ማኅበራዊ ሚዲያ ዋነኛ የዜናና የመረጃ ምንጭ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ የቀደሙ የሚዲያ አውታሮች ሲንገዳገዱ፣ አንዳንዶቹ ሙሉ በሙሉ የዲጂታል ሚዲያውን ሲቀላቀሉ እያስተዋልን ነው። በተለይ በሕትመት ሚዲያው ላይ ይህ ነው ተብሎ ለመግለጽ እሰኪያስቸግር ድረስ ፈተናውን በርትቷል።
ከተለመደው የዜና አውታርነት ወጣ በማለት ወደ ዲጂታል መዞር የጀመረው የዜና አዘጋገብ ወይም አቀራረብ ሒደት አሁን ላይ መሠረቱን እጅጉን አጠናክሮ እየቀጠለ ያለ ጉዳይ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ዋል አደር ብሏል። ከምንም በላይ ግን በአገራችን የመደበኛዎቹ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ተዓማኒነትም ላይ የማኅበራዊ ሚዲያው ትልቅ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ በየዕለቱ የምናየው እውነታ ነው።
በዓለም ላይ መረጃ ለማግኘት ብዙ አማራጮች ቢኖሩም አሁን ላይ በወጣቶች ዘንድ ዋነኛ የመረጃ ምንጭ ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኘው የማኅበራዊ ሚዲያ እንደሆነ የሚገልጸው መቀመጫውን በብሪታኒያ ያደረገው እና በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት የሠራው yougov survey የተባለው የጋዜጠኝነት ምርምር ተቋም ነው።
የአገራችን ወጣቶች ምክንያታቸው ይለያይ ይሆናል እንጂ የማኅበራዊ ሚዲያን የመረጃ ምንጭ ማድረጋቸው ከጥናቱ የተለየ ይሆናል ተብሎ አይታሰብም።
መላኩ አለማየሁ ይባላል። በሃያዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኝ ወጣት ነው። የማኅበራዊ ሚዲያን መጠቀም የጀመረው የኹለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለ መሆኑን ይናገራል። በመጀመሪያ ላይ የማኅበራዊ ሚዲያ የሚጠቀምበት ዓላማ ከሰዎች ጋር ለመገናኘት እና ለማውራት እንደነበር የሚያስታውስ ሲሆን፣ አሁን ላይ ግን ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች የሚገባው መረጃ ለማግኘት እንደሆነ ይናገራል። “ማኅበራዊ ሚዲያ ከየትኛውም ሚዲያ በፈጠነ መልኩ መረጃውን ስለሚሰጠኝ እመርጠዋለሁ” ይላል። ዋና ዋና የሚባሉት የመገናኛ ብዙኃን በማኅበራዊ ሚዲያ ተወርቶ ካለቀና ሌላ ርዕሰ ጉዳይ ከተጀመረ በኋላ እንደ አዲስ ስለሚዘግቡት ማኅበራዊ ሚዲያን ምርጫው እንዲሆን ማድረጉን ይገልጻል።
ከመታመን አንጻር ግን ማኅበራዊ ሚዲያው ሠፊ ክፍተት እንዳለበት የሚያነሳው መላኩ፣ የሚያነሱትን ጉዳዮች በማረጋገጥም ሆነ በማስተባበል ረገድ የመደበኛ ሚዲያዎች በጣም የዘገየ ሥራ ስለሚሠሩ የማኅበራዊ ሚዲያዎችን የመረጃ ምንጭ አድረጎ መጠቀም መቀጠሉን ያነሳል። በመገናኛ ብዙኃን የሚነሱ ርዕሰ ጉዳዮች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቀድመው የሚነሱ በመሆናቸው እንደአዲስ ለማየት ሆነ ለመስማት የማይጋብዙ በመሆናቸው ትኩረት ለመስጠት እንደሚቸገር ያነሳል።
