አገር አቋራጭ ጉዞና ፍተሻው

0
1484

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በሕገወጥ መንገድ የሚዘዋወሩ የጦር መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች በዝተዋል። ይህን ለመቆጣጠር በየቦታው የፍተሻ ኬላ ተቋቁሞ የፀጥታ ኃይሎች ከሕብረተሰቡ ጋር በመሆን 24 ሰዓት ይፈትሻሉ።
እንዲህ አይነት ፍተሻዎች ወደጦር ቀጠናው በተቃረቡ ቁጥር እየጨመሩ ይመጣሉ። ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ በሚወስደው የ400 ኪሎሜትር መንገድ ተጓዦች ከ20 በላይ ጊዜ ቆመው በተደጋጋሚ ለተመሳሳይ ፍተሻ ይጠየቃሉ። አላማው ተገቢ ቢሆንም ውጤታማ የማያደርግ መንገድን የሚጠቀሙ፣ እንዲሁም አጋጣሚውን ሌላ አጀንዳቸውን ለማስፈፀም የሚጠቀሙበት አሉ። ስለፍተሻዎቹ አይነትና ልዩነት የአዲስ ማለዳው ብንያም ዓሊ በተለያዩ ጉዞዎች ወቅት የታዘበውን እንዲህ አሰናድቶታል።

ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የተጀመረው ጥንት ቢሆንም፣ ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂዎች ጉዟችንን ፈጣንና ድካም የሌለበት ከአደረጉት ዓመታት ተቆጥረዋል። ቀናትን ይፈጅ የነበረው ጉዞ በሰዓታት ውስጥ እንዲያልቅ ከሚያደርጉ የመጓጓዣ መንገዶች መካከል አብዛኛው ሕብረተሰብ የሚጠቀምበት የትራንስፖርት ምርጫ አውቶቡስ የሚባለውን የሕዝብ ማማላለሻ አማራጭ ነው።

አውቶቡሶችን ተጠቅሞ መጓጓዝ ከተጀመረ ግማሽ ምዕተ-ዓመት ቢያልፍም፣ የጉዞው ቅልጥፍና እየጨመረ አድካሚነቱም ሆነ አሰልቺነቱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየቀነሰ መጥቷል። ለዚህ ደግሞ የተሸከርካሪዎቹ መዘመን የአንበሳውን ድርሻ ሲወስድ፣ የመንገዶች ምቹነትም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። ዘመናዊ አውቶቡሶች ከመጡ ወዲህ ኹለት ቀን ይፈጁ የነበሩ መንገዶች በአንድ ቀን ማለቅም ችለዋል።

ዘመናዊ መኪኖችና መንገዶች ጉዞዎቻችንን ቢያሳጥሩልንም፣ ክፍያቸው ጭማሪ ስላለው አብዛኛው ሰው አይጠቀምባቸውም። አውሮፕላንንም ሆነ የግል የትራንስፖርት አማራጮችን ለመጠቀም አቅሙ ያላቸው ጥቂቶች እንደመሆናቸው፣ አብዛኛው ተጠቃሚ መንግሥት ባዘጋጃቸው መናኸሪያዎች የሚጠቀሙትን ዋጋ የሚተመንላቸውን ተሸከርካሪዎችን መጠቀም ይመርጣል። ይህ ቢሆንም ግን፣ ከሠሞኑ እነዚህ ተሽከርካሪዎች በየመናኸሪያው እየተገኙ አይደለም።

ወቅታዊው የአገራችን ሁኔታ ስላስገደደ ተሸከርካሪዎች ለልዩ ግዳጅ ወደጦር ግንባር ስለተሰማሩ የመጓጓዣ ዕጥረት እንዳለ ተነግሯል። ለወታደር ማጓጓዣም ይሁን ለስንቅ ማመላለሻ የሚሆኑ ተሸከርካሪዎች በበጎ ፈቃደኝነት መሠማራት ከጀመሩ ውሎ አድሯል። እንደታንክና መድፍ እነዚህ ተሸከርካሪዎች ለዘመቻው ትልቅ አስተዋጽኦ ስለሚኖራቸው፣ እንደጦር መሣሪያዎቹ ይማረካሉ ይወድማሉ። ይህን እያወቁ የጋራ የአገር ጉዳይ ነው ብለው ለዘመቻው ሀብት ንብረታቸውን አሳልፈው የሚሰጡ ሊመሰገኑና ውለታቸውም ሊታወስ እንደሚገባ ብዙዎች ይስማማሉ።

