እያደር እየጨመረ ሕብረተሰቡንም እያማረረ የመጣው የኑሮ መወደድ ሕዝብን ወደ አልተፈለገ መንገድ ከመምራቱ በፊት ሊታሰብብት ይገባል። ልክ እንደጦርነት የዋጋ ግሽበቱ ሕዝብን በጅምላ የሚጎዳ እንደመሆኑ የመንግሥትን ትኩረት እንዲሁም የባለሀብቱንም እገዛ የሚፈልግ ነው።
ጠላት በሚተኮስ የጦር መሣሪያ ብቻ ሳይሆን፣ በማይታይ፣ በቀጥታ ሕዝብን አጥቅቶ በሚያስቆጣና ከመንግሥት ለይቶ በሚያስቀር ድምጽ በሌለው መሣሪያ ሊያጠቃ እንደሚችል ሊታወቅ ይገባል። መንግሥት የዋጋ ግሽበት መኖሩን ባይክድም መጠኑ ግን ሌሎች ከሚሉት አኃዝ ጋር እንደሚለያይ ይነገራል። የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን የተወሰኑ ምርቶች ላይ ተመርኩዞ የሚያወጣው የዋጋ ግሽበት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በሐምሌ ወር በ26.4 በመቶ መጨመሩን ይፋ አድርጓል። በሰኔ ወር 24.5 በመቶ የነበረው የዋጋ ግሽበት በግንቦት ወር ከነበረው 19.7 በመቶ ጨምሮ እንደሆነ ይታያል።
የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበት አለካክ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች ከባለሙያዎች ቢሰነዘርም፣ መንግሥት የተቀበለውን እንኳን ብንወስድ በየወሩ የዋጋ ግሽበቱ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል። የቀደሙ ወራትን የዋጋ ግሽበት ከተመለከትን ያለፈው ወርን የሚስተካከል የለም። ዓመታትን አነጻጽረን ከተመለከትን ደግሞ ከ1966 አብዮት ወዲህ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የታየበት አመት የፈረንጆቹ 2008 ሲሆን፣ አማካዩ 44 በመቶ ገደማ ነበር። ቀጣዩ በ1991 የተመዘገበው ሲሆን፣ ከ35 በመቶ በላይ ነበር። በ2011 የፈረንጀቹ አመት 32 በመቶ፣ እንዲሁም በ1976 ላይ 28 በመቶ ተመዝግቧል። የዓለም ባንክ ካወጣው ከዚህ መረጃ አንፃር ኢትዮጵያን ፈትነዋት ካለፉት ከእነዚያ ውድ አመቶች ቀጥሎ የባለፈው ወር አኃዝ በቀጣይነት የሚቀመጥ ነው።
የትኛውም ቁጥር የኑሮ መወደዱን ከሚነግረን በላይ የሕብረተሰቡ ስሜት ዋናው የግሽበቱ ጠቋሚ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ሆድ ጠኔን መቋቋም በማይችልበት በክረምት ወራት የኑሮ ውድነቱ እንቅልፍ ያሳጣቸው ነዋሪዎች በለሊት ወጥተው ዝናብ እየወረደባቸው ሸማቾች ማኅበር በር ላይ በረጅሙ ተሰልፈው ዱቄት ለመግዛት አንጀት በሚበላ አኳኋን ሲጠብቁ ማየት እየተለመደ መጥቷል። አብዛኞቹ አቅመ ደካማ እናቶች ሲሆኑ፣ ልጆችና ወረፋውን እየጠበቁ መቆም ያቃታቸው እናቶች በየጥጋጥጉ ተወሽቀው ማየቱ ምን ያህል ችግሩ ውስጣቸው ሰርስሮ እንደገባ ያሳያል።