መደበኛ ሚዲያው መረጃን በፍጥነት እና በሚፈለገው መጠን ወደ ሕብረተሰቡ ማድረስ እንዳልቻለ በሠፊው የሚተችበት ጉዳዮ ነው።
አሁን ላይ በዓለም ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከአንድ የሚዲያ መንገድ ወደ ሌላ እየተዘዋወርን ነው ያለነው የሚሉት ደግሞ ጋዜጠኛ ደመቀ ከበደ ናቸው። በፊት ላይ ኅትመት ሠፊውን የመረጃ አቅራቢነት ቦታውን ይዞ የቆየ ቢሆንም፣ ከኅትመት ወደ ሬዲዮ ከዛም ወደ ቴሊቪዥን አሁን ላይ ደግሞ የኢንተርኔት አግልግሎት መስፋፋትን ተከትሎ የዲጂታል ሚዲያ ዘመን ላይ ደርሰናል።
ይህ የዲጂታል ሚዲያ እንደ ሬዲዮ የምንሰማው፣ እንደ ቴሌቪዥን የምንመለከተው እና እንደ ጋዜጣ የምናነበው ነገር በአንድ ላይ ይዞ በመምጣቱ ትልቅ እድል ለማኅበረሰቡ ይዞ መጥቷል ሲሉ ያብራራሉ።
በእነዚህና በሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች የማኅበራዊ ሚዲያው በመደበኛ ሚዲያው ላይ መረጃ በፍጥነት ተደራሽ በማድረግ ረገድ ትልቅ ዕድል ሰጥቶታል። በተከታዮችም በኩል መረጃን በፍጥነት ተደራሽ ከመሆን አንጻር ዲጂታል ሚዲያው ተመራጭ እየሆነ ይገኛል።
ማንኛውም ግለሰብ መረጃ አለኝ ብሎ በሚያስበው ጉዳይ ላይ እንዳሻው ማጋራት የሚችልበት ሁኔታ ስላለ በኤዲቶሪያል ከሚመራው የመደበኛ ሚዲያ የተሻለ ነጻነት አለው ይላሉ ጋዜጠኛ ደመቀ ከበደ።
ይህ የግለሰቦች ሐሳባቸውን በነጻነት መግለጽ ያስቻለ ዘርፍ በመሆኑ መረጃን ለሚፈልጉ ሰዎች ከመደበኛው ሚዲያ በተሻለ ፍጥነት ማድረስ አስችሏል። ከዚህም በተጨማሪም የሰውን ትኩረት ሊስቡ የሚችሉና የሰውን የመረጃ ፍላጎት መሰረት ያደረጉ መረጃዎችን ሰዎች አንዲያቀርቡ ሠፊ እድል ሰጥቷቸዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ ክንዱን እያበረታ እንዳለ የሚስተዋለው የዲጂታል ሚዲያው አንዳንድ ሚዲያዎችን ማንገዳገዱ እየታየ ነው። ሆኖም የተንገዳገዱትም ቢሆኑ የዲጂታል ሚዲያውን እንደ አንድ የመረጃ ማሠራጫ መንገድ አየተጠቀሙበት ባለመሆናቸው ነው ይላሉ ጋዜጠኛ ደመቀ።
“በአጠቃለይ መደበኛ የሚባሉ ሚዲያ ዘርፎች እየተንገዳገዱም ሆነ እየወደቁ ያሉት በዲጂታል በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያው ጫና ብቻ አይደለም። ማኅበራዊ ሚዲያው አንዱ ምክንያት እንጂ ብቸኛው እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል” በማለት አጽንዖት ይሰጣሉ።
በዋነኝነት መረጃ ከማቀበል አንጻር መደበኛ ሚዲያው በዲጂታል ሚዲያው ለመበለጡ ዋነኛ ምክንያት ይዘውት ከሚመጡት ይዘት አንጻር ነው ይላሉ። ከይዘት በኩል ደካማ አቀራረብ ይዞ የመጣ ማንኛውም ሚዲያ ካለው ተገዳዳሪ እኩል ለመራመድ ባለመቻሉ ከጨዋታ ውጪ ከመሆን ሊድን አይችልም ሲሉም ያክላሉ።