የንብረቶቹ ባለቤት ማንነት እንዳይታወቅ ታርጋቸውን እስከመፍታት የሚደርስ ትብብር ቢደርግላቸውም፣ ይህን ተገን አድርገው ሌሎች አጭበርባሪዎች ዕድሉን እንዳይጠቀሙበት ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ለዘመቻው አገልግሎት ስለመስጠታቸው ለማወቅ የሚያስቸግር አነስተኛ ተሸከርካሪዎችም ታርጋ ፈተው ለጦር ቀጠናው ቅርብ በሆኑ አካባቢዎች በንግድ ሥራ ተሰማርተው ይታያሉ። በርግጥ ግዳጅ ሳይኖርባቸው ተገትረው ይቁሙና ሕብረተሰቡ ይቸገር ማለት ሳይሆን፣ ታርጋቸውን መልሰው መለጠፍ የሚችሉበት ሁኔታ ቢመቻች ጥሩ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ። በአንዳንድ አጋጣሚ ኹለቱም(የፊትም የኋላም) ታርጋ የሌላቸው የሕዝብ ማመላለሻዎች ከፍተኛ ጭማሪ በማድረግ ሲያመላልሱ ይታያሉ። ማውረድ ከሚጠበቅባቸው ቦታም አርቀው የሚያወርዱ ደንታ የሌላቸው አሽከርካሪዎችንም ማየትም እየተለመደ ነው።

በጦር ግንባር ጦሩ ከሠፈረበት አካባቢ ቆመው ግዳጅ የሚጠብቁ አውቶቡሶች መኖራቸውን በተወሰኑ ግንባሮች ተገኝታ ያስተዋለችው አዲስ ማለዳ፣ ባደረገችው ማጣራት በእንዲህ ዓይነት መንገድ ከግማሽ በላይ የሚሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተሸከርካሪዎች ከመደበኛው ሥርዓት ወጥተው እያገለገሉ ነው እንደሚባል ነው። ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ወደደሴ ለመጓዝ ቀድሞ ትኬት መቁረጥ ካለመቻሉ በላይ፣ ሕዝቡ ጠዋት 11 ሰዓት እንዲመጣ እየታዘዘ፣ ከሌሊት ጀምሮ ለረጅም ሰልፍ ይዳረጋል። በብርድ ዕቃ ተሸክሞ ቆሞ ሲጠብቅ ከንጋቱ አንድና ኹለት ሰዓት እንደዘበት የሚደርሱበት መንገደኛ፣ ለብዙ እንግልት ተዳርጎ በፐርሰንት ክፈል ተብሎ ከፍተኛ ጭማሪ፣ ለነዛው የሉም ለተባሉት መኪኖች፣ ከፍሎ ረፍዶበት ይደርሳል::

ከረጅም ሰልፍ በኋላም ቢሆን ያ ኹሉ መንገደኛ ተጨማሪ ክፍያ እየከፈለ መጓዝ መቻሉ የሚያሳየው የተሸከርካሪ ዕጥረት መኖሩን ሳይሆን ዋጋ ጨምሮ ለመውሰድ አጋጣሚውን ለመጠቀም የፈለጉ አገልግሎት ሰጪዎች መኖራቸውን ነው። በፊት እንዲህ አይነት ሴራ ለመፈጸም መናኸሪያ ሳይገቡ በየሰፈሩ የሚደበቁ ነበሩ። ተጓዡ መኪና አጥቶ ሲጨንቀው ደላላ በመላክ በከፍተኛ ጭማሪ የሚወስዱትን አሽከርካሪዎችንም ሆነ መኪኖችን መንግሥት ይቆጣጠር ነበር።