ገበያ ሊሸምት የወጣ ሰው ፈገግ ብሎ ማየት ይቅርና ሐሳብ ያናወዘ አእምሮውን ገታ አድርጎ አስፋልት መሻገር ሲቸግረው ለማየት ጊዜ አይወስድም። የኑሮ ውድነቱን በዶላር መጨመር እያመኽኙ አላግባብ የሚበለጽጉ የመኖራቸውን ያህል፣ ምን እንደሚነግዱ አማራጭ አጥተውም የሚንከራተቱ ብዙ ናቸው። ዕቃ እየተወደደባቸው የንግድ ዘርፋቸውን የሚቀይሩ በርካቶች የመኖራቸውን ያህልም፣ ይህን ያህል ጨመረ እያሉ መርዶ በየቀኑ መንገር የሚጨንቃቸው ነጋዴዎችንም ማየት ብርቅ እንደማይሆን ግልፅ ነው። መንግሥት የዋጋ ግሽበት የሚከሰትበት ምክንያት ይጠፋዋል ባይባልም፣ ጭማሪው አላግባብ እንዲፋጠንና መሠረታዊ ፍጆታዎች ላይ ሕዝብን በሚያማርር መልኩ ዋጋ የሚጨምሩትን ሊቆጣጠር እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።
ነጻ ገበያ የታወጀበት ዘመን ላይ ብንሆንም፣ መንግሥት ያላቀረባቸው መሠረታዊ ፍላጎቶች ላይም ሆነ ማንኛውንም ሸቀጥ ተጠቅሞ አላግባብ ለመክበር የሚያስብን ማስተማር ካልተቻለ፣ ለሌላው አስተማሪ የሆነ እርምጃ በመውሰድ ከነድርጊቱ ለሕዝብ ማጋለጥ ያስፈልጋል። ፈረንጆቹ `Naming and shaming` እንደሚሉት በእንዲህ አይነት ተግባር ላይ የተሳተፉትን እያጋለጡ ለማሸማቀቅና ደንበኛ እንዲያጡ ማድረግ ሊጠቅም ይችላል። አላግባብ መበልጸግን ለመቆጣጠር የወጣውን ሕግም ተጠቅሞ አማራጭ አሳጥተው ሕዝብን ለመበዝበዝ የቋመጡትን አደብ ማስያዝ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች።
በተለይ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ከመኖሪያ ቀዬው የተፈናቀለውን ሕብረተሰብ እንደጠላት በሚያስብል መልኩ ገንዘብ የበዘበዙ መኖራቸው ብዙዎችን አንገት ያስደፋ ነበር። የውጭ ዜጋን ጭምር የምታስተናግድ አገር ውስጥ እየኖርን፣ ቤት ንብረቱን ጥሎ በመጣ በገዛ አገር ዜጋ ላይ ይህን መሰል ግፍ ሲፈጸም ማየት፣ ካአፈናቃዮቹ ድርጊት የማይተናነስ እንደሆነ ለመገንዘብ አያዳግትም። የደሴ ከተማ ነጋዴዎች ፈጸሙት ሲባል የተሰማው ነገር ከተማይቱ ከነበራት ስም አኳያ እጅግ አሳፋሪ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ሳይቀሩ ተችተውታል።
በከተማው ውስጥ ያሉ አንዳንድ መደብሮች፣ ሆቴሎች እና ምግብ ቤቶች፣ እንዲሁም ቤት አከራዮች መንግሥት የሌለ እስኪመስል ድረስ ምንም ነገር ሳይጨምርባቸው ተፈናቃይ ስለበዛ ብቻ ዋጋ ሲያንሩ ነበር። አሳዛኝና አሳፋሪ የሆነውን ተግባር ብዙዎች “ልብ የሚሰብር ነው” ብለው ቢተቹትም፣ ምንም ሳይለወጥ መቆየቱ ብዙዎችን አስቆጭቷል።
የሕዝብን መፈናቀልና የወገንን ስቃይ እንደመታደልና እንደልዩ መልካም ድል ያዩት ነጋዴወች፣ አርቆ ባለማሰብ የ150 ብር አልጋ 1000 ብር፣ ከ35 እስከ 50ብር የነበረውን የፆም ምግብ ከ130 ብር በላይ ሲሸጡ ነበር። እንዲሁም 700 መቶ ብር ይከራይ የነበረን ቤት እስከ3500 ብር አስገብተውት እንደነበር በመጥቀስ በእነሱ ድርጊት ማፈራቸውን የዛው ከተማ ነዋሪዎች ጭምር አጋልጠዋል። ከመዝረፍ ምንም አይለይም የተባለለትን ይህን ድርጊታቸውን መክሮም ሆነ ገስጾ ማስቆም ባይቻልም፣ የመቅጣት ሥልጣን ያለው መንግሥት ድርጊቱ ስር እስኪሰድ ዝም ማለት እንዳልነበረበት አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች።