መደበኛ ሚዲያዎች የቴክኖሎጂም ሆነ የሰው ኃይል ከመኖር ጋር በተያያዘ ምቹ ዕድል ያላቸው ቢሆኑም፣ ሰበር ዜናም ሆነ ኹነቶች በቦታው ተገኝቶ የመሥራት አቅሙ ቢኖራቸውም ማኅበራዊ ሚዲያውን ከመገዳደር አንጻር ግን ትልቅ እክል አለባቸው። ለዚህም ለማስረጃነት የሚቀርበው መደበኛ ሚዲያዎች በመላው አገሪቱ የሚከሰቱ ኹነቶችን በቀጥታ ሥርጭት ለማስተላለፍ ፍላጎት ቢኖራቸው እንኳን ለሥርጭት የሚያወጡት ወጪ ቀላል የሚባል አይደለም። ምክንያቱም ለቀጥታ ሥርጭት የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች ከፍ ያለ የገንዘብ አቅምን የሚጠይቁ ከመሆኑ በላይ፣ ሙሉ በሙሉ ለመሸፈን የሚጠይቀውን የሰው ኃይል ማሟላት ትልቅ እክል እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ነገር ግን በአሁን ሰዓት ኹሉም ግለሰብ በእጁ በሚገኙ ዘመን በወለዳቸው ተንቀሳቃሽ ስልኮች በመጠቀም ከያለበት መረጃን ማቅረብ በመቻሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የመደበኛው ሚዲያ ተገዳዳሪ ሆነው ሰውን ወደ ራሳቸው ለመሳብ አስችሏቸዋል።
“መደበኛ ሚዲያዎች በተመረጠ ቦታ ላይ ብቻ ሆነው ነው ዘገባቸውን የሚሠሩት” የሚሉት በዘርፉ ላይ ያሉት ደመቀ፣ ይህ ኹኔታ በዲጂታል ሚዲያው ላይ ተፎካክረው በፍጥነት መረጃን ለሕዝብ በማድረሳቸው ሒደት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አለው ይላሉ። ከመደበኛ ሚዲያው ውጪ ያሉት ግን የትኛውም ቦታ ላይ ሆነው፣ ርቀት ሳይገድባቸው መረጃዎችን ቦታው ላይ በመገኘት በስፋት ለታዲሚያቸው ማቅረብ መቻላቸው የመረጃ ምንጭ ሁነው መቅረብ ለመቻላቸው ምቹ መደላድል ፈጥሯ ሲሉም ያስረዳሉ።
አሁን ላይ ቴሌቪዥን ወይም ሬዲዮ ላይ የዜና ሰዓት ጠብቄ የምከታተልበት ምንም ምክንያት የለኝም የሚለው ደግሞ በረከት ሰለሞን የተባለ አስተያት ሰጪ ነው። “ዘመኑ ባመጣልኝ የቴክኖሎጂ መንገድ ተጠቅሜ መረጃዎችን ማግኘት እየቻልኩ፣ ለምን የተለመዱትን የዜና ምንጮች መጠበቅ አስፈለገኝ?” ሲልም ጥያቄውን ያነሳል። ከተአማኒነት አንጻር በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ሠፊ ችግር ያለ ቢሆንም፣ ከተለያየ ምንጮች እያመሳከረ እውነታውን ለመረዳት እንደሚጥርም ያክላል። መረጃን በፍጥነት ከማግኘት አንጻር የዲጂታል ሚዲያው ትልቅ ግልጋሎት እየሰጠ መሆኑንም ይጠቅሳል።
የዲጂታል ሚዲያው የአብዛኛውን ሰው ትኩረት ለመሳብ ያስቻለው፣ ትልቁን ቁጥር ይዘው በሜዳው ላይ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት በዕድሜያቸው ወጣት የሚባሉት በመሆናቸው ነው። አብዛኛው የዲጂታል ሚዲያው ተጠቃሚ ወጣቱ ትውልድ ከመሆኑ አንጻር መረጃን በፍጥነት ካንዱ ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ ለመዘወር ቀላል እንዳደረገው ይታመናል።
“ትልቁ መታየት ያለበት ጉዳይ የትውልዱ ጉዳይ ነው። አሁን ያለው ትውልድ ባብዛኛው ወጣት በመሆኑ በስፋት የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ነው። ይህ ደግሞ ቴክኖሎጂን በመጠቀም መረጃን የማግኘት ዕድሉን ሠፊ ያደርገዋል። በዚህም ምክንያት መደበኛውን የሚዲያ መንገድ ሳይከተሉ መረጃን ለማግኘት ተመራጭ ያደርጓቸዋል” ሲሉ ጋዜጠኛ ደመቀ ከበደ ይገልጻሉ።
