የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዲስ ሕንጻ ግንባታ ከቆመ ወራትን በማስቆጠሩ የአደጋ ስጋት መፍጠሩ ተገለጸ

0
745

ከተመሰረተ ስልሳ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረው የቀድሞው ‹‹የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር ቤት›› የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤትን ለማዘመን በማሰብ ከአጠገቡ አዲስ ሕንጻ ለመገንባት ታቅዶ ወደ ግንባታ ቢገባም የግንባታው ሒደት ግን በሚፈለገው ደረጃ እየተጓዘ እንዳልሆነ በቴአትር ቤቱ ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ከመነሻው ጀምሮ ከነባሩ ሕንጻ አጠገብ አዲሱ መገንባት የለበትም የሚሉ ባለሙያዎች በሰፊው ድምጻቸውን ሲያሰሙ የነበሩ ቢሆንም ግንባታው መጀመሩ ይታወሳል።
በወቅቱ ግንባታውን በአፍሮ ጽዮን ሥራ ተቋራጭ ድርጅት አማካይነት ለመገንባት ወደ ሥራ ቢገባም፣ አሁን ላይ የሕንጻው ግንባታ ሙሉ በሙሉ መቆሙ ተገልጿል።
ግንባታው ከቆመ ስድስት ወራት ተቆጥረዋል የሚሉት ስማቸውን መናገር ያልፈለጉት የቴአትር ቤቱ ባለሙያ፣ “አጉል ቦታ ላይ ነው የቆመው” ሲሉም ይናገራሉ። ነባሩ ሕንጻ እንዳይወድቅና እንዳይሸረሸር የሚረዳው ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ተገንብቶ ሳያልቅ መቆሙ ነባሩ ሕንጻ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ሲሉም ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ተቋራጩ ሥራውን በአግባቡ ባለመሥራቱ ውሉ መቋረጡን የሚያነሱት ደግሞ በከተማ ልማት በኩል የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ተክለጻዲቅ ተክለአረጋይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት ነባሩ ሕንጻ የመውደቅና የመሸርሸር አደጋን በተመለከተ “ሥራ ተቋራጩ ሲወጣ መሥራት የነበረበት ቢሆንም፣ ለመሥራት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት ሳይሠራ ወጥቷል። ሆኖም በአሁን ሰዓት ላይ በልዩ ሁኔታ ከመንግሥት አስፈቅደን በሌላ ተቋራጭ በነባሩ ሕንጻ ላይ አደጋ እንዳይደርስ የመከላከል ሥራ በመሠራት ላይ ነው” ይላሉ የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ።
የግዢ ኤጀንሲን አስፈቅደን፣ የተሻለ ተቋራጭን መርጠን ቀድሞ የነበረው ተቋራጭ ይሠራበት በነበረው ዋጋ እንዲሰራ አግባብተን ከክረምቱ እና ከውኃ ጋር በተያያዘ በነባሩ ሕንጻ ላይ አደጋ እንዳይደርስ የመከላከል ሥራ ለመሥራት ሞክረናል በማለት ያለውን ሒደት ያስረዳሉ።
ቀሪ የሕንጻውን ሒደት በተመለከተ ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን የሰጡት ተክለጻዲቅ ተክለአረጋይ፣ ሌላ ሥራ ተቋራጭ ለማወዳደር እንዲረዳ የሰነድ ዝግጅት እንደጨረሱ የገለጹ ሲሆን፣ ሆኖም የጨረታ ሒደት ረጅም ጊዜ ስለሚወስድ የበላይ አመራሩ በልዩ መልክ ይሠራል ብሎ ለሚያምነው የሥራ ተቋራጭ በቀጥታ ግንባታውን ሊሰጠውም ይችላል ብለዋል። ይህ ካልሆነ ግን ነሐሴ ወር ላይ አዲስ ሥራ ተቋራጭ ለማስገባት ጨረታ እንደሚወጣም ገልጸዋል።
አዲስ የሚገነባው ሕንጻ ባለ12 ወለል እና በሰባት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍ ሲሆን፣ 1.5 ቢሊዮን ብር ወጪም ያስወጣል ተብሏል። አዲሱ ሕንጻ የቴአትር መስሪያ ቦታዎችን ቁጥር ከመጨመሩ ባለፈ፣ የጊዜውን ዘመናዊነት የሚያሟላና ሙዚየምን ጨምሮ የተለያዩ መገልገያዎችን የሚይዝ እንደሚሆን ተገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here