በአዲስ አበባ የራስ ምታት የሆነው የቤት ኪራይ የዋጋ ንረት

0
1802

በመዲናችን አዲስ አበባ በየወቅቱ የሚጨምረው የቤት ኪራይ የዋጋ ንረት ማኅበረሰቡን እያማረረና ኪሱን እያራቆተ ይገኛል። የኪራዩ መጠን አብዛኛው ማኅበረሰብ ከሚያገኘው ወርሃዊ ገቢ የማይተናነስ ነው። ዕውነታው ይታወቅ ከተባለ በአዲስ አበባ የኑሮ ውድነት የራስ ምታት እንዲሆን ከሚያድረጉት ምክንያቶች የመጀመሪያውን ደረጃ የሚዘው የቤት ኪራይ የዋጋ ንረት መሆኑን ማንም ሰው ሳያቅመቅማማ ይስማማበታል።
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለምግብና ለልብስ ከሚወጣው ወጪ ይልቅ ለቤት ኪራይ የሚወጣው ሚዛን የሚደፋ እየሆነ መጥቷል።

በእርግጥ በዚች ምድር ላይ በቋሚነት ሊዘልቁ የሚችሉ ዋጋዎች ሊኖሩ አይችሉም። ኹሉም ነገሮች በቋሚነት ይቀጥላሉ ብሎ መደምደም እንደማይቻል የማንም ሕሊና ያለምንም ክርክር ይስማማበታል።
በመዲናችን አዲስ አበባ ከትራንስፖርት ባሻገር ስለ ቤት ኪራይ ሲነሳ ጉዳዩ እንደ ወባ ሕመም የሚያንገሸግሻቸው ሰዎች በርካቶች ናቸው።

በኪራይ የሚኖሩ አብዛኞቹ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከፍ ያለውን ገቢያቸውን ቅድሚያ የሚነጥቃቸው የቤት ኪራይ መሆኑን አበክረው ሲናገሩ ይደመጣሉ። በኪራይ ቤት ለሚኖሩ ዜጎች የቤት ኪራይና የትራንስፖርት ወጪ የአንድ ሳንቲም ኹለት ገጽታዎች ሆነው በመተባበር የሚደቁሷቸው ማነቆዎች ናቸው። ሆኖም ግን የኑሮ ውድነት ሲነሳ ማኅበረሰቡ ቀድሞ የሚማረረው በቤት ኪራይ ጉዳይ ነው።

የተሻለ የኪራይ ዋጋ ያላቸው ቦታዎች አገኘን ብለው የከተማዋን ጫፍ መርጠው በመከራየት ደስታቸውን አጣጥመው ሳይጨርሱ፣ ዕለት በእለት ለትራንስፖርት የሚያወጡት ወጭ ከቤት ኪራይ ትርፍ ትሆናለች ተብላ የታሰበችውን ብር ከኋላ በመከተል ቅርጥፍ አድርጎ በልቷት ይገኛሉ።

አሁን አሁን የአዲስ አበባን ኑሮ አጣጥሞ ለመኖር የመኪናና የቤት ባለቤት መሆን ከፍተኛውን ድርሻ እየያዘ መጥቷል። ኹለቱ ቁሶች ያሉት ሰው በልኩ ለመኖር ካሰበ የተጋነነ ገቢ ላያሻው ይችላል። ቤትና መኪና ካለው ከፍተኛ ወጪን በመቀነስ ለመኖር አቀበት የሚሆነውን አስቤዛ ማሟላት ስለሚችል ቀሪዎቹን ባለው ትንሽ የገቢ ምንጭ መሸፈን ይችላልና ነው።

ይሁን እንጅ በአዲስ አበባ ከተማ ይህ አይነት ዕድል በጥቂቶች ዘንድ ቢኖርም፣ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ይህን መሰሉ ዕድል እንደ ሰማይ የራቀባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ናቸው።
በዚህ ወቅት በመዲናችን አዲስ አበባ የሚገኙ ዜጎች፣ በተለይም በመንግሥትና በግለሰበቦች ስር ቅጥረኞች ሆነው በቤት ኪራይ ሕይወት የሚኖሩት ሠራተኞች፣ ለመደምደም በሚያስደፍር መልኩ የገቢና የወጪ ፍሰታቸው አለመመጣጠኑ ይስተዋላል።
የወር ደሞዝተኞችና የቀን ሠራተኞች ከሚያስገቡት ገቢ ይልቅ የሚያወጡት ወጭ ከፍተኛ ነው። ለዚህ የገቢና ወጭ መዛነፍ ዋና መንስኤ ለቤት ኪራይ የሚወጣው ብር መሆኑ አያጠራጥርም።

