ሠሞኑን መነጋገሪያ ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ የአህያ ዕርድ በድጋሚ ሊጀመር ነው መባሉን ተከትሎ የተሰጡ አስተያየቶች ናቸው። ከዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ አህያ ታርዶ ለገበያ ሊውል ነው ሲባል ያልተቃወመ አልነበረም።
የታረዱት አህዮች ሥጋ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ለገበያ ይቀርባል ባይባልም፣ የጅብ ሥጋ ሲሸጡ በተያዙባት አገር ዕድሉ ተመቻችቶላቸው አይምሩንም በሚል ዕሳቤም ብዙኀኑ ተቃውሞት ነበር። ኩባንያው ማረጃና መበለቻ ቄራውን ገንብቶ ሥራ እስኪጀምር ምንም ሳይባል ቆይቶ፣ እንዲያውም ከመንግሥት ዕውቅና አግኝቶ ሥራውን ከጀመረ በኋላ ላይ ነበር ሲጮህበት ሥራውን ለማቆም የተገደደው።
ብዙዎቻችን የምናስታውሰው፣ አንዲት አህያ ታርዳ ቆርቆሮ ላይ ተደርጋ ስትገፈፍ የሚያሳይ ምስልን ነበር። አብዛኛው ድርጊቱን የተመለከተ ኢትዮጵያዊ፣ “እነዚህ ቻይናዎች መዓት ሳያመጡብን በፊት አስወጧቸው፣ እምቢ ከተባለም ማንም አህያውን እንዳይሸጥላቸው” እያለ ሲቀሰቅስ ነበር።
“አህያ ቢውል ቢያድር እንጂ የጅብ መሆኗ አይቀርም” ይባል የነበረው ቀረ እያሉ፣ ያረጁት ቢታረዱና ቆዳቸውና ሥጋቸው ተዘጋጅቶ ወደውጭ ቢላክ ምን አለበት እያሉ ለማግባባት የሞከሩ ነበሩ።
ኢትዮጵያ የኃይማኖተኞች አገር ናት፤ እድሜ ልኳን ስታገለግለን የኖረችውን አህያ ገለናትም ልንጠቀምባት አይገባም በሚል፣ እንዲሁም እንደቤተሰብ የምትታይ በመሆኗ መጦሪያ ባይኖራትም ጅቡ ይብላት፤ እሱስ ማን አለው በማለት ጉዳዩን በማዋዛት ሲቃወሙ ብዙዎች ቆይተዋል።
የሕዝቡ ቁጣ የበረታበት መንግሥት እስኪበርዱ ብሎ ነው መሰል ከልክሎ ወደሌላ አገር እንደሄዱም አስወርቶ ነበር። ነገር ግን፣ ሕዝቡ የማስታወስ ብቃቱ አጭር ወይም “ሾርት ሜሞሪ” ነው ብለው የሚያምኑ ባለሥልጣናቱ፣ በድብቅ መልሰው ፈቅደውላቸው ከሰሞኑ ዕርድ መጀመራቸው ተወርቷል።
ድጋሚ ጀመሩ መባሉን ተከትሎ ሕዝቡ እንደቀደመው ጊዜ “ጉድ ነው” እያለ እንዳይወያይበት ከዛ የባሰ ሰው ላይ የሚፈፀምን ግፍ እየሠማ ስለለመደው ብዙም ትኩረት አልሰጠውም። ያም ቢሆን ግን የተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች በዝምታ አላለፉትም።
አንዳንዶች ተግባሩን ፊት ለፊት መደገፍ ፈርተው መንግሥትንም ሆነ ባለሃብቱን ላለማስቀየምም፣ የተግባሩ በጎ ጎን የመሰላቸውን ለማስተላለፍ ሲጥሩ ነበር። በሕገ-ወጥ እየወጡ ጎረቤት አገር ከሚታረዱ እዚሁ እንጠቀምባቸው የሚለውን አመክንዮ ብዙዎች መቀበላቸው፣ “በፊትም እንጠቀም ነበር እኮ አሁን ምቀኝነት ካልሆነ” አስብሎባቸዋል። የተወሰኑት ውሳኔው የተወሰነበትን ምክንያት ተነግሯቸው ይሁን እየገመቱ ለማስተባበል ሞክረዋል። ያም ሆነ ይህ ግን ቀናት አልፈው ምንም የተከለከለም ሆነ የቀረበ ሪፖርት የለም።
የተወሰኑ ግለሰቦች እናንተን ሳይሆን እዚህ አካባቢ ያሉትን አህዮች ነው የሚመለከተው በማለት በጉዳዩ ለማሾፍ የተቃወሙትንም ለመዝለፍ ሞክረዋል። አንዳንዶች፣ “ጥርሱ እንደወለቀበት ጅብ ምነው ትታረድልን አላችሁ” እያሉ አፀፋውን ለመመለስ ሞክረዋል።
በሌላ በኩል፣ ዕርዱ አሰላ ነው የሚፈፀመው በመባሉ ለተረብ የተጋለጡ የአሰላ ልጆች ምላሻቸውን አሰምተዋል። የሚታረዱት አህዮች በ100 ኪሎ ሜትር ውስጥ የሚገዙ አይደሉም መባሉን በማንሳት አረጋግተዋል። በር ላይ የቀረቡላቸውን በምን እንደሚለዩ እየጠቀሱ እነሱም በተወለዱበት ቦታ ተለይተው መድሎ ሊፈፀምባቸው ነው ብለዋል። የአሰላ ሻጭ አርቆ ወስዶ ላለመሸጡ፣ የሌላውስ ለምን እንደተፈረደበት ግን ማንም ደፍሮ አልተናገረም። አህዮቹን ለመለየት መታወቂያ እንዳይታደላቸውም የሰጉ አሉ።
ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n