ከትራፊክ ፖሊሶች ጋር በመተባበር ውስጥ ለውስጥ መንገዶች ድረስ በመዝለቅ ታርጋ የመፍታትና የመቅጣት ተግባር ይከናወን ስለነበር ችግሩ ዘልቆ አልቆየም ነበር። አሁን ግን ዘመቻውን እንደምክንያት በመጠቀም፣ አንድ መኪና እንኳን አስቀድሞ ገብቶ ትኬት የማይቆረጥባቸው ቀናት እንደሚደጋገሙ ችግሩን ያስተዋሉት ይናገራሉ።

የላምበረት መናኸሪያ የሕዝብ ትራንስፖርት ቡድን መሪ ተወካይ የሆኑትን ገዛኸኝ አየለን አዲስ ማለዳ ባነጋገረችበት ወቅት፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ዕጥረት ለመፍጠር የሚሞክሩትን ለመቆጣጠር እየተሞከረ እንደሆነ ተናግረዋል። ሕብረተሰቡ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚጭኑትን በመለየት እንዲጠቁም የሚመክሩት እኚህ ኃላፊ፣ ዕጥረቱን ለማካካስ የፐርሰንት ጭማሪ ተደርጎ ሕብረተሰቡ እንዲገለገል እየተደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል። ሲመለሱ ጭነው መመለስ ስለማይችሉ ነው ቢሉንም፣ ካደረሱበት ሲመለሱም ዕጥረት አለ በሚል በተመሳሳይ ጭነው እንደሚመለሱ መመልከት ይቻላል። ይህ ቢሆንም ግን፣ ዋናው ትኩረት እጅግ ጭማሪ አድርገው ውጭ በሚጭኑት ላይ መሆኑን አተኩረዋል። ሕብረተሰቡ ጠዋት ተሰልፎ ሲረፍድበትና ሲጨንቀው በደላሎች አማካይነት እየተወሰደ ጉራንጉር ውስጥ ተደብቀው በሚጭኑ ሚኒባስና አምቡላንሶች ለመሳፈር ሲገደድ ይታያል።

አዲስ ማለዳ በተጓዘችበት ዕለት ጉዳዩን ለማጣራት ሞክራ፣ 2 አምቡላንሶች በ500 ብር ዋጋ ሞልተው ጉዞ አድርገዋል፤ ሦስተኛውም ተሳፋሪ እስኪሞላለት እየጠበቀ ነበር። ተመኑ ከ200 ብር የማይበልጠውን መንገድ ከዕጥፍ በላይ ማስጨመራቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከለመዱት መደበኛው ጭማሬያቸውም 100 ብር ጨምረው ሕዝቡን እያሻሙ እንዲጓዝ ያደርጋሉ። ዋጋ ማስወደዳቸው ብቻ ሳይሆን ከትራፊክ ለማምለጥ ውስጥ ለውስጥ እየተሸሎከሎኩ ሕብረተሰቡን ለአላስፈላጊ እንግልት ይዳርጋሉ። በየመንገድ ቆሞ ጥቆማ ለሚሰጥ ቅድሚያ ተቆራጭ ስለሚደረግ ድንገት የተያዘ ደውሎ ያማርርባቸዋል።

በሕገ-ወጥ መንገድ ከመናኸሪያው ቢርቁም፣ ከከተማው ግን ተደብቀው መውጣት አይቻላቸውም። ጣፎ አደባባይ የሚባለው ጋር በትንሹ ሦስት የሚሆኑ ባለመኪና ትራፊኮች ቆመው መውጫ የሌላቸውን ያስቆማሉ። እየተፈራረቁ ስልክ እየተደወለላቸው ከማን ጋር እንደሚያወሩ ባይታወቅም፣ መኪኖችን መርጠው ማስቆማቸው ግን ግልጽ ነው። እኛ የነበርንበት ምንም አይነት ክፍያ ባለመክፈሉ አስቁመውት፣ ወይ አይቀጡት ወይ መክረው አይለቁት ሕዝቡ እስኪሰላች አትውረዱ ተብሎ አሽከርካሪውና ትራፊኮቹ በየተራ ስልክ እያወሩ ለ30 ደቂቃ ያህል ከቆዩ በኋላ ትኬት ሳይቀበል ሹፌሩ እየተናደደ መምጣቱን ማየት ተችሏል።

