መጻሕፍት – ከብረት አጥሮቹ መካከል

Views: 91

ለአንድ ዓመት ያህል በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በእስር ቆይቶ በነጻ የተፈታው ፍቅሩ አማረ (ስሙ የተቀየረ) ከመታሰሩ በፊትም ሆነ በኋላ ከንባብ የለያየው አልነበረም። ይልቁንም በእስር ቆይታው ቤተዘመዱ ጥየቃ ሲሔድ መጻሕፍት ሲወስድለት ደስተኛ ይሆን ነበር። መጻሕፍት ለእርሱ ጓደኞቹ ስለሆኑ።
ታድያ በማረሚያ ቤቱ ቤተ መጻሕፍት መኖሩን፣ መጻሕፍት ሲመጡለት ግን በቶሎ እንደማይገባና ተፈትሾ እና ታይቶ እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ አጫውቷታል።
በማረሚያ ወይም እስር ቤቶች የሚገኙ ሰዎች አንዳንዴ ራሳቸውንና የሕይወት ጥሪያቸውን በማረሚያ ቤት የሚያገኙበት አጋጣሚ አለ። ይህን የጠቀሰው ፍቅሩ፤ በዚህና በሌሎችም ጥቅሞቹ በማረሚያ ቤቶች መጻሕፍት የመገኘታቸውን ጥቅም አጥብቆ ይናገራል።
እንደ ፍቅሩ ያሉ የማንበብ ፍላጎት ያላቸውና በተለያየ ምክንያት በማረሚያ ቤት የሚገኙ ሰዎች በእርግጥ የመጻሕፍት አገልግሎት ያስፈልጋቸዋል። ወዲህ ደግሞ ትምህርት ቤቶችና በወጣት ማእከላት በሚገባ በበቂ ሁኔታ ያልተሟላው የቤተ መጻሕፍት ነገር፣ ለማረሚያ ቤቶች ለማሟላት ማሰብ ቅንጦት ሊመስል ይችላል፤ ግን አይደለም።
እንደውም ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩ ወጣቶች ተፈጥረዋል። ሰላማዊት በለጠ ደግሞ ከእነዚህ ወጣቶች መካከል በግንባር ቀደምነት ትጠቀሳለች። ሰላማዊት በ2010 መጨረሻ ላይ ነበር ለማረሚያ ቤቶች የመጻሕፍት ማሰባሰብ ሥራን የጀመረችው። አሁንም የዚሁ በጎ ተግባር ዋና አስተባባሪ በመሆን እያገለገለች ነው።
ነገሩ እንዲህ ነው፤ የገጣሚ ደበበ ሰይፉ ወንድም መኮንን ሰይፉ በእጁ ከነበሩት በርካታ መጻሕፍት የተወሰኑትን የሚሰጥበት ቦታ ይፈልግ ነበር። እናም ‹‹ለማረሚያ ቤት ብንሰጥስ›› ሲል ሐሳቡን ለጋዜጠኛ ሙሉጌታ አንበርብር ያቀብላል። ሙሉጌታም ጉዳዩን ለሰላማዊት ያጫውታትና እርሷ ከአዲስ አበባ፣ ሙሉጌታም በነበረበት ከሐዋሳ እያንዳንዳቸው ተጨማሪ 500 መጻሕፍትን አሀዱ ብለው ሰበሰቡ።
‹ንባብ ለሕይወት› ዓመታዊ የመጻሕፍት አውደ ርዕይና ሽያጭ መድረክ ላይ ኤፍሬም ጀማል አብዱን አገኙት፣ ቡድኑን ተቀላቀለ። እነዚህ ሦስት ወጣቶች መጻሕፍቱን ሰባስበው ለሐዋሳ ማረሚያ ቤት እንዲሁም ለጅማ ዞን ማረሚያ ቤት አስረከቡ።
ቀጠሉ፤ የመጀመሪያ መድረክ ተዘጋጀ። ከዐስር በላይ አንጋፋና ወጣት የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ይዘው ያዘጋጁት ይህ መድረክ መግቢያው ኹለት መጻሕፍት ነበር። በዚህም መሠረት 1550 መጻሕፍትን መሰብሰብ ችለዋል። ይህንንም ለባሕርዳር እና ፍኖተ ሰላም ማረሚያ ቤቶች እኩል አካፈሉ።
ከዚህ በኋላ ነው ሦስት ሆነው መሥራታቸው ቀርቶ፣ ሥራውን ሰላማዊት ለብቻዋ የተረከበችው። በዚህም ግንቦት 27/ 2011 አንድ መድረክ አዘጋጀች። በዚህም ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ ብቻውን 1000 መጻሕፍት ያበረከተ ሲሆን፣ የሌሎችም ተጨምሮ የተሰበሰቡት ከ2600 በላይ መጻሕፍት፣ ደብረብርሃን እና አሶሳ ማረሚያ ቤቶች ተከፋፈሉት።