የዋጋ ግሽበቱ ያስከተለው የኑሮ ውድነት ለብዙ ማሕበራዊ ችግሮች እንደሚያጋልጥ እሙን ነው። የሚበላን መጠን በመቀነስ ብዙ ሕፃናት እንዲቀነጭሩ መንስዔ ከመሆኑ ባሻገር ከምግብ ዕጦት ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ በሽታዎች በማጋለጥም ለበርካቶች ሕይወት መጥፋት ምክንያት እንደሚሆን ይታመናል። ማጣቱና ምን ይውጠናል በሚል የቸገረው ብቻ ሳይሆን ስለሌላው የሚያስበውም ለሥነ-ልቦና ዕክል መዳረጉ አይቀሬ ነው። ጦርነቱም ሆነ የኮሮና ወረርሽኙ ካስከተለው ተፅዕኖ በላይ በእያንዳንዱ ቤት ከፍተኛ የሆነ የደህንነት ስጋት ስለሚፈጥር በቀላሉ የማይሽርን ቁስል ፈጥሮ እያመረቀዘ ይቆያል።
የኑሮ መወደድ እየጨመረ ሲመጣ እንደ በፊቱ ሲርበው ቤቱ ዘግቶ የሚሞት ይኖራል ተብሎ ስለማይገመት ለስርዓት አልበኝነት በር ይከፍታል። ዝርፊያና ውንብድናን ከማስፋፋቱ ባሻገር እንዲህ አይነት ተግባሮች ለወደፊት ሁኔታው ቢሻሻልም ልምድ ሆነው ስለሚቀሩ ከባድ መዘዝ ያስከትላሉ። የራበው ለምኖም የሚያበላው ካጣ በረሀብ ከሚሞት በጦርነት መሞትን እንደሚመርጥ ይታወቃል። ይህም የኑሮ ውድነት በኹለቱም ወገን ያለውን ስለሚጎዳ ወደ ጦርነት በመትመም በቀላሉ ጦርነቱ እንዳይቆም ሊያደርግ ይችላል።
የዋጋ ግሽበቱ ያስከተለው የኑሮ መወደድ ሊያመጣው የሚችለው መከራ እየታወቀ የቀልድ ምንጭ የሚያደርጉት ደግሞ በርካቶች ናቸው። ኩንታል ጤፍ 400 ገባ ተብሎ የተቀለደበት ጊዜ አልፎ በአሁን ወቅት ፈገግ የማያሰኝ በሰው ቁስል እንጨት የሚሰነዝር ተግባር እየተስተዋለ ይገኛል። የተወደደን ሽንኩርትና ዘይት በስጦታ መልክ በማቅረብ የተጀመረው አጉል ቀልድ፣ ችግሩን ከማላመድ በዘለለ የሚመለከተው አካልም ሆነ ሕብረተሰቡ እንደቁምነገር አይቶ ዕርምጃ እንዳይወሰድ የማድረግ ኃይሉ ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል።
“ኹሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት” የሚባልበት ዘመን አሁን ተረስቶ፣ ጥቂት ያማረንን ይቅርና ግዴታ የሚያስፈልገንን ለማግኘት የማንችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ገንዘባችን ያለው ዋጋ እያሽቆለቆለ፣ የእኛ ፍላጎትም እያደር እየተሽመደመደ ቢመጣም፣ መሻሻል ሳይታይ ኹሉ ነገር እየባሰበት ይገኛል። የኑሮ መወደድ መዘዙ ከባድ እንደሚሆን መንግሥት ለመረዳት ከጎረቤት ሱዳን ጀምሮ የበርካታ አገራትን የቅርብ ጊዜ ክስተት መመልከት ይገባዋል። “የአበራሽን ጠባሳ እያየ” እኔ ላይ እሳቱ አይደርስም እያለ ዶላርን የሚያሳጣም ሆነ ግሽበቱ እንዲፋጠን የሚያደርግ ግለሰብም ሆነ ተቋም፣ እሳቱ ሰደድ ሆኖ ሲመጣ ማምለጫ እንደማያገኝ ሊገነዘብ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።
ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013