በየመንገዱ እዚህ ቦታ ነን በሉ እየተባለ የተነሳንበትንም ጭምር እንድንዋሽ ከተደረገ በኋላ ሰንበቴ ከተማ መውጫ ተቆርጦ ፍተሻ ይበዛበታል ለተባለው መንገድ ዝግጅት አድርገዋል። ከአዲስ አበባ መውጫ ጀምሮ በተለያዩ አካላት አሰልቺ የሚባል ፍተሻ ተካሂዷል።

የፍተሻዎች መደጋገም
ከአዲስ አበባ ሳንወጣ በፊት ለፍተሻ መቆም የጀመረው መኪናችን ደሴ ከተማ አምሽቶ እስኪገባ በአጠቃላይ 23 ጊዜ እንዲቆም ተደርጓል። ከ23ቱ ፍተሻዎች ትክክለኛ ነበር ማለት የሚቻለው ኮምቦልቻ መግቢያ የነበረውና ኹሉም ዕቃ ወርዶ (ከጉምሩክ የወጣ ተብሎ ሠነድ የቀረበበት በኹለት ትልልቆቹ በርሚሎች ከታሸገ ነገር በስተቀር) እያንዳንዱ እየተበተነ ተፈትሿል። ይህ የሆነው ከዚህ ቀደም በቦታው ላይ የተያዘ መሣሪያ ስለነበርና ምስጋና ስለቀረበላቸው እንደሆነ ሰምተናል። ይህ ቢሆንም ግን፣ ከሹፌሩና ከረዳቱ ጋር አምባጓሮ ከመፍጠር አላገዳቸውም። “መሽቶብናል አታዘግዩን” በሚልና፣ “እንዴት እንዲህ ትላላችሁ” በሚል በሲቪል ፈታሽና በባለመኪናዎቹ መካከል ግርግር ተፈጥሮ ታጣቂዎችና ተጓጓዡ ሊያበርደው ችሏል።

አብዛኞቹ ፍተሻዎች መታወቂያ ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። አንዳንድ ፈታሾች ዕድሜው ያልደረሰ ከእናቱ ጋር የሚጓዝ ታዳጊንም ለምን የለውም ሲሉ ተደምጠዋል። በቆምንባቸው በኹሉም ቦታዎች መታወቂያ ማሳየት ግድ ሲሆን፣ አንዳንዴ ያስወርዳሉ አንዳንዶቹ ደግሞ ከፍ አድርጋችሁ ካሳያችሁ በቂ ነው ብለው ይናገራሉ።

ከ23 ፍተሻዎች 14ቱን ያስቆሙት ትራፊክ ፖሊሶችና ፌደራል ፖሊሶች ናቸው። ደሴ መግቢያ ላይ መውጫህ የታለ ብላ ከጠየቀች እንስት ትራፊክ በስተቀር የአብዛኞቹ ትኩረት ተጓጓዦቹ ላይ ነው።ኹለት ሰው ትርፍ በመያዙ ካስጠነቀቀችው ሌላ ትራፊክ በስተቀር ለመቅጣት የሞከረ የለም። በዚህ ረገድ ከደሴ ወደሌላ የወሎ ግዛት ስንጓዝ ተጠይቆ የማያውቅ መውጫ ጠይቆ ረዳቱ “የለኝም” ሲል፣ “በል እኚህን ሰው ካሉህ ትርፍ ሰዎች ላይ ጨምረህ ውሰድ” በማለት ተሳፋሪውን ያስደመመ ትራፊክም አጋጥሟል።

