ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው የውጭ የትምህርት ዕድል እንድታገኙ እናደርጋለን የሚሉ አካላት በአዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣቱንና ወጣቶችን በማታለል ከፍ ያለ ገንዘብ እያጭበረብሩ መሆኑን ቅሬታ አቅራቢዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ድርጅቶቹ ራሳቸውን ኤጀንሲ ብለው እንደሚጠሩም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በከተማዋ በተለይም ደግሞ ቦሌ አካባቢ ይህን ዓይነት ድርጊት የሚፈጽሙ ሕገ ወጥ ኤጀንሲዎች በስፋት ይገኛሉ ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ በሚሠሩት ድርጊትና በሚናገሩት ከእውነት የራቀ ንግግር ወጣቱን በማታለል ብዙ ብር እንደሚቀበሉ ነው የጠቆሙት። በዚህም የውጭ ትምህርት ሒደቱን ለማስጀመሪያ በሚል እስከ ሠላሳ ሺሕ ብር የሚቀበሉ ሲሆን፣ ገንዘቡን ከተቀበሉ በኋላም አድራሻቸውን እንደሚያጠፉ ነው የተገለጸው።
ሌሎች ሕገ ወጥ ኤጀንሲዎችም እንዲሁ፣ አመልካቾችን ውጭ አገር ከሚገኝ የትምህርት ተቋም ተቀባይነት አግኝታችኋል፣ ለዚህም የሚሆን በማለት እስከ መቶ ሺሕ ብር የሚደርስ ገንዘብ አምጡ ብለው ከተቀበሉ በኋላ ደብዛቸው እንደሚጠፋ በቅሬታ አቅራቢዎች ተመላክቷል።
የብቃት ማረጋገጫም ሆነ ሕጋዊነት ሳይኖራቸው እንዲህ ዓይነት ተግባር በመፈጸም ከሕዝቡ ገንዘብ የሚያጭበርብሩ ግለሰቦች እና ሕገ ወጥ ተቋማት በመብዛታቸው ዕርምጃ ካልተወሰደበት ሌሎችም በዚህ ተግባር ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ ወስብስብ ችግሮችን ይፈጥራልም ብለዋል፡፡
በውጭ አገር ነጻ የትምህርት ዕድል (scholarship) ማግኘት የሚፈልጉ ዜጎች የትምህርት ዕድሉን እንዲያገኙ የሚሠሩ ሕጋዊ ኤጀንሲዎች ላይም ተመሳሳይ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ተገልጿል፡፡
ስሜ እንዳይጠቀስ ያለችና በዚህ ዘርፍ ሕጋዊ ሆኖ በሚሠራ አንድ ኤጀንሲ ውስጥ ሠራተኛ የሆነች ወጣት ለአዲስ ማለዳ በሰጠችው አስተያየት፣ በሕገ ወጥ አካላት 20 እና 30 ሺሕ ብር የተጭበረበሩ ብዙ ወጣቶች እኛ ጋር ይመጣሉ ስትል ገልጻለች፡፡ በዚህም በሌሎች ያደረባቸውን ክህደት በመፍራት እኛንም ለማመን ስለሚቸገሩ ማረጋጋጫችን እና ፈቃዳችንን እንዲመለከቱት ፊት ለፊት እናስቀምጣለን። በእኛ ኤጀንሲ ውጭ አገር ሔደው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ያሉ ሰዎች ጋርም ለማገኛኘት ሙከራ እናደርጋለን ነው ያለችው፡፡ ይህም የሆነው በከተማዋ በዚህ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ገንዝብ የሚያጭበርብሩ አካላት በመብዛታቸው መሆኑን ገልጻለች፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ዳንኤል ሚልኬሳ በጉዳዩ ላይ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት ሃሳብ፣ ችግሩን እርሳቸውም ሲወራ ከመስማት በዘለለ እንደማያውቁት ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ግን፣ እንደዚህ ዓይነት ሥራ ላይ የተሠማሩ አካላት በመጀመሪያ ዘርፉን ከሚመለከት ተቋም የሙያ ብቃት ማረጋገጫ መውሰድ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ ለምሳሌ፣ ጤና ላይ የሚሠማሩ አካላት ከጤና ሚኒስቴር የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ቅድሚያ እንደሚወስዱት ሁሉ፣ ትምህርት ላይ የሚሠማሩም ከሆነ ከትምህርት ሚኒስቴር ወይም ከትምህርት ቢሮ ሊሆን ይችላል የብቃት ማረጋገጫውን መውሰድ አለባቸው ነው ያሉት፡፡ በዚህ መንገድ መስመሩን ተከትለው የመጡ አካላትን ወደ ክፍለ ከተሞች በመምራት በወረዳ ሕጋዊ የንግድ ፈቃድ እንዲያገኙ ይደረጋል ሲሉም ጠቁመዋል፡፡
አያይዘውም፣ አሁን ላይ በከተማችን ውጭ አገር የመማር ፍላጎት ላላቸው ውጭ ሔደው እንዲማሩ በማመቻቸት ላይ ተሠማርተው የሚሠሩ አካላት ፈቃድ ሊኖራቸውም ላይኖራቸውም ይችላል፡፡ ፈቃድ እንደሌላቸው እና እንደሚያጭበረብሩ ጥቆማ ከደረሰን ግን አጣርተን እንዲዘጉና ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ እንችላለን በማለት ገልጸዋል፡፡
አዲስ ማለዳ በዚህ ጉዳይ ላይ ለትምህርት ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርባ፣ በትምህርት ስም እንደዚህ አይነት ሕገ ወጥ የድለላ ተግባር የሚሠሩ አካላትን የመቆጣጠር ኃላፊነት የፖሊስ ነው የሚል ምላሽ እግኝታለች፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ብሎም በከተማዋ ያለውን ከፍተኛ የሥራ አጥ ቁጥር ተከትሎ፣ ሥራ እናስቀጥራችኋለን፣ ወደ ውጭ እንድትሄዱ እናደርጋለን እንዲሁም የተለያዩ የውጭ ትምህርት ዕድሎችን እናመቻቻለን የሚሉ ግለሰቦች እና ሕገ ወጥ ተቋማት ከመብዛታቸውም በላይ፣ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያጭበረብሩ በማኅበረሰቡ ዘንድ በተደጋጋሚ የሚገለጽ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014