በዚህ ችግር ሰለባ የሆኑ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለአብነት ተጠቃሽ ናቸው። የሆነው ሆነና የቤት ኪራይ የዋጋ ንረት እንደ እሬት መሯቸው የአጣብቂኝ ሕይወትን በመምራት የሚኳትኑ ዜጎችን መመልከት እየተለመደ የመጣ ጉዳይ ሆኗል።
በአዲስ አበባ ከተማ ለሚስተዋለው የኑሮ ውድነት መንስኤ ነው ለሚባለው የቤት ኪራይ የዋጋ ንረት መከሰት እንደ ምክንያት ሆነው የሚመዘዙ የተለያዩ ችግሮች አይጠፉም። ከእነዚህም መካከል የሚከተሉትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።
የከተማዋን ማደግ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ማለትም የተለያየ የሥራ ዕድል ይኖራል ተብሎ ስለሚታሰብ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ዜጎች ቁጥራቸው በየዕለቱ መጨመሩ አንዱ ነው።

በከተማው የሚኖሩ አብዛኞቹ አከራዮች ኪራይን እንደ ዋና የገቢ ምንጭ በመጠቀማቸው፣ ወጪያቸው በኑሮ መወደድ ምክንያት በጨመረባቸው ቁጥር ገቢያቸውን ከፍ ለማድረግ በመገደዳቸው የሚያደርጉት ወቅቱን ያልጠበቀ የኪራይ የዋጋ ጭማሪም ሌላኛው ምክንያት ነው።
ሶስተኛው ምክንያት ደግሞ የዶላር ምንዛሬ ጨመረ በማለት ባለቤቶች በፈለጉት ዋጋ የማከራየት ነጻነታቸውን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ቤት የሚያከራዩበትን ዋጋ ከመጠን በማሳለፋቸው እንደሆነ ይነገራል።

በከተማው የሚኖሩት አብዛኛዎቹ ዜጎች ከተለያየ የአገሪቱ አካባቢዎች የተሰባሰቡ በመሆናቸው ለመኖር ሲሉ ያላቸው አማራጭ ግዴታ አከራዮች በሚጠሩት የኪራይ መጠን መከራየታቸው ለቤት ኪራይ የዋጋ መናር አይነተኛ ምክንያት ሆኖ ይስተዋላል።
አዲስ አበባ ውስጥ የራሱ ቤት ያለው ሰው ያገኘውን ሠርቶ ባልተጋነነ ሁኔታ ፍላጎቱን አሟልቶ መኖር ይችላል።

በከተማዋ በግል ንግድ ከሚከንቀሳቀሱ አንዳንድ ወፍራም ገቢ ካላቸው ባለሀብቶች በተቃራኒ የሚገኙ፣ በተለይም በግልም ሆነ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞችና በቀን ሥራ የሚተዳደሩ ዜጎች ከእጅ ወደ አፍ የዘለለ ገቢ እንደማይኖራቸውም ይታወቃል።
በመሆኑም ለቤት ኪራይ ከሚያወጡት ብር ለመዳን የራሳቸውን ቤት መገንባት ግድ ቢላቸውም፣ ያላቸው ገቢ ይህን ለማድረግ አይፈቅድላቸውም።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት ከኪራይ ቤት ኗሪዎች ጋር ቆይታ አድርጋለች። ቤተልሄም ፍቃዱ ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው ጎጃም ሲሆን፣ ወደ አዲስ አበባ ከተማ መጥታ ተከራይታ በመኖር አስረኛ ዓመቷን አክብራለች።
ቤተልሄም ባሳለፈችው የልጅነት ዘመኗ የትምህርት ገበታዋን ሰንሠለቱን በጠበቀ መልኩ በመከታል እስከ 12ኛ ክፍል ብትማርም፣ የ12ኛ ክፍል ፈተና ግን ወደ ቀጣዩ የትምህርት ደረጃ እንድትቀላቀል ሊፈቅድላት አልቻለም።

ቤተልሄም ፍቃዱ በግብርና ዘርፍ ከሚተዳደሩ ቤተሰቦች የበኩር ልጅ በመሆኗ፣ ቤተሰቦቿ ከእርሷ አከታትለው የወለዷቸውን ልጆች የሚያሳደጉበት የእፎይታ ጊዜን ለመስጠት እንዲሁም የራሷን ሕይወት ለመመስረትና ቤተሰቦቿን ለማገዝ ስትል ነበር ወደ አዲስ አበባ ከተማ ያቀናችው።

ወደ ከተማው ከማቅናቷ በፊት ኹሉም ነገሮች አልጋ ባልጋ ባይሆኑላትም የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራትና ጎን ለጎንም ትምህርቷን በመከታተል በልቧ ውስጥ የታተመ ዓላማዋን እውን ለማድረግ መትጋት ሌላኛው የጉዞዋ ምክንያት ነበር። ነገር ግን፣ አዲስ አበባ ያለው የኑሮ ውድነት ነገሮችን ኹሉ እንዳሰበችው ሊያደርግላት አልቻለም።

