ዛሬ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት በሕዝብ የተመረጠውና እንደገና የተዋቀረው አዲስ መንግሥት በፌዴራል ደረጃ ይመሠረታል።
ከጥዋቱ 2:30 ጀምሮ የኢፌዲሪ 6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የምስረታና የመክፈቻ ጉባኤ እንደሚካሄድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል።
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት፥ በሕዝብ ተመርጦ አዲስ የሚቋቋም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ጊዜውን መጀመር ያለበት በ“መስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ ነው” ብሎ በደነገገው መሠረት ነው ዛሬ በፌዴራል ደረጃ አዲስ መንግሥት የሚመሠረተው።
በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ የመክፈቻ ጉባኤ ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር የሚያደርጉ ሲሆን፤ ንግግራቸውም የዘንድሮውን በጀት ዓመት የመንግሥት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች እንደሚያመላክት ይጠበቃል።
በመስራች ጉባኤው ላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡
በጉባኤውም በሁለቱም ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤ እና ምክትል አፈ ጉባኤ የሚሾሙ ሲሆን፤ እንዲሁም ምክር ቤቱ በ6ተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳድሮ አብላጫ ወንበር ያገኘው ብልፅግና ፓርቲ የሚወክለውን ዕጩ፣ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ይሰይማል፡፡
ይህን ተከትሎም የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በዓለ ሲመት የሚከናወን ሲሆን፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአዲስ ተሿሚው ጠቅላይ ሚኒስትር የሚቀርብለትን የካቢኔ አባላት እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ሹመት መርምሮ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የጉባኤው ሂደትም በአገር ውስጥ የቴሌቭዥንና ሬዲዮ ጣቢያዎች በቀጥታ ስርጭት የሚተላለፍ ይሆናል፡፡
__________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n
__________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