ሰላማዊት ከመጻሕፍትና ንባብ ጋር በልጅነት ነው የተዋወቀችው፤ ‹‹ያኔ አሁን ከማነበው በላይ አንብቤአለሁ›› ትላለች። ደራሲ አሸናፊ መለሰ አማራኛ መምህሯ መሆኑ ንባብን እንድታጸና ረድቷታል። አሁን ታድያ ቀን ከመደበኛ ሥራዋ ስትመለስ፣ ማምሻውን ከ11 ሰዓት ጀምሮ እስከ ሦስት ሰዓት ድረስ የተጠራችበት ሔዳ፣ ወደ እርሷ ያቀኑትንም አስተናግዳ መጻሕፍትን ለመሰብሰብ ጊዜ ትሰጣለች፤ ከቅዳሜና ከእሁዷም እንደዛው።
የመጻሕፍት ዓይነቶች
ፍቅሩ ወደ ማረሚያ ቤቶች የሚገቡ መጻሕፍትን በተመለከተ የተወሰነ ክትትል መደረጉን አይጠላውም። ለታራሚ ሥነልቦና የሚያስፈልግና የሚጠቅም እንጂ፣ የማይሆን ስሜት የሚፈጥርና ተጽእኖ ሊያሳድር የሚችል መጽሐፍ ባይገባ ይመረጣል ሲልም አስተያየት ሰጥቷል።
ነገሩን እነ ሰላማዊትም በሥራቸው አልዘነጉትም። እስከ አሁን 6 ሺሕ 100 መጻሕፍት ተሰብስበው ለማረሚያ ቤቶች ተሰጥተዋል። ሰላማዊት እንደገለጸችው፣ እስከ አሁን መጻሕፍቱን የተረከቡ ስድስት ማረሚያ ቤቶችም ይሄ አይግባም፣ ይሄ ይውጣ የሚል አስተያየት ሰጥተው ክልከላ አላደረጉም። ነገር ግን አስተባባሪዎቹ አስቀድመው በዚህ ላይ ጥንቃቄ ያደርጋሉ።
ሰላም የሚከተለውን አለች፣ ‹‹ስንቀበል የይዘት ምርጫ የለንም፤ ነገር ግን ታራሚዎቹን የሚጠቅም፣ የሚያንጽ እና ሊጠቅም ይችላል የሚሉት መሆን አለበት፤ መልካምነታቸው እንዳለ ሆኖ ልግስናችን ለውጥ ያመጣል ወይ የሚለውን ታሳቢ እንዲያደርጉ እንላለን››
ታድያ በዚህ መሠረት መጻሕፍት ይመረጣሉ። ‹የተሻለ ዜጋ ሊወጣ እየፈለግን የሚያቃቅር ሐሳብ ማስገባት የለብንም›› ስትል ሰላማዊት ገልጻዋለች። ተስፋን የሚነጥቁ ሳይሆን የሚሰጡ፣ ልዩነትን የሚሰብኩ ሳይሆን አንድነት ላይ ያተኮሩ መጻሕፍት ለሚፈለገው ለውጥ ጠቃሚ እንደሚሆኑም እሙን ነው።
የታራሚዎች ምላሽ
ሰላማዊት እንዳለችው ቤተ መጻሕፍት የሌለባቸው ማረሚያ ቤቶች አሉ። መጻሕፍትን ሲሰጧቸው ቤተ መጻሕፍት የገነቡ እንዳሉ ሁሉ፣ ተቀብለው እስከ ቅርብ ጊዜ ደረስ የስቀመጡና ቤተ መጻሕፍት ያላዘጋ ማረሚያ ቤቶች እንዳሉ መታዘቧንም ጠቅሳለች።
‹‹አብዛኛው ሰው ለጥየቃ ሲመጣ ምግብና ልብሰ ነው የሚያመጣልን። ይህ ያስፈልጋችኋል ብሎ ያመጣልን [መጻሕፍትን]የለም። እናንተ ግን ከዛ ባለፈ የሚጠቅም ነገር ነው ያመጣችሁልን እና እናመሰግናለን።›› እነ ሰላማዊት ከአንድ ታራሚ የተቀበሉት አስተያየት ነው።
ግን አሁንም ቢሆን ብዙ ችግር አለ ትላለች ሰላማዊት። በተለይም ሴትና ወንድ እስረኞች መቀላቀል ስለማይችሉ ቤተ መጻሕፍቱ ደግሞ በወንዶች ማረሚያ ቤት የሚገኝ በመሆኑ፣ ሴቶች መጻሕፍት አያገኙም። ይህን ለመፍታት ለጊዜው የውሰት አገልግሎት አማራጭ ሲሆን፣ እኩል አገልግሎት መስጠት እንዳለበት ግን ሰላማዊት አጥብቃ ገልጻችለች።
ፍቅሩ በበኩሉ፤ መጻሕፍትን ማድረሱ ጥሩ ሆኖ ለንባብ ማነሳሳትም ያስፈልጋል። እንደሚለው ከሆነ በውጪ ያለ ሰው፣ ታራሚ ሁሉ የንባብ ፍላጎት ያለው ቢመስለውም፣ እውነቱ እንደዛ አይደለም። ቢያንስ እርሱ በግሉ የታዘበውን ሲያብራራ፣ ‹‹ብዙዎቹ መጻሕፍት አያነቡም። ያለውን ቤተ መጻሕፍትም አይጠቀሙበትም። እናም የንባብ ቅስቀሳውና ማንቃቱ በማረሚያ ቤት ውስጥም ያስፈልጋል።›› ብሏል።
እስከ መቼ ይቀጥላል?
