ምርት ገበያ ቡናን ወደ ውጭ ለመላክ የቀጥታ ግብይት ሥርዓት መጀመሩ ተገለጸ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቡናን ወደ ውጭ ለመላክ የቀጥታ ግብይት መጀመሩን አስታወቀ። በዚህም በምርት ገበያው በኩል ወደ ውጭ የሚላኩ ቡናዎች መጠን እንዲቀንስ ማድረጉን ምንጮች ጠቁመዋል።
በበጀት ዓመቱ በቀጥታ የተገበያየው የቡና መጠን 248 ሺሕ ቶን ሲሆን፣ ከምርት ገበያው ውጭ 90 በመቶ ግብይት ተፈጽሟል። በዚህም በኢትዮጵያ ካለፉት አስርት ዓመታት ወዲህ በቡና ይገኝ የነበረውን ከ600 እስከ 800 ሚሊዮን ዶላር ወደ 970 ሚሊዮን ማሳደግ ተችሏል።

ባለፈው ኹለት ዓመት አንድ ቶን ይሸጥ ከነበረበት ከ2800 ዶላር የግብይት መጠን ወደ 4000 ዶላር ማደጉ ታውቋል።
ላኪዎች እና አቅራቢዎች በቀጥታ ከገዢዎች የሚልኩትን የቡና ጥራት፣ ምርት ገበያው ደረጃውን ዝቅ እያደረገ ይልክ የነበረበትን አሰራር ማስቀረት መቻሉን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
አዱኛ አክለውም ላኪዎች በምርት ገበያው በኩል በሚያስተላልፉበት ወቅት በማከማቻ ውስጥ ደረጃቸው ዝቅ ባሉ ቡናዎች እንደሚቀየርባቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ ነጻነት ተስፋዬ በበኩላቸው፣ ቡና የሚላክላቸው አገራት በምርት ገበያው በኩል ተገበያየቶ የሚደርሳቸው ጥራቱን ያልጠበቀ ቡና ነው በማለት ቅሬታ ማንሳታቸውን ያረጋገጡ ሲሆን፣ ስህተት ተፈጥሮ ያለፉ በመኖራቸው የሚከሰት እንደሆነ ነጻነት ጠቁመዋል። ተቋሙ ደረጃ በመስጠት ቡናዎቹን በምርምር ሒደት ካሳለፈ በኋላ ላኪዎች ቡናውን ሲወስዱ ቅሬታ ካላቸው ድጋሚ እንዲታይ ማስደረግ የሚችሉ እንደሆነ የጠቆሙት ነጻነት፣ በራሳቸው መንገድ መርምረው መላክ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል።

ተቋሙ 2000 ለሚሆኑ ተገበያዮች የአቅም ግንባታ ሥልጠና በመስጠት ባለሙያ(ሰርቲፋይድ) ማድረግ ችሏል። ይህ የአቅም ግንባታ መፍጠር ተገበያዮች ያለተቋሙ እገዛ በራሳቸው ወደውጭ የሚልኩበትን አማራጭ በመፍጠር አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ አድርጓል።

የቡና ግብይት ከአገሪቷ ኢኮኖሚ ትልቁን ድርሻ የያዘ መሆኑ ይታወቃል። በመሆኑም በበጀት ዓመቱ 25 በመቶው ገቢ የተገኘው ከቡና ነው። የቡና ግብይትን ትልቅ ደረጃ ለማድረሰ በመንግሥት በኩል ማሻሻያ መደረጉን ነጻነት ጠቁመዋል። ባለፉት አራት ዓመታት የማሻሻያ ሥራዎች በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ መሪነት ሲካሄድ ቆይቷል።

በዚህ ላይ ተቋሙን ጨምሮ፣ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን፣ ቡና አቅራቢዎችና ቡና ላኪዎች፣ ብሔራዊ ባንክ፣ ገቢዎች እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ማሻሻያ ተደርጓል።
ይህ ማሻሻያ ተግባራዊ ሲሆን ምርት ገበያው ቡና ማገበያየቱን የሚቀጥል መሆኑን ነጻነት ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

ማሻሻያው የራሳቸው የእርሻ ቦታ ያሉ አርሶ አደሮች በቀጥታ ለላኪዎች በመሸጥ ላኪዎች ደግሞ ተቋሙ ሳይገባ ወደ ውጭ የሚልኩበትን አማራጭ ፈጥሯል።
ምርት ገበያው 218 ሺሕ ቶን ቡና አገበያይቷል። ይሕም ከዕቅዱ 99 በመቶ ማሳካት ተችሏል። በምርት ገበያው ያለፈው የጥራት ጉድለት ቢኖርበትም እንኳን ወደ ውጭ ከመላኩ በፊት በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ማዕከላዊ የምርምር ጣቢያ እንደሚፈተሸ ተናግረዋል።

በማሻሻያው ላኪዎች በቀጥታ ወደውጭ በሚልኩበት ወቅት ምርት ገበያ በማገበያየቱ የሚያገኘውን 0.04 በመቶ ገቢ የሚያጣ ሲሆን፣ ሌሎች አዲስ በሚጀምራቸው የግብይት ግብዓቶች ለማካካስ ማቀዱን ሰምተናል።
በሌላ በኩልም ምርት ገበያው ወንበር መሸጡን አቁሟል። ኅብረት ሥራ ማኅበራት ወንበር ገዝተው እንዲገቡ ተደርጓል። 30 የአገናኝ አባላትን ወደ ምርት ገበያው ማስገባት ተችሏል።

የ2013 በጀት ዓመት ተቋሙ ከሚያገበያያቸው 13 አይነት ምርቶች፣ ከ614 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ምርት በ39.6 ቢሊዮን ብር ያገበያየ ሲሆን፣ በዚህም ከዕቅዱ 96 በመቶ ማሳካት መቻሉ ተገልጿል። ከተጠቀሰው ምርት 35 በመቶውን የቡና ግብይት እንደሚይዝ ታውቋል።

ይህን ያህል ግብይት ለመፈጸም የታክስ ስርዓቱን የተጠቀመ ሲሆን፣ 1.7 ቢሊዮን ብር ለመንግሥት ገቢ ማድረግ ችሏል።
የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች በመከፈታቸው ግብዓት እንደሚያስፈልጋቸው ይታወቃል። ይህን የግብዓት ፍላጎት ለማርካት በዚህ ዓመት ከጥቅምት ጀምሮ 430 ሺሕ 680 ቶን አኩሪ አተር ለዘይት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ማቅረብ ተችሏል። ይህ ደግሞ ከውጭ የሚገባውን ዘይት በመቀነስ የአገር ውስጥ ምርት በመጨመር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነጻነት ተናግረዋል።

ምርት ገበያው ከማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ጋር በመፈራረም በቀጣይ ዓመት የማዕድን ምርቶችን ለማገበያየት ዕቅድ ይዟል። ኦፓል፣ ሳፋይር እና ኤመራልድ የተባሉትን የጌጣጌጥ ማዕድናት ለማገበያየት ዝግጅት እያደረገ ነውም ተብሏል። ምርት ገበያው በበጀት ዓመቱ ኹለት ቅርንጫፎችን በመክፈት የቅርንጫፎቹን ቁጥር 25 አድርሷል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የአይቲ ሲስተሙ ጠንካራ በመሆኑ እና የራሱ የመረጃ ማዕከል (ዳታ ሴንተር) ያለው በመሆኑ መንግሥት ላቀደው የስቶክ ማርኬት ግብይት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆኑንም አስታውቋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here