የቆመ መኪና በተመሳሳይ ቁልፍ በማስነሳት ሰርቆ የወሰደዉ ወንጀለኛ በስድስት ዓመት ፅኑ እስራት መቀጣቱን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቀ።
ወንጀሉ የተፈፀመዉ እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ቦታዉ ጀሞ 02 አካባቢ ሲሆን ድርጊቱን የፈፀመዉ በረከት ተስፋዬ የተባለ የ21 አመት እድሜ ያለዉ ተከሳሽ ነዉ ፡፡
ተከሳሹ በቀን 8/12/2013 ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት ሲሆን ንብረትነቱ በግል ተበዳይ መዝገቡ ሹሜ የተመዘገበዉን እና ደንበሩ ሹሜ በዉክልና የሚያስተዳድሩትን የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 1-17391 አ.አ ቶዬታ አይሲ ኮሮላ፤ የዋጋ ግምቱ 300.000 ሶስት መቶ ሺ ብር የሆነዉን መኪና ከቆመበት ቦታ በተመሳሳይ ቁልፍ በማስነሳት ነው ሰርቆ የወሰደው።
ተከሳሹ የወሰደውን መኪና እያሽከረከረ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ልዩ ቦታዉ ጀሞ 03 አደባባይ ሲደርስ መኪናዉ ተገልብጦ በመቆሙ ምክንያት የተያዘ ሲሆን ተከሳሽ የወንጀል ህግ አንቀፅ 669/3/ለ ላይ የተደነገገዉን ድንጋጌ ተላልፎ በፈፀመዉ የከባድ ስርቆት ወንጀልም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶበታል፡፡
ተከሳሽ ጉዳዩን ስለመፈፀሙ ፍርድ ቤት ቀርቦ የእምነት ቃሉን ሲጠየቅ ወንጀሉን መፈፀሙን ያመነ ሲሆን፤ ወደቤቴ ለመሄድ ሳስብ ስለመሸብኝ ባለቤቱን ሳላስፈቅድ መኪናዉን ይዤዉ እየሄድኩ ሳለ መንገድ ላይ ተገልብጦብኛል በዚህም ጥፋተኛ ነኝ ሲል ወንጀሉን መፈፀሙን አምኗ ቃሉን ሰጥቷል፡፡
መዝገቡን የተመለከተዉ የፌዴራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምደብ ወንጀል ችሎት ተከሳሽ ጥፋተኛ ነዉ ሲል የቅጣት ዉሳኔዉን ያስተላለፈ ሲሆን ተከሳሹ ወንጀሉን ማመኑ፣ እድሜዉ ዝቅተኛ መሆኑንና ከዚህ በፊት የነበረዉን መልካም ባህሪ ለቅጣት ማቅለያነት በመያዝ በቀን 4/13/2013 በዋለዉ ችሎት ሌሎችን የህብረተሰብ ክፍሎች ያስተምራል ያለዉን በስድስት አመት ፅኑ እስራት ይቀጣ ሲል ወስኖበታል፡፡



