በፌደራል መንግሥትና በሽብረተኝነት በተፈረጀው ሕወሓት መካከል የተፈጠረው ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ ያልተጠበቁ ነገሮች እየተከሰቱ ነው። በኹለቱ አካላት መካከል የተፈጠረው ልዩነት ከቃላት መወራወር ወደ ኃይል ማምራቱን ተከትሎ እስካሁን መቋጫ ያላገኘው ጦርነት ቀስቅሷል።
በሽብርተኝነት በተፈረጀው ሕወሓትና የፌደራል መንግሥት መካከል የሚደረገው ጦርነትን ተከትሎ ከሕወሓት ጋር ቁርኝት አላቸው የተባሉ የንግድ ቤቶች እየተዘጉና ሰዎች እየታሰሩ ነው። የንግድ ቤቶች መዘጋትና የሰዎች መታሰር ወደ አዲስ አበባ ዘልቆ መግባቱ የሚታወቅ ሲሆን፣ አዲስ አበባ ላይ የሚገኙ ከሕወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ የንግድ ቤቶች ታሽገዋል። ከዚሁ ጋር በተያዘያ ለእስር የተዳረጉ ግለሰቦችም አሉ።
አዲስ አበባ የኹሉም ክልል ተወላጆች ለመኖሪያነትና ለመነገጃነት መርጠዋት የሚኖሩባት የኢትዮጵያዊያን የጋራ ዋና ከተማ ነች። በአዲስ አበባ ከኹሉም ክልል የመጡ ዜጎች በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ አሁን ያለው ወቅታዊ የፖለቲካና ጦርነት ሁኔታ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ አንዳንድ የንግድ ቤቶች መዘጋትና ለግለሰቦች መታሰር ምክንያት ሁኗል። የታሸጉት የንግድ ተቋማት የትግራይ ክልል ተወላጆች ንብረት መሆናቸው መንግሥት እየወሰደ ያለው እርምጃ ሕጋዊ መሠረት ያለው ነው ወይስ ማንነት ላይ ያነጣጠረ የሚለው ጉዳይ መልስ የሚፈልግ ሆኗል።
መንግሥት ሕግ በመጣስ የጠረጠራቸውን በአዲስ አበባ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች የንግድ ቤቶችን መዝጋትና ግለሰቦቹን ማሰር በአብዛኛው የጀመረው የፌደራል መንግሥት ከስምንት ወር ቆይታ በኋላ በተናጠል ተኩስ አቁሞ ትግራይን ለቆ በወጣ ማግስት መሆኑ የሚታወስ ነው። ለንግድ ቤቶቹ መዘጋት ምክንያት ናቸው ተብለው በመንግሥት በኩል ከተገለጹት መካከል በተለይ የታሸጉት ባለኮከብ ሆቴሎች መከላከያ ሠራዊተን የሚያዋርዱ ተግባራት በመፈጸማቸው፣ በሽብርተኝነት የተፈረጀውን ሕወሓትን በገንዘብ በመደገፋቸውና መመሪያ በመተላለፋቸው መሆኑ ተገልጿል።
መንግሥት ባቀረበው ምክንያት ከታሸጉ የንግድ ተቋማት መካከል አብዛኛዎቹ ባለኮከብ ሆቴሎች፣ ባርና ሬስቶራንት ናቸው። ከባለኮከብ ሆቴሎች በተጨማሪ በከተማዋ የሚገኙ ትናንሽ የንግድ ቤቶች ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ መታሸጋቸውን አዲስ ማለዳ ታዝባለች። የታሽጉት ትናንሽ የንግድ ቤቶች እንደ ቡና ቤት፣ ሻይ ቤትና ቁርስ ቤትን ያካተቱ ሲሆኑ፣ በተለያዩ የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢዎች የሚገኙ ናቸው። አዲስ ማለዳ እንደሰማችው ከሆነ ትናንሽ ንግድ ቤቶቹ የታሸጉት ከሕወሓት ጋር የተገኛኙ ፖለቲካዊ ሐሳቦችን በማራመዳቸው ነው ተብሏል።
