መንገድ መነሻና መድረሻ ያለው ዓላማው የሚታወቅ መንቀሳቀሻ ነው። ማንኛውም ነገር መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ እንዳለው ኹሉ ከአጀማመሩ መንገዱ የተስተካከለ ካልሆነ መዳረሻው ጋር እንደማይደረስ ይታወቃል። ቦታው መድረስ የማይቀር ቢሆን እንኳን፣ አንዳንድ ነገሮች በወቅቱ ካልተከናወኑ መዘግየታቸው እንዳልተከናወኑ ያደርጋቸዋል።
በአገራችን የተከሰተው ጦርነት አንድ ዓመት ቢያስቆጥርም ግቡን መች እንደሚመታም ሆነ በምን መንገድ እንደሚያልቅ ሳይታወቅ ብዙዎችን እያሳሰበ ይገኛል። የጦርነት ዓላማ አሸንፎ ፍላጎትን ማሳካት ቢሆንም፣ ይህ ግን በሕዝብ ዘንድና በመንግሥት በኩል ተመሳሳይ ላይሆን ይችላል። የሕዝብ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ማንኛውም የመንግሥት ተግባር በወቅቱና በሚፈለገው መንገድ መከናወን እንደሚገባው አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።
ጦርነቱ የተጀመረበት ምክንያት ከሞላ ጎደል ቢታወቅም፣ እስካሁን ያልተፈጸመበትንና ውጊያው አብቅቶ ወደ ነበርንበት በቶሎ መመለስ ያልተቻለበትን ምክንያት ሕዝብ እንዲያውቅ አልተደረገም። በውጊያ መሀል ላይ እውነተኛ ምክንያቱን መናገር ለተፋላሚው ወገን ይጠቅማል ተብሎ ሊሆን ቢችልም፣ የደጋፊን ትዕግስት እንዳያስጨርስ ቢያንስ ምክንያቱ ቢነገር መልካም ነው።
በ15 ቀን ተጠናቀቀ ሲባል የነበረው ውጊያ እንደተባለው ሳይሆን ቢቀርም ሕዝብ አለማኩረፉ ይታወቃል። ጦርነቱ አማራና አፋር ክልል ገብቶ ከፍተኛ ዕልቂትና ውድመት ከተከሰተ በኋላም፣ በአጭር ጊዜ ዋና ከተማ በመግባት ሁሉን እንቆጣጠራለን እየተባለ በድጋሚ የሕዝብ ተስፋ እንዲያንሠራራ ቢደረግም፣ አሁን ድረስ ለውጥ ሳይሰማ መከራውም ሆነ ዕልቂቱ ቀጥሏል።
የሕዝብ ርብርብ እንዲደረግ በተደጋጋሚ እየተጠየቀ፣ በጎ ምላሽ ተሰጥቶ ወታደራዊ የበላይነት ሲያዝ የተጀመረው እንቅስቃሴ ስለሚቋረጥ መልሶ ለመጠቃት በር መክፈቱ በተደጋጋሚ ታይቷል። ሕዝብ እንዲዘናጋ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ “ሰላም ነው” የሚል ወሬ ሲሆን፣ ጥቃቅን የድል ወሬዎች፣ እንዲሁም ጠላትን መናቅና “ሆ” ተብሎ ዕርምጃ እንዳይወሰድ የሚያደርግ ሐሳብ በዋናነት ይጠቀሳል። “ጠላት ብዙ ሆኖ መጥቷል” ማለት በአንድ በኩል እውነታን ማሳወቅ ቢሆንም፣ ትንሽ ነን ብሎ የሚያስብን ሊያሸብር እንደሚችል መገንዘብ እንደሚስፈልግ አዲስ ማለዳ ታመላክታለች።
በሌላ በኩል፣ በጦር ሜዳ ተማረከ እያሉ በውጊያ ወቅት የጦር መሳሪያ ደርድሮ ከማሳየት የሚዋጋበት አጥቶ ለተቀመጠ በማስታጠቅ እንዲሳተፍ ማድረጉ ሳይሻል አይቀርም የሚሉ በርካታ አስተያየቶች ሲሰጡ ይሰማል። እንዲህ አይነት የሕዝብ አስተያየትን እያሰናዳ ለሚመለከተው አካል እንዲደርስ የሚያደርግ ራሱን የቻለ ኃይል ያስፈልጋልም የሚሉ አሉ።
