በደሴ ከተማ ለተፈናቃዮች የሚሰጥ የዕርዳታ ክፍፍል ፍትሃዊ አይደለም ተባለ

0
1025

ከተለያዩ የሰሜን ወሎ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ለሚገኙ ሰዎች የሚሠጠው ዕርዳታ ክፍፍሉ ኢ-ፍትሃዊ መሆኑን በበቦታው ያሉ ተረጂዎች ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
አዲስ ማለዳ በቦታው ሆነው መረጃ ካቀበሏት ሰዎች እንደተረዳችው ከሆነ፣ በሕጉ መሠረት ድጋፉ የሚሰጠው በምዝገባ ሲሆን፣ ዕርዳታውን ለማግኘት ተፈናቅሎ የመጣ እያንዳንዱ ግለሰብ በአካል ተገኝቶ መመዝገብ አለበት።

ከዚህም በተጨማሪ ድጋፉ በሚደረግበት ወቅት የተመዘገበው ግለሰብ በአካል ተገኝቶ ድርሻውን መውሰድ የሚጠበቅበት ሲሆን፣ እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው መሆኑን ከተለያዩ የሰሜኑ አካባቢዎቸ መጥተው በደሴ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
የዕርዳታ ክፍፍሉ ኢ-ፍትሃዊ ነው የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ልጅ የሌላቸውና ቤተሰብ የማያስተዳድሩ ግለሰቦች “ቤተሰብ አስተዳዳሪ ነን” በማለት እየተመዘገቡ መሆናቸውን ነው የተገለጹት።

ባሳለፍነው ሳምንት (የጥቅምት ሦስተኛ ሳምንት) በደሴ ከተማ በነበረው የዕርዳታ ክፍፍል ወቅት አድሎአዊ አሠራር እንደነበር የጠቆሙት ተረጅ ግለሰቦቹ፣ የተሰጠው የዱቄት የዓይነት ድጋፍ በትክክል አልተከፋፈለም ሲሉ ነው የተናገሩት።
የዓይነት ክፍፍሉ በብር ሲተመን ለአንድ ሰው 260 ብር የሚደርሰው ሲሆን፤ “የቤተሰብ አባላት አለን” በማለት አንድ ሰው ከራሱ በተጨማሪ የአምስት የስድስት ሰው ድርሻ የወሰድበት አጋጣሚ ነበር ሲሉ ነው ያስተዋሉትን ያብራሩት።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ይህ ኢፍትሃዊ የዕርዳታ ክፍፍል ለመፈጠሩ ዋነኛ ምክንያቱ ተፈናቅለው የመጡትን ሰዎች ለመመዝገብ ከየወረዳው የተመደቡ ሰዎች በዘመድ አዝማድ ስለሚሠሩ ነው ብለዋል።

ለአዲስ ማለዳ መረጃ ካቀበሉት ሰዎች መካከል ኹኔታውን ስትከታተለው የነበረችውና ስሟ እንዳይጠቀስ የጠየቀችው ወጣት፣ አንድ ገና ያልወለደ ወጣት በስድስት ቤተሰብ ተመዝግቦ ሲቀበል አይቻለሁ ብላለች። ወጣቷ አያይዛም የወጣቱ ቤተሰቦችም በራሳቸው ስም ተመዝግበው ተቀብለዋል ስትል ነው የጠቆመችን።

የሚስተዋለው ፍትሃዊ ያልሆነ አሰራር እየተፈጠረ ያለው አንዳንድ መዝጋቢዎች የሚያውቋቸውን ሰዎች በአካል ሳይገኙ ብዙ ቤተሰብ እንዳላቸው አድርገው ስለሚመዘግቧቸው ነው በማለት ነው የገለጸችው።
ወጣቷ በመጨረሻም፣ ምንም እንኳን ከሌሎች አካባቢ የመጡ ተፈናቃዮችን በሚመዘግቡ ኮሚቴዎች በኩል ችግሩ ባይጠፋም፣ ኢ-ፍትሃዊ የዕርዳታ ክፍፍሉ በይበልጥ ያስተዋለችው በቆቦ ከተማ ኮሚቴዎች እንደሆነ ተናግራለች። ዕርዳታው በበጎ አድራጎት የሚሰጥ በመሆኑ፣ ሆን ብሎ የሚከታተል ሰው ባለመኖሩና ወቅቱ ከባድ በመሆኑም፣ እርስ በእርሳችን በመተዛዘን ቢያንስ ለአዛውንቶች እንኳን እገዛ ብናደርግ መልካም ነው በማለት ነው አስተያየቷን የሰጠችው።

ሌላኛው ቅሬታ አቅራቢም ቤተሰቦቹን በጎን አስመዝግቦ እና እራሱ በአምስት ቤተሰብ ተመዝግቦ በክፍፍሉ ወቅት በአካል ሳይገኝ ብር የተላከለት ሰው አውቃለሁ በማለት ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጸው። አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት ይምዝገባ ያካሂዳሉ የተባሉ ኮሚቴዎች ሥራቸውን እንዴት እንደሚያከናውኑ ለማነጋገር ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካላት ቀርቷል።

አዲስ ማለዳ በቀደምት ዕትሞቿ በጦርነቱ ምክንያት ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ተከራይተው የሚኖሩ ሰዎች በመጠለያ ካሉት ጋር ተመሳሳይ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ያቀረቡትን ቅሬታ ስትዘግብ መቆየቷ ይታወሳል።


ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here