ታርጋ መፈታት ቆሟል በሚል ሆን ብሎ በሚያውቀው ትራፊክ በተቀጣው ትኬት ሽፋን ሲጓጓዝ የነበረው አሸከርካሪ፣ ሊሾ የሆነ ጎማና መቀየሪያ ኤስኮርት ይዞ ረጅም ርቀት በመጀመሩ መኪናው አራት ጊዜ በብልሽት ለማቆም ተገዷል። ያለቀ ጎማው ተንፍሶ ቢቀይረውም፣ ቅያሪው ብዙ አልቆየም። ምሳ ሲበላ ዋናው እንዲሠራ ተደርጎ ስለነበር መቀየሪያው በተራው ሲፈነዳ የነበረው ቢመለስም ትንሽ ተጉዞ በድጋሚ ሊተነፍስ ችሏል። መቀየሪያ የሚያውስ ሌላ ተሸከርካሪ እስኪመጣ፣(ብዙዎቹ የለንም እያሉ አንዳንዶች የተነፈሰ ይዘው እንደሚጓዙ እየተናገሩ ሲያልፉ) በተገኘው ተቀይሮም ጉዞ እስኪጀመር ኹለት ሰዓት ጉዞው ዘግይቷል ። ትራፊኮች መቆጣጠር ያለባቸው እንዲህ የመንገደኞችን ደህንነት ሊጎዳ የሚችል ነገርን ቢሆንም ማናቸውም ሳያስተውሉት፣ ሰዓት ዕላፊ በታወጀባት ደሴ ኹለት ሰዓት አልፎ የገባው ተጓጓዥ ዕቃውን ራሱ ተሸክሞ ወደሚያርፍበት ለመጓዝ ተገዶ ነበር። ምግብ ቤቶችም ተዘግተው ስለነበር አልጋ ፈልጎ ከሚያድረው ምን ያህሉ ጾሙን እንዳደረ ማወቅ አይቻልም።

400 ብር ገደማ በሚከፈልባቸው ዘመናዊ አውቶቡሶች በግማሽ ቀን ይገባ የነበረው ተጓጓዥ፣ ትኬት አገኛለሁ ብሎ የእነሱን ቆርጦ ባለማደሩ ከእነሱ ዋጋ በላይ ከፍሎ ለሙሉ ቀን ለእንግልት ተዳርጎ ውሏል። ሕብረተሰቡ መንግሥትን ተማምኖ ሌሊት ቢወጣም፣ እንዳሰበው ሳይሆን ቀርቶ ለከፍተኛ ወጪ ተዳርጓል። “መኪና የለም፤ ፍተሻ ይበዛል” በሚል ምክንያት ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ ጥቅማቸውን በማስቀደም ሕዝብን የሚያማርሩት ላይ በተመሳሳይ ዕርምጃ መውሰድ ግድ ይላል። አንድ ቀን እንኳን በአገር አቋራጭ ተሸከርካሪ ተጉዞ የሚያውቅን ብናነጋግር፣ ምን ያህል ሒደቱ እንደሚያማርር መገንዘብ አያዳግትም።

በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት ዕጥረት መፈጠሩ ወይም ፍተሻ መብዛቱን ማማረር ባይቻልም፣ ሒደቱን ተጠቅመው ሕዝብን የሚጎዱ ሥራቸው ከጠላት ተግባር ተለይቶ መታየት የለበትም። ሰው አማራጭ የሚያጣበትን ወቅት ተጠቅመው ብቻ ሳይሆን፣ አማራጭ እንዲያጣ አድርገው በጥቅም ተሳስረው የሚያንከራትቱና የሚያደኸዩ ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ሊታሰብብት እንደሚገባ የማይናገር ተጓዥ አለ ማለት አይቻልም። ለምዶት የተባለውን እሺ እያለ የሚኖረውን ያህል፣ ለአላስፈላጊ ግጭትና ችግር የሚዳረገውም ብዙ ነው።
በአንድ ቀኑ ጉዞ ከቆምንባቸው 23 ኬላዎችና ጊዜያዊ የፍተሻ ጣቢያዎች ዘጠኙ በወታደራዊ ታጣቂዎች የተደረጉ ፍተሻዎች ናቸው። ቦታዎቹን ዘርዝረን በማስታወሻ ብንይዛቸውም ለደኅንነታቸውም ሆነ ዓላማቸውን እንዳያሳኩ ዕንቅፋት እንዳንሆን ስንል ለእናንተ ይፋ አናደርጋቸውም። ነገር ግን፣ የአማራና ኦሮሚያ ክልል ግዛቶች በሚፈራረቁባቸው መሬቶች ተደጋጋሚ ፍተሻዎች ይስተዋላሉ። መውጫና መገንጠያ ባሉባቸው ቦታዎች የተለመደ ሲሆን፣ አንዳንዶች ያለፈው ላይ ወርደን ተፈትሸናል ሲባሉ በጅምላ አይተው የሚያሳልፉም አሉ። መልክ እየመረጡ ፀጉረ ልውጥ የመሰሉዋቸውን ብቻ መታወቂያ እየጠየቁ የሚያሳልፉም ነበሩ።

