ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የሚጓዙ ተሳፋሪዎች ከነባሩ ታሪፍ በላይ እየከፈሉ ነው

0
1106

ከአዲስ አበባ ወደተለያዩ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚጓዙ ተሳፋሪዎች ሲከፍሉት ከነበረው ታሪፍ ከዕጥፍ በላይ እየከፈሉ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ቅሬታ አቅራቢዎች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ ከተማ ለመሄድ ሲከፍሉት የነበረው 180 ብር ሲሆን፤ አሁን አውቶቢስ ባለማግኘታቸው በአነስተኛና መለስተኛ የሕዝብ ማመላሰሻ መኪና 500 ብር ከፍለው እየተጓዙ ነው።
ከላምበረት መናኸሪያ ወደ ደሴ ከተማ ለመሄድ ከታሪፉ ዕጥፍ በላይ በመክፈል ከዕቅድ ውጭ ለሆነ ወጭ ተዳርገናል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ከታሪፍ በላይ ከፍለው ለመሄድ ቢስማሙ እንኳን የመኪና አቅርቦት ባለመኖሩ ከወጭው በተጨማሪ በሕዝቡ እሽቅድድምና ትርምስ ለአካላዊ እንግልት እንደተዳረጉ ጠቁመዋል።

ታደለች አሳልፍ የተባለችው ቅሬታ አቅራቢ ወጣት፣ ባሳለፍነው ሳምንት (መስከረም 16) ከላምበረት መናኸሪያ ወደ ደሴ 500 ብር ከፍዬ ነው የሄድኩት በማለት ከገጠማት በመነሳት ምስክርነቷን ገልጻለች።

ትኬት ለመቁረጥ ከኹለት ቀን በላይ ወደ ላምበረት መናኸሪያ ብትመላለስም መኪና ባለመኖሩ ትኬት መቁረጥ እንዳልቻለች ታስታውሳለች። ‹‹በመጨረሻም በአነስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት በመጓዝ ከታሪፍ በላይ ለሆነ ወጭ ተዳርጌአለሁ›› በማለትም ታስረዳለች።
አክላም ሕዝቡ ላላሰበበት ወጪ ከመዳረግ አልፎ ሳምንቱን ሙሉ በመናኸሪያው እየተጉላላ መሆኑን የገለጸች ሲሆን፣ በተለይም በዕድሜ የገፉ ሰዎች ተጋፍተው ወረፋ ለመያዝ አቅም ስለሚያንሳቸው የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ መፍትሄ ሊሰጥበት ይገባል በማለት አሳስባለች።

ትዕግስት ምስጋን የተባለች ወጣትም በበኩሏ፣ ባሳለፍነው ሳምንት ከአንድ ቀን በፊት ትኬት ለመቁረጥ ወደ ላምበረት መናኸሪያ ብትሄድም በትኬት ቆራጮች ዘንድ ‹ዛሬ ትኬት መቁረጥ አይቻልም። ነገ ነይ› በመባሏ ሳትቆርጥ እንደተመለሰች ትናገራለች። እንደተባለችው በማግስቱ ብትሄድም ትራንስፖርት እንዳላገኘች ነው እማኝነቷን የተናገረችው።

‹‹እስከአሁን በነበረው አሠራር ነገ ለሚደረግ ጉዞ ዛሬ ማለትም አንድ ቀን ቀድሞ ትኬት እየተቆረጠ የቆየ ቢሆንም፣ አሁን ላይ የመኪና ዕጥረት በመኖሩ ከጉዞው ዕለት ጠዋት ውጪ መቁረጥ አይቻልም›› ያለችው ትዕግስት፣ ጠዋት ላይ ተሳፋሪ ስለሚበዛ የሰዎች ትርምስና መጉላላት ከመፈጠሩም በላይ የታሪፍ ጭማሪ እንዳለና ከታሪፍ በላይ ከፍላ ለመሄድ እንኳን መኪና አለማግኘቷን ነው የጠቆመችው።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት የላምበረት መናኸሪያ የሕዝብ ትራንስፖርት ቡድን መሪ ተወካይ ገዛኸኝ አየለ ጋር ቆይታ ያደረገች ሲሆን፣ የቀረበው ቅሬታ እውነት መሆኑን በመመስከር ምክንያቱንም አብራርተዋል።
ተወካዩ እንደሚሉት ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ በጦርነቱን ምክንያት መኪናዎች ግዳጅ በመውጣታቸው የተሽከርካሪ ዕጥረት እንደገጠማቸው እና ትኬት በቀጣይነት እየተቆረጠ አለመሆኑን አመላክተዋል።

ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ተሽከርካሪዎች ወደ ጦርነቱ ለግዳጅ ሔደዋል ያሉት ገዛኸኝ፣ በዓሉን (የመስቀል በዓል) በማስመልከት ካለው የተሳፋሪ ፍሰት ብዛት አንጻር ከመናኸሪያ ውጪ ያሉ ተሽከርካሪዎችን ወደ መናኸሪያ በማስገባት አገልግሎቱ የሚሰጥበት አጋጣሚ መፈጠሩን ገልጸዋል። ከመደበኛ ውጪ ለሆኑ ተሽከርካሪዎች ከ35 እስከ 50 በመቶ ጭማሪ መደረጉንም ነው አያይዘው የጠቆሙት።

ገዛኸኝ አክለውም ‹‹ትኬት የምንቆርጠው ተሽከርካሪ መኖሩን እርግጠኛ ስንሆን ነው። እርግጠኛ ካልሆንን ተገድደው የሄዱት መኪናዎች ተመልሰው ችግሩ እስከሚስተካከል ድረስ በተለመደው መልኩ ቅድሚያ መቁረጥ አንችልም›› ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ከተወካዩ እንደሰማችው፣ ወደተለያዩ አቅጣጫዎች የተመደቡት ተረኛ ተሽከርካሪዎች መገኘት እንዳልቻሉና ባሳለፍነው ነሐሴ 15/2014 ወደ ሰሜኑ ክፍል የመንገደኞች አገልግሎት ለመስጠት የተገኘው አንድ አውቶብስ ብቻ መሆኑን ነው።

500 ብር የሚያስከፍሉት የተሽከርካሪ ዕጥረት መኖሩን ምክንያት በማድረግ ከመናኸሪያ ውጪ ‹በሕገ ወጥ የሚሠሩ› ሹፈሮች መሆናቸውን ያመላከቱት ቡድን መሪው፣ በተቻለ መጠን ችግሩን ለማቃለል በተወሰነ የዋጋ ጭማሪ ወደ መናኸሪያው ከሚያስገቧቸው ተሽከርካሪዎች ይልቅ በውጪ ያሉት ይበልጥ ውድ መሆናቸውን አመላክተዋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለመጠየቅ ወደ አዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ዳይሬክተር አረጋዊ ማሩ በተደጋጋሚ ስልክ ብትደውልም፣ ስልክ ባለማንሳታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻለችም።


ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here