የጦርነቱ ዓላማ ማሸነፍ እንደመሆኑ የመረጃ አስፈላጊነቱ ላይ በማመን ለጋራ ዓላማ መረባረብን ይጠይቃል። አንድ ዓይነት መዳረሻ ጋር ለመገናኘት ኹሉም በአንድ ዓይነት መንገድ ይጓዝ ባይባልም፣ አንዱ ያንዱን እንዳያረዝምበትም ሆነ እንዳያጠፋበት የሚያናብብ የጋራ ጠቋሚ ያስፈልጋል። በእንዲህ ዓይነት ጉዞ ኹሉን ማሰገደዱ ውጤታማነቱ ዝቅተኛ እንደመሆኑ “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” የሚለውን ብሒል በመከተል ውጤታማ ለመሆን መጣሩ ይበጃል።
እህል ያለ ዘሪ “ወፍ ዘራሽ” ቢባልም፣ አፍርቶ ከተገኘ ተመጋቢን አያጣም። እህልን የሚዘራ የሚዘራበትን ቦታ ቀድሞ ማወቅ፣ ማለስለስና ወቅቱን ጠብቆ መዝራት ይጠበቅበታል። ምቹ ቦታን ሳይዝ የሚዘራ፣ ለዘሪውም ሆነ ለማንም ስለማይሆን ባክኖ መቅረቱ አይቀርም። ወቅቱን ሳይጠብቅ የሚዘራ ገበሬም ቀድሞ ካከናወነ ለአዕዋፋት ሲሳይ ይሆንበትና ከነመሬቱ ባዶውን ይቀራል። ዘግይቶ የዘራም፣ እህሉ ሳያድግ ጫጭቶ ስለሚቀርበት እንደቀደመው አስተካክሎ ለመድገም እንኳን ዕድልን አያገኝም። ለከብቱ የሚሆነው ሊያገን ቢችልም ለእርሱ የሚሆን ግን ባለማግኘቱ ቢያንስ ለአንድ ዓመት መቸገሩ አይቀሬ ይሆናል።
የጦር ገበሬም የሚያሰማራውን ወታደር እንደዘር እህሉ ቀድሞ ጥራቱን ማወቅ ይጠበቅበታል። በችኮላ የማያውቀውን እህል ገበሬ እንደማይዘራው፣ የጦር አዛዥም የሚያዛቸውን ወታደሮች ብቃትና ድክመት ማወቅ ግድ ይለዋል። የሠራዊቱን ክህሎትና ተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን ማወቅ የሚጠበቅበት፣ እንደአርሶደሩ የሚያዋጋበትንም ሆነ የሚያዝበትን መሬት ማወቅ እንዳለበት የአዲስ ማለዳ እምነት ነው።
የጦርነት ውጤት የሚወሰነው በብዙ መንገዶች እንደመሆኑ ኹሉንም አማራጮችንም ሆነ ዕድሎች መዳሰስ ከአንድ የጦር መሪም ሆነ ከበታች አዛዥ ይጠበቃል። ወታደራዊ ሳይንሱን ለባለሙያዎቹ መተው ቢገባም፣ እንደሕዝብ የሚታዩ መዘናጋቶችንም ሆነ ክፍተቶችን ከመጠቆም ልንታቀብ አይገባም። ከዚህ ጉዳይ ጋር በተገናኘ በጦር ሜዳ አካባቢ ስለመተላለፊያ ቀዳዳዎች የሚነገሩ ያልጠሩ ቅሬታዎች አሉ።
ተዋጊዎች ግድ መደበኛ መንገድን ተከትለው ፊት ለፊት መጋፈጥ እንደማይጠበቅባቸው ይታወቃል። አንዱ የዘጋውን በር ሌላው ለማስከፈት የግድ ያንኑ መስመር ተከትሎ እንደማይመጣ ሊታወቅ ይገባል። መደበኛ ጦር ከሚሰፍርባቸው መንገዶች ይልቅ ድንገተኛነትን ለመውሰድ የሚፈልግ አካል የእረኛ መንገዶችን፣ እንዲሁም ከነዋሪው በስተቀር ማንም የማያውቃቸውን መሿለኪያዎችን እንደሚጠቀም ግልጽ ነው። እንዲህ አይነት መተላለፊያዎች ቆረጣ ለሚባለው የውጊያ ስልት ትልቅ አስተዋጽዖ ስላላቸው ይበልጥ ሊታሰብባቸው እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።
ሠሞኑን በደሴ ዙሪያ በተለይ ከውጫሌ ወደ ቦሩ ሜዳ ከሚያስገባ ፒስታ መንገድ ተነስቶ ከኩታበር አድርጎ የመጣው ጋር ተቀላቅሎ ቀጥታ የመኪና መንገዱን ተከትሎ ይመጣል ተብሎ የነበረ ጦር ያልተገመተ አቅጣጫን እንደተጠቀመ ይነገራል። በታሪካዊው መሆነኛ ተራራ በኩል በማሳበር በሩጋ አድርጎ ከጦሳ ተራራ በስተጀርባ በመዝለቅ ከደሴ በስተምዕራብ ለመግባት ታስቦ ነበር። ይህም ተትቶ ጦሳን በመዞር ታቹን በገራዶ አድርጎ ወደ ደሴ ከደቡብ ምዕራብ በኩል ለማጥቃት ታስቦ ነበር። እንደታሰበው ሳይሆን ሩጋ ጋራው ላይ ተደርሶ የአንድ ቀን ፍልሚያ ከተደረገ በኋላ ሾልኮ የገባው ጦር ወደኋላ እንዲያፈገፍግ መደረጉን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። ይህ የሚያሳየው የቦታውን ኹሉንም መግቢያና መውጫ የሚያውቅ ወይም የሚመራ የአካባቢው ተወላጅ በቅርብ እንደሌለ ነው።