በመደበኛው ሚዲያ በኩል ከመረጃ አቅርቦት ፍሰት ችግር አንጻር ያለውን ክፍተት በተመለከተ ባለሙያው ሲያስረዱ፣ “ጥራት ያለው መረጃ ለመስጠት የሚያስችል የመረጃ አቅርቦት ከፍተት አለ። በብዛት፣ በጥራት እና በፍጥነት መወዳደር እንዳይችሉ ወይም ተፎካካሪ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል” ብለው በመደበኛው ሚዲያ ዘርፍ በኩል ያለባቸውን ተግዳሮቶች ያስረዳሉ።
ከዚህም በተጨማሪ የማኅበራዊ ሚዲያው መደበኛ ሚዲያውን እየበለጠ ካለበት ምክንያቶች አንዱ ብለው የሚያነሱት፣ የመንግሥትም ሆነ የግል መደበኛ ሚዲያዎች በንግድ ላይ የተመሠረተ አልያም በመንግሥት ድጋፍ ላይ የቆመ እንቅስቃሴ ስለሚያደርጉ ድጋፍ ወደሚገኝበት እየተከተሉ የመዘገብ እና ለነሱ የሚስማማ ነገር የመዘገብ ግፊት አለባቸው። በዚህም ምክንያት የዲጂታል ሚዲያው መረጃ በፍጥነት ከማቅረብ አንጻር መደበኛው ሚዲያን እየተገዳዳረው በአብዛኛውም አልፎት ሲሄድ እየተመለከትን እንደሆነ ያነሳሉ።
በአንዳንድ ባለሙያዎች በኩል አጀንዳን ከመስጠት ረገድ መሆን የሚገባው ከመደበኛው ወደ ማኅበራዊው ሚዲያው መሆን አለበት ብለው ሐሳብ የሚሰጡ አሉ። ሆኖም አሁን በአገራችን እያየነው ያለነው በተገላቢጦሽ ከማኅበራዊ ሚዲያው ወደ መደበኛ መሆኑ ትክክል አለመሆኑን በማንሳት ሐሳብ ይሰጣሉ።
እንደ ጋዜጠኛ ደመቀ ከበደ አስተያት ከሆነ አጀንዳ ከመፍጠር አንጻር በኹለቱም በኩል ጥንካሬም ድክመትም አለባቸው በማለት ሐሳባቸውን ያነሳሉ። በዚህ ረገድ ኹለቱም ዘርፎች የራሳቸውን ጥረት በማድረግ ላይ ቢሆኑም፣ አንዱ ከሌላኛው የተሻለ አጀንዳ ይፈጥራል ብሎ ለመደምደም እንደሚቸገሩ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ አጋርተዋል።
በዲጂታል ሚዲያው በኩል የማኅበራዊ ገጾች በስፋት ከሚስተዋልባቸው ዋነኛ ችግር መካከል የመረጃው ተዓማኒነት ዋነኛው እንደሆነ መናገር ለቀባሪው ማርዳት ነው የሚሆነው። በዚህም ምክንያት በነሱ በኩል የሚተላለፉ መረጃዎች ሀሰተኛ ሆነው ሲገኙ መረጃዎችን ከማጥራት አንጻር ትልቅ ክፍተት ይታይባቸዋል ይላሉ ደመቀ ከበደ። ይህ ጉዳይ ግን በመደበኛው የሚዲያ ተቋማትም ላይ የሚታይ ጉዳይ በመሆኑ ኹለቱም የሚጋሩት ክፍተት እንደሆነም ጨምረው ያነሳሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚለቀቁ ሀሰተኛ መረጃዎችን ለማጣራትና ለሕብረተሰቡ ለማሳወቅ የተወሰኑ ግለሰቦች እና ተቋማት ብቅ ብቅ እያሉ ቢሆንም፣ በነሱ ብቻ ጥረት የሚሣካ ጉዳይ አይደለም። በመሆኑም ኹሉም ያገባኛል የሚል ሰው ጉዳዩን በትኩረት ሊያየው የሚገባ አንገብጋቢ ነገር መሆኑ ነጋሪ አያሻም። ከዚህም በላይ ግን መደበኛ ሚዲያዎች በማኅበራዊ ሚዲያው የተጋረጠባቸውን የመረጃ ፍሰት ችግርና የሕልወና ስጋት ለመፍታት ያላቸውን ዓቅም አሟጠው መጠቀም ግድ የሚልበት ሰዓት ላይ ይገኛሉ።
ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013