ጦር ግንባር አቅራቢያ ያሉ ፍተሻዎች
ከደሴ ከተማ ሰሜን ምስራቅም ሆነ በስተሰሜን ምዕራብ ባሉ ለጦር ግንባር ቅርብ በሆኑ ቦታዎች አዲስ ማለዳ በተለያዩ ቀናት በመጓዝ ሁኔታውን አስተውላለች። ፍተሻው የሚጠናባቸው ቦታዎች የመኖራቸውን ያህል፣ ወጣቱ በየቦታው ያደርገው የነበረው ፍተሻ አሰልቺ ስለነበር እንዲቀር በመደረጉ መሻሻሉን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በአፋሯ ጭፍራ ከተማ አድርጎ አማራ ክልል ውስጥ ወደምትገኘው ሶዶማ ግዛት በተደረገ ጉዞ ድሬሮቃ ከተማ እስክንደርስ በርካታ ፍተሻዎችን አሳልፈናል። የዕርዳታ እህልና ቁሳቁስ በጫነ መኪና እንደመሳፈራችን፣ “ድጋፍ ሰጪ” ነን በሚል ብዙዎቹን ፍተሻዎች ያለምንም መስተጓጎል አልፈናል። ብቅ ብሎ የተጫነውን ያዩ ጥቂቶች ሲሆኑ፣ “ማለፊያ ወረቀቱስ” ብለው የጠየቁ አንድ ቦታ ላይ የነበሩ ፈታሾች ናቸው። ወረቀቱ ቀድሞ ያለፈ አብሮ ተጓዥ መኪና ጋር እንደሆነ ተነግሯቸው የመኪናውን አይነት ለማጣራት ጠይቀው አሳልፈዋል።

ይህን ከመሰለ ማጣራት ውጭ ዕቃው ምን እንደሆነም ይሁን ለማን እንደሆነ ቢሮክራሲ የበዛበት ማጣራት ሳይደረግ በቶሎ ለመድረስ ተችሏል። በደረስንበት የጦር ሰፈር መጓጓዣ አጥተው ረጅም ርቀት ከካምፕ ካምፕ በእግር የሚጓዙ ወታደሮችን አይተናል። አንዳንዶቹ እየለመኑ በመሳፈር የፈለጉበት ድረስ ተጉዘው ይወርዳሉ። አንዲት አብራን የተጓዘች ወታደር ጋር ባደረግነው ቆይታ፣ ለደህንነታቸው ሲባል ስልካቸውን እንዳይጠቀሙ ቢደረግም፣ ሕዝብ መሀል በመሆናቸው በየቀኑ የፈለጉበት መደወል እንደሚችሉ ነግራናለች።

