የኢትዮጵያ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተለማማጅ ሠራተኞች የሙያ መልመጃ አፈጻጸም መመሪያ ማዘጋጀቱን ገለጸ።
የሠራተኛና ማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያዘጋጀው የተለማማጅ ሠራተኞች የሙያ መልመጃ አፈጻጸም መመሪያ፣ አሠሪዎች ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት ለኢኮኖሚው አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እና የሠራተኛውን የሙያ ክህሎት በተግባር ለማዳበር በሥራ ገበያው ብቁና ተወዳዳሪ
የሰው ኃይል ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል። ይሁን እንጅ እስካሁን ተለማማጅ ሠራተኞች ተገቢውን የሙያ መልመጃ ሥልጠና በመውሰድ ተወዳዳሪ የሚሆኑበት እና አሠሪው ተለማማጅ ሠራተኞችን መልምሎ የሚያሠራበት ግልጽ የአሠራር ሥርዓት አለመኖሩ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱ በረቂቅ መመሪያው ላይ ተገልጿል።
ክፍተቱን የተመለከተው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ወጥነት ያለው የተለማማጅ ሠራተኞች የሙያ መልመጃ አሠራር ሥርዓት በመዘርጋት፣ የአሠሪውን የሰው ኃይል ፍላጎት ለማሟላት እና የተለማማጅ ሠራተኞን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ በአሠሪና በሠራተኛ ጉዳይ ዐዋጅ ቁጥር 1156/2011 መሠረት መመሪያው መዘጋጀቱ ተመላክቷል።
የመመሪያው ዋና ዋና ዓላማዎች የተለማማጅ ሠራተኞች የምዝገባ እና ምልመላ ሒደትን፣ የተለማማጅ ሠራተኞችን የሙያ መልመጃ ውል እና ይዘትን እንዲሁም የአለማማጅ ድርጅት እና የተለማማጅ ሠራተኛን ግዴታ ለመወሰን መሆኑን በረቂቁ ላይ ተገልጿል።
በረቂቅ መመሪያው ላይ የአለማማጅ ድርጅት እና የተለማማጅ ሠራተኛ ግደታ የተቀመጠ ሲሆን፣ አለማማጅ ድርጅት በዐዋጁ መሠረት ለወጣትና ሴት ሠራተኞች የተከለከሉ ሥራዎችን ያለማሠራት፣ ለለማጁ በውሉ መሠረት በጊዜውና በቦታው ተገቢውን ክፍያ የመክፈል፣ የሕዝብ በዓላትና የዕረፍት ጊዜ ከእነ ክፍያው የመፈጸም፣ የለማጁን ሰብዓዊ ክብርና መብት የመጠበቅና የማክበር እንዲሁም ለለማጅ የሠለጠነበትን ሙያና ሥልጠናው የፈጀውን ጊዜ የሚገልጽ የምስክር ወረቀት የመስጠት ግዴታ ይኖርበታል።
በረቂቅ መመሪያው ላይ የተካተተው የለማጅ ሠራተኛ ግዴታ፤ የሥራ ስዓት ማክበርና ያለበቂ ምክንያት ከሥራ አለመቅረት፣ የድርጅቱን ምስጢር መጠበቅ፣ የድርጅቱን ደንብና ሥርዓት የማክበር እና ለሥራ የተሰጡትን መሣሪያዎችና ንብረቶች በጥንቃቄ የመያዝ ግደታ እንደሆነ ተጠቅሷል።
አሠሪዎች ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት በኢኮኖሚው አዎንታዊ አስተዋፆ እንዲያሳድሩ እና ሠራተኛው የሙያ ክህሎት በተግባር በማዳበር በሥራ ገበያው ላይ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ዐዋጅ 1156/2011 መሠረት ተዘጋጀው የሙያ መልመጃ የአፈጻጸም መመሪያ ለማዳበር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተጨማሪ ግብዓት በመሰብሰብ ላይ ነው ተብሏል።
በሌላ በኩል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአገር ውስጥ የወቅት ሠራተኛ የሥራ ስምሪት አፈጻጸም መመሪያ ተሻሽሎ ተጨማሪ ግብዓት ከሕዝብ እየተሰበሰበ እንደሆነ ገልጿል። በዚህ መመሪያ ማንኛውም ሰው ሥራ ፈላጊውን ለመቅጠርም ሆነ ለማስቀጠር ከሥራ ፈላጊው ላይ ገንዘብ መቀበል የተከለከለ ነው።
የተሸሻለው ረቂቅ መመሪያ የዘመነ የሥራ ሥምሪት እንዲኖር፣ የሥራ ገበያ መረጃን ከሥራ ፈላጊ ጋር በማገናኘት ሥራ ፈላጊ እንደፍላጎቱና እንደችሎታው፣ እንዲሁም አሠሪው ለሥራው ብቁ የሆነ ሠራተኛ እንዲያገኝ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚያስችል ተመላክቷል።
ቅጽ 3 ቁጥር 150 መስከረም 8 2014