ቤተልሄም እንግዲህ በዚህ ወቅት ነው የአዲስ አበባን የቤት ኪራይ ኑሮ ’ሀ’ ብላ የጀመረችው። ለመጀመሪያ ጊዜ የተከራየችውን ቤት ያገኘችው በደላሎች አማካኝነት ሲሆን ቤቱ ከከተማው ወጣ ያለ በመሆኑ የተሻለ ዋጋ ተበሎ 1500 ብር ነበር የምትከፍለው።
የቤት ኪራዩን ብር ቅድሚያ መክፈል እንዳለባት ተነግሯት በውሉ መሰረት የከፈለች ሲሆን፣ የመጣችበትን ዓላማ ለማሳካት ሥራ ለማፈላለግ ብትሞክርም በቀላሉ ማግኘት ግን አልቻለችም። ሥራ ለማኘግት ዉሎዋን በዙረት የምትጀምረው ቤተልሄም አንድ ቀን ዕድል ገጥሟት ለጽዳት ሠራተኝነት ወደጠራት መሥሪያ ቤት ጎራ አለችና ስለደሞዟ ጉዳይ ስትጠይቅ ከ2ሺሕ ብር የዘለለ እንደማይከፈላት ተገለጸላት።

ሌላ የሥራ ዕድል እንደማታገኝ የአዲስ አበባ ቆይታዋ በተግባር ያስተማራት ቤተልሄም ፈቃዱ፣ የሚከፈላት ደሞዝ ከቤት ኪራይና ከትራንስፖርት እንደማይዘል ቢገባትም ከመቀመጥ ይልቅ የተገኘውን መሥራቱ የተሻለ መሆኑን በመገንዘብ ተስማምታ ሥራዋን ጀመረች።
አሁን ነገሮች ተቀይረዋል፤ ቤተልሄም በጧት ተነስታ በማታ ነው ወደ ቤቷ የምትገባው። በእንደዚህ ኹኔታ የሚመሹትና የሚነጉት ቀናት ገቢዋን ከቀለብ፣ዕቃና ትራንስፖርት ጋር ተባብረው እያዳክሙባት መጥተዋል።
ወሩን ጠብቆ የሚመጣው የቤት ኪራይ እየተቃረበ ነው። ከመኖሪያ ቤቷ ርቀት ጋርና ከታክሲ መወደድ ጋር ተያይዞ ለትራንስፖርት የምታወጣው ወጭ ስታነጻጽረው ለቤት ኪራይ ከምታወጣው ወጭ አልተናነሰም።

በእንደዚህ አይነት ሕይወት ኹለት ዓመትን ብታስቆጥርም ሠርቶ ለቤት ኪራይና ለትራንስፖርት ከማስረከብ በዘለለ ያነገበችውን ዓላማ የሚያሟላ ገቢ ማግኘት አልቻለችም። በተለይም ትምህርቷን መከታተል አለመቻሏና ቤተሰቦቿን ካለማገዟ በበለጠ የራሷን ሕይወት እንኳን በውል አለመምራቷ ያበሳጫታል።

ቢሆንም ግን አሁንም የተሟላ ባይሆንም ካለችበት የተሻለ ኑሮን ለመኖር የሚያስችል ሥራን ለመሥራት ማቀዷን አላቆመችም። የሥራ ቦታዋን ለቃ ሌላ ቦታ በመቀጠር ተመሳሳይ ሥራዎችን ሠርታለች። አሁን ግን መቀጠር በቃኝ ብላ በሊስትሮ ሥራ ተሠማርታ ትገኛለች።
ሆኖም ግን የተሻለ ገቢ ቢኖራትም የቤት ኪራይ የዋጋ መናር ከእጅ ወደ አፍ አይነቱን ኑሮ ፈቀቅ እንዳላደረገላት ነው ተናገረችው። ’’በአዲስ አበባ ከተማ ለመኖር የቤት ኪራይ የዋጋ ንረት አፋጣኝ መልስ ያሻዋል፤ ካልሆነ ግን የኑሮው ሒደት በድካም የሚገኘውን ገቢ ለአከራዮች እያስረከቡ መኖር ነው’’ ትላለች።

ቤተልሄም በመጨረሻም የቤት ኪራይ ዋጋ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ከቀጠለ ሕይወትን መምራት አቀበት ይሆናልና በመጀመሪያ ቤት አከራዮች መደጋገፍ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ መሆኑን ከእንደገና መለስ ብለው ቢያስቡና አስተያየት ቢያደርጉ ለኹላችንም መልካም ነው ትላለች።
በኹለተኛ ደረጃ ደግሞ መንግሥት በኪራይ ቤት የሚኖሩ ብዙ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች እንዳሉ በማሰብ መፍትሄ ሊሰጥበት ይገባል በማለት ነው ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራት ቆይታ ሐሳቧን የገለጸችው።
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ባለሥልጣናትም የ2014 የበጀት ዓመትን አስመልክቶ ሐምሌ 21/2013 ዓ.ም. ባደረጉት ስብሰባ ቤቶችን ለመገንባት ዕቅድ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ በሒደት ላይ የሚገኘው የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን፣ በ2014 የበጀት ዓመት ከተያዘው የቤት ግንባት ዕቅድ ውስጥ ለኪራይ የሚገነቡ 9ሺ ሦስት መቶ ሰላሳ ቤቶች መኖራቸውን ገልጿል።


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here