ይሁን እንጅ በመንግሥት እየታሽጉ ያሉ የንግድ ቤቶች ከትግራይ ክልል ተወላጆች ጋር የተገናኙ መሆኑን ተከትሎ፣ የክልሉ ተወላጆች ላይ የመብት ጥሰትና ስጋት የሚፈጥር ጉዳይ እንዳይሆን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ብዙዎች ስጋት አላቸው።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰማኮ) ከኹለት ሳምንት በፊት ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ፣ አዲስ አበባን ጨምሮ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የደርሰውንና በትግራይ ተወላጆች ላይ የደርሰ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስር፣ የንግድ ቤት መዘጋት እና የእንግልት መረጃ እየተከታተለ እንደሆነ ገልጿል።
ከሰኔ 22/2013 ጀምሮ ተባብሶ የታየው ክስተት ተገቢውን ትኩረትና መፍትሔ ካለማግኘቱ በተጨማሪ፣ በስፋት የሚደመጡ የጥላቻና ግጭት ቀስቃሽ ንግግሮች ሁኔታውን ሊያባብሱና ብሎም በማኅበረሰቦች መካከል ያለውን ትስስር ሊያላሉ የሚችሉ ናቸው ሲል ኮሚሽኑ በመግለጫው ጠቅሷል። በአዲስ አበባ የንግድ ቤቶች መታሸግ የጀመረው የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ በወጣ ማግስት መሆኑን የኮሚሽኑ መግለጫ ያጠናክራል።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገረቻቸው የሕግ ባለሙያው ካፒታል ሄኖክ፣ የንግድ ተቋማት በኹለት መንገድ ሊታሸጉ እንደሚችሉ ይገልጻሉ። አንደኛው በጊዜያዊነት የሚታገድ ሲሆን፣ ኹለተኛው መንገድ የንግድ ተቋማት ሥልጣን በተሰጠው አካል በቋሚነት የሚታገዱበት መሆኑን ገልጸዋል።
በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ተቋማትን የማሸግና ከሥራ ማገድ የሚችለው ሥልጣን የተሰጠው አካል ብቻ መሆኑን የሚጠቁሙት የሕግ ባለሙው፣ የንግድ ተቋማትን ከሥራቸው ለማገድ በቅድሚያ በሕግ አግባብ የተረጋገጠ መሆን እንዳለበት ይገልጻሉ። የንግድ ተቋማትን የማሽግ ሥልጣን ያለው አካል ተቋሙ ፈቃድ ከተሰጠው ሥራ ውጪ ሲሠራ ከተገኘ፣ መክፈል የሚገባውን ግብር በወቅቱ ካልከፈለና የተገልጋዮች መብትን ከጣሰ በሕግ አግባብ ሊታገድ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ይሁን እንጅ የንግድ ተቋማት ሲታሸጉ በተለይ ማንነት ላይ ያነጣጠረ የሚመስል ነገር ሲኖር በከፍተኛ ጥንቃቄ ነገሮች ከሕግ አግባብ ውጪ እንዳይፈጸሙ መጠንቅ እንደሚገባ ሙያዊ ሐሳባቸውን አካፍለዋል። የሕግ ባለሙያው ይህን ያሉት የንግድ ተቋማት ሊታሸጉ የሚችሉት በሕግ የተቀመጡ ቅድመ ኹኔታዎችን ሲጥሱ፣ ግብር ሳይከፍሉ ሲቀሩ እና በሚሰጡት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ላይ ችግር ከተፈጠረ መሆኑን በማስታወስ ነው።
የንግድ ተቋማት ከላይ የተጠቀሱትን የሕግ ገደቦችን ጥሰው ከተገኙ በማንኛውም ጊዜ ሊታሸጉ እንደሚችሉ የሚገልጹት ካፒታል፣ የንግድ ተቋማትን የማሸግ ሥልጣን ያለው አካል ተቋሞቹን ሲያሽግ በማንነት ላይ ያነጣጠሩ እንዳይመስሉ በሕግ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን መከተል እንዳለበት መክረዋል። የንግድ ተቋማትን የማሸግ ሥልጣን ያለው አካል የሕግ አካሄዶችን ያልተከተሉ እገዳዎች ካደረገ በማንነት ላይ ያነጣጠረ እንዳይመስልና ሌላ ትርጉም እንዳይሰጠው ከፍተኛ ጥንቃቅ ማድረግ እንደሚገባ ባለሙያው አሳስበዋል።
በአዲስ አበባ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች የንግድ ተቋማት እሽጋ ከማንነት ጋር የተገናኘ እንዳይሆን ስጋት እንዳለ በሚዲያዎች ሲገለጽ ተሰምቷል። የንግድ ቤቶቹ መታሸግ ከማንነት ጋር የተያያዘ አንድምታ እየፈጠረባቸው እንደሆነ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት መግለጻቸውን ኢትዮ ኤፍ ኤም ባሳለፍነው ሳምንት ዘግቧል።
