በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያን ወረዳ 70 ሰዎች በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች መታገታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።
የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደገለጹት ከሆነ፣ “የኦነግ ሸኔ ተላላኪዎች” ናቸው ያሏቸው አካላት በጊዳ አያና ወረዳ አንገር ጉተን ከተማ ነዋሪዎችን “ዕርዳታ ልትሰጡ ነው” ብለው ሰብስበው ወደ መኪና ካስገቧቸው በኋላ እንዳገቷቸው ገልጸዋል።
ባሳለፍነው ጥቅምት 15/2014 መነሻቸውን አንገር ጉትን አድርገው ወደ ነቀምት ሲጓዙ የነበሩት ኹለቱ አውቶብሶች፣ በታጣቂዎቹ አማካይነት ውኬ ልጎ መገንጠያ ላይ መታገታቸውን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል። እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት በተፈረጀው ኦነግ ሸኔ የታገቱ ተሳፋሪዎች በመኪኖቹ ውስጥ እንዳሉ ወሮ አለልቱ ተብሎ ወደሚጠራው ቦታ ተወስደዋል።
ሽብርተኛ በተባለው የሸኔ ታጣቂዎች ታገቱ የተባሉት ነዋሪዎቹ፣ በኹለት የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ተሳፍረው የነበሩ ሕጻናትና ሴቶች፣ እንዲሁም ሽማግሌዎችን ጨምሮ በቁጥር 70 መሆናቸው ተመላክቷል።
ከታገቱት ሰዎች መካከል የተወሰኑትን ለማወቅ የተቻለ ሲሆን፣ ከእነሱም መካከል አለምነሽ አማረ የተባለች ሴት የስምንት ወር እና የኹለት ዓመት ከስምንት ወር ሕፃን ልጆቿ ጋር እንደታገተች ማረጋገጣቸውን የአካባቢው ነዋሪ ተናግረዋል። ሙሉ የኔሁን፣ ብርቴ የኔሁን፣ አማረ ፍቃዱ፣ አዝመራ አለልኝ እና ሌሌችም የጉትን ከተማ ነዋሪዎች መታገታቸውንና ያሉበትን ኹኔታ አለመታወቁን ነው ለአዲስ ማለዳ የተገለጸው።
ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስም የታገቱት ሰዎች በምን ኹኔታ ላይ እንዳሉ ማወቅ አለመቻላቸውን ነው ነዋሪዎቹ የገለጹት። “የታገቱት ሰዎች መመለስ ያጠራጥረናል” የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ ከዚህ በፊት በታጣቂዎቹ ታግተው የነበሩ ሰዎች በሕይወት መመለስ አለመቻላቸውንም አስታውሰዋል።
ነዋሪዎቹ እንደሚሉት፣ የመከላከያ ሠራዊቱ ዕርዳታ እንዲያደርግ ሲጠየቅ “ከመንግሥት ፈቃድ አልተሰጠንም” የሚል ምላሽ ከመስጠት ውጭ የወሰደው ዕርምጃ የለም ተብሏል። ከቤታቸው ወጥተው ወደ አጎራባች አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች “ስለ ታገቱት ሰዎች ኹኔታ ከከተማው ከንቲባ ምላሽ ስናጣ ወደ ፖሊስ አዛዦች ሔደን ዕርዳታ ብንጠይቅም፣ መፍትሔ ሊሰጡን ፈቃደኞች አልሆኑም” ሲሉ ነው የተናገሩት።
የአንገር ጉትን ነዋሪዎች ካሁን በፊት በሸኔ ታጣቂዎች ጥቃት እየደረሰባቸው መሆኑን እያመላከቱ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ የአሁኑ እገታ ከመደረጉ ቀድም ብሎ ነዋሪዎቹ ለሚመለከታቸው አካላት ኹሉ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ቢጠይቁም የተሠራ ሥራ ባለመኖሩ ችግሩ መፈጠሩን ጠቁመዋል።
ከታገቱት ተሳፋሪዎቹ ጋር የነበሩ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የአንገር ጉትን መንደር 10 የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች መለቀቃቸውን ነዋሪዎቹ የገለጹ ሲሆን፣ ተመርጠው የቀሩት የአማራ ተወላጆች እንዴት እንደሆኑ አልታወቀም ብለዋል።
የአዲስ ማለዳ ምንጮች አያይዘውም፣ የሚመለከተው አካል ለታገቱት ሰዎች ይደርስላቸው ዘንድ በተስፋ እየጠበቁ መሆናቸውን ገልጸው፣ ለታገቱት መንግሥት ይድረስላቸው ሲሉ አሳስበዋል።
አዲስ ማለዳ ስለጉዳዩ ምላሽ ለማግኘት ወደ አንገር ጉትን የፖሊስ አዛዥ ሻምበል ኩምሳ መኮንን የደወለች ሲሆን፣ አዛዡ “ምንም አልተፈጠረም” በማለት ስልካቸውን ዘግተዋል። በተደጋጋሚ ሲደወልላቸው ስልካቸውን በመዝጋታቸው የአዲስ ማለዳ ተጨማሪ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።
አዲስ ማለዳ በምስራቅ ወለጋ ዞን በጊዳ አያና ወረዳ ሦስት አርሶ አደሮች፣ በኪራሙ ወረዳ ቃና ውልማይ ቀበሌ ከ50 በላይ ንጹኃን ዜጎች፣ እንዲሁም በዚሁ ወረዳ አዲስ አለም ከተማ ውስጥ 60 ንጹኃን ነዋሪዎች ሽብርተኛ በተባለው የሸኔ ታጣቂ እንደተገደሉ ስትዘግብ መቆየቷ ይታወሳል።
ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014



