለማረጋጋት ቢሞክርም፣ ከሦስት ሰዎች ሞት በተጨማሪ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች መቁሰላቸው ተገልጿል።
በዚህ ሒደት ውስጥ ታጣቂዎቹ የሦስት ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ ማድረጋቸውን የሚገልጹት ምንጫችን፣ ሌሎችም ጉዳት የደረሰባቸው እንዳሉና በመጨረሻ ግን ታጣቂዎቹ በመከላከያ ኃይል ከተማውን ለቀው እንደወጡ ጠቁመዋል።
በመተከል የሚፈጸመው ግድያና አፈና አሰቃቂ መሆኑን የጠቆሙት የአዲስ ማለዳ ምንጮች፣ የመንግሥት ቸልተኝነት በንጹሐን ዜጎች ላይ ለሚደረስው ጥቃት ሚና እንዳለው ጠቁመዋል። በዞኑ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ የማሕበረሰብ ከፍሎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ማሕበረሰቡን ቢቀላቀሉም፣ በዜጎች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት መሻሻል እንዳላሳየ ተመላክቷል።
በዞኑ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ኃይል ንጹሐን ዜጎች ላይ የሚፈጽመው ጥቃት እንዲቆም የሚፈልግ የመንግሥት አመራር ያለ አይመስልም ሲሉ ኗሪዎች ጠቁመዋል።
ከጫካ ተመልሰው የተሃድሶ ስልጠና ወሰደዋል የተባሉ አካላት የክልሉ መንግሥት በየወረዳው ሥልጣን እንደሰጣቸው የሚታወስ ነው። ይሁን አንጅ ታጥቀው ይንቀሳቀሱ ከነበሩት መካከል ሥልጣን የተሰጣቸው ግለሰቦች የሚፈልጉት ሥልጣን እንዳልሆነ የሚያሳዩ ተግባራትን እየፈጸሙ ነው ተብሏል። በዚህም ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ በውል ለማወቅ እንዳልተቻለም ለግለሰቦቹ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጠቁመዋል።
የመተከል ዞን ሕዝብ በአሁኑ ስዓት ከበቂ በላይ ችግር ስላስተናገድ ሠላም እንደሚፈልግ የጠቆሙት ኗሪዎቹ፣ መንግሥት ችግሩን ለማስቆም ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
በአሁን ወቅት መተከል ላይ የታረሰ መሬት እንደሌለ ተገልጿል። በዚህም የዞኑ ሕዝብ በሚቀጥለው 2014 ለረሀብ ሊጋለጥ ይችላል የሚል ስጋት ተፈጥሯል። በመተከል ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ይኖሩ የነበሩ ዜጎች በተለያዩ ጊዜያት በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ተፈናቅለው አሁን ላይ በዞኑ በተመረጡ ቦታዎች በመጠለያ ካምፕ ይገኛሉ።
በመጠለያ ጣቢያ ተጠልለው ጥበቃ እየተደረገላቸው የሚገኙ ዜጎች፣ በነጻነት መንቀሳቀስ እንዳልቻሉና የክልሉ መንግሥት አመራሮች በቁርጠኝነት ከሠሩ የታጠቀውን ኃይል ማስቆም እንደሚቻል ጠቁመዋል። ይሁን እንጅ እስካሁን በታየው የአመራር ሥራ ውጤት አለመምጣጡን የሚገልጹት የአዲስ ማለዳ ምንጮች፣ ከችግሩ ጀርባ የአመራሮች እጅ እንዳለበት በርካታ ማሳያዎችን ታዝበናል ብለዋል።
በዞኑ በተደጋጋሚ በንጹሀን ዜጎች ላይ በሚፈጸመው ጥቃት ሙሉ በሙሉ የአመራሩ እጅ እንዳለበት የሚናገሩት የአዲስ ማለዳ ምንጮች፣ ከዚህ በፊት የመተከል ዞን ሕዝብ አሁን ታጥቀው ጥቃት ከሚፈጽሙት የማሕበረሰብ ከፍሎች ጋር አብሮ የኖረ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመተከል ዞን የሚፈጸው ጥቃት ከዓመት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ችግሩ እንደቀጠለ ነው። ዞኑ የጸጥታ ችግር ቀጠና መሆኑን ተከትሎ በኮማንድ ፖስት እየተመራ እንደሚገኝ የሚታወቅ ነው። በዞኑ ከሚገኙ ወረዳዎች ተፈናቅለው አካባቢውን ለቀው የወጡ ከ50 ሺሕ በላይ ዜጎች ከሰፈሩበት ቦታ ወደ ዞኑ ተመልሰው በተመረጡ አካባቢዎች በመጠለያ ካምፕ እየኖሩ ይገኛሉ።
ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013