ጦርነት የተፋላሚ ወገን እንቅስቃሴን አስቀድሞ ማወቅን ይጠይቃል። አንድ የጦር መሪ ቼዝ የሚባለውን ጨዋታ ማወቅ ይጠበቅበታል የሚባለው፣ ሌላኛው ወገን ምን ሊያደርግ እንደሚችል ኹሉንም አማራጮች አስቀድሞ በመገምገም ዝቅተኛ ጉዳት የሚያስከትልበትንና ከፍተና ኪሳራ በተፋላሚው ላይ የሚያደርስበትን ዕርምጃ ቀድሞ ሲወስን በመሆኑ ነው። “እንዲህ ባደርግ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ” ብሎ ማሰብ ብቻ ሳይሆን፣ ምንም ባላደርግ ምን ይሆናሉ ብሎ የእሱንም ወገንም ሆነ የተፋላሚውን ውሳኔ ከባህሪው ጋር በማቀናጀት መገመት ይጠበቅበታል።
የሥነልቦና ባለሙያዎች እንደሚናገሩትም፣ የተቃራኒ ወገን መሪም ሆነ የበታቹ ምን አይነት ጠባይ እንዳለው መረዳት ጥቅም ይኖረዋል። የሰላይ ሥራም ወታደራዊ ቦታዎችንና ምስጢሮችን መውሰድ ብቻ ሳይሆን፣ የአመለካከት ኹኔታንም መገምገም ነው። ንዴቱን የማያሳይ ሰው ማናደጃ ቅጽል ስም እንደማይወጣለት ኹሉ፣ እንደግስላ እያናደዱ ራሱን እንዲያጠፋም ሆነ አስቦ እንዳይመታ ለማድረግም ስስ ብልትን መረዳት እንደሚያስፈልግ ይታመናል።
ጦርነቱ ለረጅም ጊዜ ሳይጠናቀቅ እንዲዘገይ የተደረገው ይህን መሰል ዝግጅት ለማድረግ ነው ቢባልም፣ አሁንም ሰው እያለቀ ውጤቱን ማየት አልተቻለም። ማማሟቂያ ነው እየተባለ፣ ሕይወቱ መፈተሻ እንደሆነ እንዲሰማው የሚያደርገው ይህ አገላለጽ ተገቢ ስላልሆነ ዕርማት እንዲደረግ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።
የትኛውም ነፍስ እኩል ክቡር እንደመሆኑ መሳለቂያ መሆን የለበትም። ከየትኛውም ወገን ቢሆን የተማረከም ሆነ የተሰዋ ሰው አስከሬንን በማሳየት የሚገኝ ትርፍ የለም። መላው ዓለም ስለእኛ ያለው አመለካከት ከተቀየረ የምንጎዳው ኹላችንም እንደመሆናችን፣ ጠላታችንም ቢሆን ሰው እንደመሆኑ ሰብዓዊ እንከብካቤ ልናደርግለት ይገባል። ለአስከሬንም ቢሆን አባቶቻችን ጥንት እርስ በርስ ከተዋጉ በኋላ እንደሚያደርጉት ክብር ልንሰጥ ይገባል። ትውልድ ላይ ተቀርፆ የሚቀርን ግፍ አስከሬንም ላይ ቢሆን መፈጸሙ ለምንፈልገው መዳረሻ እንቅፋት ስለሚሆነን አስቀድመን ብናስብበት መልካም ነው።
ኹለት እግር አለኝ ተብሎ ኹለት ዛፍ ላይ እንደማይወጣው፣ መንግሥት ነኝ ተብሎም ሆነ የሕዝብ ነጻነት ታጋይ ነኝ በሚል ሥም የሚደረግ ሕሊና ቢስ ተግባር ወደ ራስ መምጣቱ አይቀርም። አፍን የሚያሲዝ ዜና ጠብቁ ተብሎ፣ ሕዝብን በጅምላ እንደሚጨርስ ዕርምጃ መኩራራት ተገቢ አይሆንም። የበፊት አባቶች ከኹሉም ወገን ሰው በብዛት ሳያልቅ ጦርነት እንዲቋጭ ይጥሩ ነበር። አሁን ግን በግዳይ መኩራራት ብቻ ሳይሆን መታበይም ይታያል። መመካት ኹሉን በፈጠረ አምላክ ብቻ መሆን ሲኖርበት፣ በትጥቁም ሆነ በሠራዊቱ ብዛትና ጥራት መሆኑ ማብቃት እንዳለበት አዲስ ማለዳ ታምናለች።
ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014