ኢትዮ ኤፍ ኤም እንደዘገበው ከሆነ፣ በአዲስ አበባ ከተፈጠረው ክስተት ጋር በተያያዘም ኑሯቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የትግራይ ተወላጅ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ከጸጥታ አካላት እና ከአዲስ አበባ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ጋር በተወያዩበት ወቅት ይህን ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የፌደራል መንግሥት ትግራይን ሰኔ 21/ቀን 2013 ለቆ መውጣቱን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሆቴሎች፣ መጠጥ ቤቶችና ምሽት ቤቶች ሲታሸጉ በመንግሥት በኩል ከተሰጡ ምክንያቶች መካከል አንደኛው በሽብርተኛነት የተፈረጀውን ሕወሓትን መደገፋቸው ነው።
የሕግ ባለሙያው ካፒታል እንደሚሉት፣ ባለፈው ዓመት ተሻሽሎ ሥራ ላይ በዋለው የጸረ ሽብር አዋጅ መሠረት፣ በሽብርተኝንት ከተፈረጀ ድርጅት ጋር ግንኙነት ያለውና የሚደግፍ አካል እንደ ሽብርተኛ እንደሚቆጠር ይናገራሉ። የታሸጉት የንግድ ተቋማትም ይሁኑ የታሰሩ የንግድ ተቋማቱ ባለቤቶች በሕግ የተቀመጠውን ገድብ አልፈው ከተገኙ በሕግ አግባብ የመጠየቅ ግደታ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የታሸጉ የንግድ ተቋማትና የታሰሩ ሰዎችን መንግሥት እንዳለው በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ድርጅት ጋር ግንኙነትና ድጋፍ ያደረጉበት ማስረጃ ከተገኘ ተገቢ እንደሚሆን ጠቁመዋል። በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ድርጅት ጋር ግንኙነት ማድረጋቸውና ድጋፍ ማድረጋቸውን አረጋግጦ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በኹለተኛ ደረጃ ለንግድ ተቋማቱ መታሽግ ምክንያት የሆነው በመከላከያ ሠራዊት ላይ ስም የማጥፋትና የማራከስ ተግባር ፈጽመዋል ተብለው ሲሆን፣ የንግድ ተቋማቱ በመንግሥት የተጠቀሰውን ተግባር ፈጽመው ቢገኙም እንኳን፣ ገለልተኛ የንብረት አስተዳደር ተቋቁሞ የንግድ ተቋማቱን ችግር በሕግ መፍታት የሚቻልበት አግባብ እንዳለ የሕግ ባለሙያው አንስተዋል።
የሕግ ባለሙያው እንደሚሉት፣ በአጠቃላይ በአዲስ አበባ የታሸጉ የንግድ ተቋማትን ጉዳይ ትክክል ነው አይደለም ብሎ ለመወሰን የተጠረጠሩበት የሕግ ጥሰት መፈጸሙን ማረጋገጥ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል። ይሁን እንጅ መንግሥት እየሠራው ያለው ሥራ ከሕግ አግባብ ውጭ እንዳይፈጸምና ሌላ ትርጉም እንዳይፈጥር መጠንቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአዲስ አበባ የታሸጉ የንግድ ተቋማት በስራቸው የሚስተዳድሯቸው ሠራተኞች ለጊዜውም ቢሆን ከሥራ ውጭ መሆናቸውን ተከትሎ ለችግር እና እንግልት እንዳይዳረጉ በመንግሥት በኩል ተገቢ ጥንቃቄ የተሞላበት የሕግ ስርዓት መከተል እንደሚገባም ተገልጿል።
ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013