ሰላማዊት እንደምትለው ማኅበር የማቋቋም እርምጃው ተሔዶበታል። እናም ማረሚያ ቤቶችን በመጻሕፍት ከማዳረስ ውጪ ለገጠር ትምህርት ቤቶች፣ ለወጣት ማዕከላት ቤተ መጻሕፍት ማስገንባት ድረስ እቅዳቸው ነው። ከዛም አልፎ በካፌና መንገዶች ላይ በተለያየ ጥበቃ የሚቀመጡ ሰዎች እንዲያነቡ የሚችሉባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸትንም ከረጅም ጊዜ እቅዳቸው ውስጥ አኑረዋል።
በዚህ የምታገኘው ውስጣዊ እርካታ እንደሆነ የምትናገረው ሰላማዊት፣ አቅም ያላቸው ግለሰቦች ቢያንስ መድረኮች ላይ በነጻ የኪነጥበብ ሥራዎችን የሚያቀርቡ ባለሙያዎች፣ ከጊዜያቸው ውጪ ገንዘብም ወጪ እንዳያደርጉ፣ ወጪያቸውን ቢሸፍኑልን ደስ ይለናል ትላለች። የኪነጥበብ ባለሙያዎች ሐሳቡን ወድደው ያለ ክፍያ ነውና የሚያገለግሉት።
ሰላማዊት በምታስተባብረው በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ወጣቶች፣ በበጎ ፈቃድ የሚሠሩ ናቸው። ብዙውን ወጪ ብዙ ጊዜ የሚሸፍኑትም ራሳቸው መሆናቸውን የጠቀሰችው ሰላማዊት፣ በተለየ ግን ጅማ፣ ሐዋሳ፣ ባህርዳር እና አሶሳ ዩኒቨርሲቲን አመስግናለች። መጻሕፍቱን ወደ ማረሚያ ቤቶቹ በማድረስና ወጪዎችን በመሸፈን ድጋፋቸው ከእንቅስቃሴው ጋር ስለነበር።
በአንጻሩ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ተመሳሳይ ድጋፍ ባለማድረጉ፣ የተሰረዙ መርሃ ግብሮች ስለመኖራቸውጠቅሳለች። ቢሆንም በራሳቸው ወጪ መጻሕፍቱን በደማቅ መርሃ ግብር እንዳስረከቡ አስታውሳለች።
ፈቃደኛ የሆነ ቢያግዘን ያለቻቸው ጉዳዮች አሉ። መጻሕፍትን የማቀስቀመጫ ቦታ፣ መጻሕፍቱን ከሚገባው ቦታ ለማድረስ የማጓጓዣ ነገር፣ ማኅበር ሊመሠርቱ ስለሆነ ቋሚ ቢሮ እንዲያገኙ የሚረዳቸው ይፈልጋሉ። ያም ሆነ ይህ ሥራቸውን ግን እንደሚቀጥሉ ሰላማዊት ጠቅሳለች። አያይዛም በበጎ ፈቃደኝነት ሥራዎችን ያቀረቡና ሐሳባቸውን የደገፉ ሰዎችን፣ ታዳሚዎችን፣ ባሕርዳር፣ ጅማ እና አሶሳ ዩኒቨሪሲቲዎችን፤ የተቀበሏቸውን ማረሚያ ቤቶች እንዲሁም የሚድያ አካላትን አመስግኝልኝ ስትል ለአዲስ ማለዳ መልዕክት አስተላልፋለች።
ሰኞ ማምሻውን?
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በክልሉ ካሉ ሦስት ማረሚያ ቤቶች መካከል ለአንዱ 1500 መጻሕፍት አስረክበዋል። ይሁንና የተቀሩት ኹለት ማረሚያ ቤቶች ‹‹እኛንስ ምው ዘነጋችሁን?›› በማለታቸው ከነገ በስቲያ ታኅሳስ 13/2012 በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ማምሻውን 11፡00 ሰዓት ጀምሮ በሚከናወነው መርሃ ግብር የሚሰበሰቡ መጻሕፍት ለእነዚህ ኹለት ማረሚያ ቤቶች የሚሰጥ ይሆናል ተብሏል።
አንጋፋና ወጣት የኪነጥበብ ባለሙያዎች በሚሳተፉበትና ሥራዎቻቸውን በሚቂርቡበት በዚህ መድረክ መታደም ለሚሹ፣ መግቢያው ኹለት መጻሕፍት ነው ተብሏል።

ቅጽ 2 ቁጥር 59 ታኅሣሥ 11 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com