በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የሚሠሩ ሠራተኞች የአንድ ወር ደሞዝ በግዴታ እየተቆረጠ ነው

0
1133

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ባሉ መሥሪያ ቤቶች የሚሠሩ የመንግሥት ሠራተኞች ለመከላከያ ሠራዊት የከተማ አስተዳደሩ ለሚሰበስበው ድጋፍ በግዴታ የአንድ ወር ደሞዛቸውን እንዲሰጡ እየተገደዱ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

በከተማ አስተዳደሩ ስር በሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ደሞዝ እየተከፈላቸው የሚሠሩ የመንግሥት ሠራተኞች የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለመከላከያ ሠራዊት በፈቃደኝነት እንዲሰጡ የሚያዝ ድብዳቤ ቢደርሳቸውም፣ ደብዳቤውና አተገባበሩ ተቃራኒ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በስሩ ለሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያስተላለፈውን የድጋፍ ማሰባሠቢያ ቅጽ (ፎርም) አዲስ ማለዳ ተመልክታለች። ድጋፍ ማሰባሠቢያ ቅጹ “በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች ለአገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ማድረጊያ የቃልኪዳን ሰነድ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ነው።

ከተማ አስተዳደሩ ያሰራጨው የቃል ኪዳን ሰነድ ቅጽ፣ የድጋፍ አድራጊውን ሙሉ መረጃ እና በወር የሚያገኘውን የተጣራ ደሞዝ ያካተተ ሲሆን፣ ድጋፉ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ይገልጻል። “ድጋፍ የሚደረግበት ጊዜ የአንድ ወር የተጣራ ደሞዝ በአንድ ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ(ከሐምሌ 1/2013 እስከ ሰኔ 30/2014 ድረስ) ይሆናል” ይላል ለሠራተኞች የደረሳቸው የድጋፍ ማድረጊያ ቅጹ።

በከተማ አስተዳደሩ ስር ለሚገኙ መሥሪያ ቤቶች የተሰራጨው የድጋፍ ማሰባሠቢያ ቅጹ ሠራተኛው “ለኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ የሚሆን በወር ከማገኘው የተጣራ ደሞዜ ላይ በየወሩ እየተቆረጠ በአንድ ዓመት ለመክፈል በፈቃደኝነት የፈረምኩ መሆኑን አረጋግጣለሁ” ይላል። ይሁን እንጂ፣ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በከተማ አስተዳደሩ ስር በሚተዳደሩ መሥሪያ ቤቶች የሚሠሩ የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዛቸው እንዲቆረጥ የፈረሙበት ደብዳቤ ላይ እንደተገለጸው በፈቃደኝነት ሳይሆን ተገደው መሆኑን ጠቁመዋል።

ሠራተኞቹ እንደሚሉት፣ በፈቃደኝነት የሚሰጥ ከሆነ እያንዳንዱ የመንግሥት ሠራተኛ በፈቃደኝነት የሚችለውን ያህል እንዲከፍል መደረግ ነበረበት ብለዋል። ይሁን እንጅ ደብዳቤው ላይ የተገለጸው ግዴታ ከመሆኑ በላይ፣ በፈቃደኝነት ቢሆንም እያንዳንዱ ሠራተኛ በአቀሙ ልክ የፈቀደውን እንዲሰጥ መደረግ እንደነበረበት ተናግረዋል።

ከከተማ አስተዳደሩ በተሰራጨው የድጋፍ ማሰባሰቢያ ደብዳቤ የአንድ ወር የተጣራ ደሞዝ ስለሚል፣ የአንድ ወር ደሞዛቸውን ድጋፍ ለማድረግ አቅም የሌላቸውና ፈቃደኛ ያልሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች በተቀበሉት ደብዳቤ ላይ እንደየአቅማቸው ከአንድ ወር ደሞዛቸው በታች ሞልተው ቢልኩም አይቻልም ተብሎ እንደተመለሰባቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

የደሞዛቸውን 20 እና 50 በመቶ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆናቸውን በፊርማቸው ያረጋገጡ የመንግሥት ሠራተኞች አይቻልም ተብለው ሙሉ የአንድ ወር የተጣራ ደሞዛቸወን ለመስጠት እንዲፈርሙ ዳግመኛ ደብዳቤ እንደደረሳቸው አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።

ይህን ለማድረግ ፍቃደኛ ያልሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች ይህ ዘጋባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ የሐምሌ ወር ደሞዛቸው እንዳልተለቀቀላቸው ተናግረዋል። ደሞዛቸው ካልተለቀቀላቸው የመንግሥት ሠራተኞች ውስጥ መምህራን ይገኙበታል። መምህራኑ ከዚህ ቀደም ከ23 እስከ 28 ድረስ ባሉት ቀናት ይለቀቅ የነበረው ደሞዝ በመዘግየቱ የቤት ኪራይና ሌሎች መሠረታዊ ፍጆታዎችን ለሟሟላት መቸገራቸውን ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚሠሩ የአንድ ወር የተጣራ ደሞዛቸውን ሳይሆን በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የአቅማቸውን ድጋፍ ለመከላከያ ሠራዊት ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን የገለጹ ሠራተኞችን ቅሬታ ይዛ ወደ ከተማ አስተዳደሩ አቅንታለች።

አዲስ ማለዳ ከከተማ አስተዳደሩ ያገኘችው መረጃ እንደሚመላክተው ከሆነ መንግሥት ቀድሞ ከካዝናው 734 ሚሊዮን ብር ከፍሏል፡፡  አጠቃላይ የመንግሥት ሠራተኞች ደምወዝ እንዲቆረጥ ሁሉም ቀድሞ መስማማቱ የተገለጸ ሲሆን፣ አሁን ላይ መንግሥት ከካዝናው ስለከፈለ ደሞዝ መቆረጡ ግዴታ መሆኑ ተገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here