“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።
የቀረበኝንና በንባብ የማውቀውን ይህን ታሪክ ላስታውሳችሁ ወደድኩ። ምሳሌ እስከ ፍጻሜ አያጸናም የሚለውን የአገራችንን ብሂል ያዙልኝና ሐሳቤን ብቻ ልብ እንድትሉልኝ ከወዲሁ አደራ እላለሁ።
በቅዱስ መጽሐፍ ከሚገኙና በብዙኀን ከሚታወቁ ታሪኮች አንዱ የሙሴ ታሪክ ነው። ሙሴ የተወለደው በግብጽ የእስራኤል ልጆች መከራ በበዛበት ዘመን ነው። በጊዜው የነበረው የግብጽ ንጉሥ ታድያ እንደውም ወንድ ልጆች ሁሉ ሲወለዱ ወደ ወንዝ እንዲጣሉ አዘዘ። የሙሴ እናት በዛን ወቅት ነበርና የወለደችው፣ ልጇ እንዳይገደልባት ሸሸገችው። ያም እንደማያተርፍላት ስታውቅ ደግሞ በሳጥን አድርጋ ወንዝ ዳር አደረገችው።
የፈርዖን ልጅ ሳጥኑን ዐይታ አስከፈተች። በኋላም በሳጥኑ ውስጥ ያለውን የሚያሳሳ ሕጻን ልጅ ስትመለከት ልታሳድገው ወሰነች። ሙሴ ብላም ሥም አወጣችለት። ነገሩን ታድያ የሙሴ እህት በርቀት ስትከታተል ነበርና ወደ ፈርዖን ልጅ ቀርባ ልጁን ጡት የምታጠባ ሴት ላምጣልሽ አለቻት። የፈረንዖን ልጅም በሐሳቡ ተስማማች። በዚህ የተነሳ ሙሴ በግብጽ በፈርዖን ቤት ግን በእናቱ እጅ አደገ።
የዚህን ታሪክ መንፈሳዊ አንድምታ አቆይተን፣ በጨዋ ደንብ ላይ ላዩን እንመልከት። ሙሴ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ነጻ አውጥቷል። በዘመኑና በጊዜው ታላቅ የጀግንነትን ገድል የፈጸመ ነው። ይህን ሊያደርግ የቻለው እንዴት ነው? እንደውም በፈርዖን ቤት ያደገ ሰው አይደለም ወይ? አዎን ነው! ግን እናቱ እዚህ ላይ ትልቅ ድርሻ ነበራት።
የሙሴ እናት ልጇን ከሞት አትርፋለች፣ በብልሃትም ከንጉሡ ጊቢ ደርሳ ከእልፍኙ ዘልቃ ልጇን እያጠባች አሳድጋለች። ‹ከሞት ድነህ እዚህ መግባትህ እድለኛ ነህ! ዘና ፈታ ብለህ እዚህ ንጉሡ ጋር ተዝናንተህ ኑር! ራስህን አስቀድም!› የመሰለ ምክር መክራ አይደለም ያሳደገችው። በምን አወቅን? እንደዛ ቢሆን ሙሴን ምን አንከራተተው?
ሙሴ እናቱ በልጅነት የዘራችበት የአምላክ ፍቅርና ክብር፣ እንዲሁም ለወገን የመድረስና ወደፊት የመራመድ ጽናት እንደነበር በጨዋ ደንብ እንረዳለን። ሙሴ በአዋቂነቱ ማለዳ ላይ ያደረገው፣ ለትልቅ ኃላፊነት የመመረጡ መነሻም ያ ነበር።
እናት በልጆች ሕይወት ውስጥ ያላት ድርሻ ከመጋረጃው በስተጀርባ እንዳለ ከያኒ ጥልቅና ሰፊ ነው። እናት በልጇን የፈለገችውን ዓይነት ሰው ልትሠራ ትችላለች። ምንም እንኳ እንደ ኢትዮጵያዊ መለኮታዊ ኃይልና የምናምነውን አምላክ ጣልቃ ገብነት የምንሻ ቢሆንም፣ ወፎች እንኳ ሳይዘሩ ሳያጭዱ ቢበሉ መብረር እንዳለባቸው ሁሉ፣ ቤተሰብም በልጆች ስብእና ግንባታ ውስጥ እንደወፊቱ ከመብረርም ላቅ ያለ ጥረትና ሥራ ይፈለግባቸዋል።
ልጆቻቸውን ይዘው ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ፣ ከአገራቸው የተሰደዱ፣ በምቾትም ሆነ ምቾት በማጣት ውስጥ ያሉና ልጃቸውን በጭንቅ ውስጥ እያሳደጉ የሚገኙ እናቶች፣ ለልጆቻቸው ነገ ትልቅ ቦታ የሚያደርስ ስብዕናን መስጠት እንደሚችሉ ሊያስቡ ያሻል። ዛሬን ቆንጆ ልብስ ለማልበስ፣ የሚታፍጠውን ምግብ ለማቅረብ፣ ቅንጡ ትምህርት ቤት አስገብቶ ለማስተማር አይችሉ ይሆናል። ከዛ በላይ ግን ልጃቸውን አገር ወዳድ፣ ጽኑ እና ብርቱ ስብእና ያለውን የሚያደርጉበት ጥበብ አላቸው። እናቶች! ይህን ጥበብ ልብ እንበል!
መቅደስ ቹቹ
ቅጽ 3 ቁጥር 152 መስከረም 22 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n