ከጦር ግንባሩ በስተኋላ የሚመጡ ተሸከርካሪዎች በሙሉ እንደሚፈተሹ እኛም የተመለከትን ቢሆንም፣ በእግር የሚመጡ አህያና ግመልን በመሳሰሉ የጋማ ከብቶች ዕቃ ጭነው የሚያጓጉዙ እንደልባቸው እንደሚንቀሳቀሱ አስተውለናል። ከጦር ግንባሩ ፊትለፊት ማለትም በባላጋራ ከተያዘ ቀጠና የሚመጡ ግን እግረኛም ቢሆኑ ይፈተሻሉ። ዕቃ የያዘም ሆነ ያልያዘ ማንኛውም ሰው እንደሚፈተሸ የሞት መሬቱን አቋርጠው ከመጡ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ለማወቅ ችለናል። ልንነግራችሁ የማንችልን አካል በመፈተሽ ተዋጊ የነበረ ምንም ሳይዝ መልመላውን ቢመጣ እንኳን መለየት እንደሚቻል ፍተሻው ከተደረገላቸው ግለሰቦች ለመስማት ችለናል።

ከጦር ግንባር ራቅ ራቅ ብለው የሰፈሩ ወታደሮች፣ እንዲሁም በተወሰኑ ቦታዎች የተጠመዱ ከባድ መሣሪያዎችን መንገደኛው በቀላሉ ማየት ይችላል። ስልክ ሊሠራ በሚችልባቸው አካባቢዎች ያሉበትን ትክክለኛ ቦታ (ኮኦርዲኔታቸውን) ማወቅ እየተቻለ ለመሸፈን ጥረት አለመደረጉ ይገርማል። ከአንድ የመድፍ አፈሙዝ ወደሌላው በተወጠረ ገመድ ላይ የተንጠለጠለ ቋንጣ ማየት መሣሪያዎቹ አገልግሎት መስጠት ካቋረጡ ምን ያህል እንደሆናቸው ያመላክታል። በወቅቱ ውጊያ ባይኖርም የጦርነት ወቅት ላይ እንደመሆኑ ወታደሩ ስንቁን እያዘጋጀ ለመሆኑ አመላካች ነበር።

በእንዲህ አይነት መንገዶች ለቀናት ከቆየው ምልከታ በኋላ ወደ አዲስ አበባ የነበረው የመልስ ጉዞ የተለየ ነበር። የፍተሻው ብዛት አነስተኛ ከመሆኑም በላይ ያን ያህል ጠንካራ አልነበረም። ወደ አዲስ አበባ በተጠጋን ቁጥር ብዛቱ ቢጨምርም፣ በአንድ ቦታ የአንድ መንገደኛ ሰው ዕቃ ከመፈተሹ ውጭ ያን ያህል የሚያዘገይ ተደጋጋሚ ፍተሻ አልተደረገም። በአንድ ፍተሻ ጣቢያ ፖሊሱ ጭነት መኪና ላይ መውጣት ሰልችቶት ጠጠር እየወረወረ ብረት ላይ ለማረፉ ድምፅ በመስማት ጥቂት የጭነት መኪኖችን ሲያሳልፍ በቆምንበት አጋጣሚ ለማስተዋል ችለናል።

ከነበሩት ፍተሸዎች አስገራሚ የነበረው አዲስ አበባ ስንቃረብ በኦሮሚያ ልዩ ኃይል አባል የተደረገ ፍተሻ ዓላማ ነው። ከፊት ለፊታችን እንዲቆም ከተደረገ ፒካፕ መኪና ዳሽ ቦርድ ላይ ለብሶ የነበረን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሠንደቅ አላማን ጎትቶ በመውሰድ፣ የሆነ ነገር ከተናገረ በኋላ ያለ ሌላ ፍተሻ ተሸከርካሪው እንዲያልፍ አድርጓል። ነጥቆ የወሰደውን ሠንደቅ አላማ ሌሎች ከነጠቃቸው ተመሳሳይ ባንዲራዎች ጋር በማድረግ ዛፍ ላይ ሠቅሎ ተመልሷል። ይህ አይነት ተግባር የፍተሻውን ዓላማ ከመቀየሩ በላይ ሌላ ስሜትን የሚፈጥር ነው። ድርጊቱ የነበርንበት አውቶብስ ውስጥ የፈጠረውን ስሜት በቦታው የነበረ ብቻ ሊረዳው የሚችል ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 154 ጥቅምት 6 2014
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here