ደቻሳ አበበ (ዶ/ር) ይባላሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ማኅበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ የአፍሪካ ጥናትና ምርምር ተቋም የታሪክ ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸውን በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን ለንባብ ያበቁት እኚህ መምህር፣ የታሪክ መጽሐፍም አሳትመው ለተደራሲያን አቅርበዋል፡፡ ከዓመት በፊት ለንባብ የበቃው በራስ ጎበና ፖለቲካዊና ወታደራዊ የሕይወት ታሪክ ላይ የተመሠረተ መጽሐፋቸው የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ነው፡፡ የአዲስ ማለዳው ቢንያም ዓሊ ስለወቅታዊው የምስራቅ አፍሪካ ኹኔታና ስለአገር ውስጥ ክስተቶች ከታሪክ አንጻር፣ እንዲሁም ስለራስ ጎበና ታሪክ የተመለከተ ቆይታ ከእሳቸው ጋር አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ እንደታሪክ ባለሙያ ሳየው አዲስ ነገር የለም። እንደግለሰብ ስመለከተው፣ ኢትዮጵያ በብዙ ወጀቦች ውስጥ አልፋ ነው እዚህ የደረሰችው። አሁን ያለው ዓይነት ውጣውረዶች የነበሩ ናቸው። አሁን በእኛ ጊዜ ያለፈውን ባንደግም ይመረጥ ነበር። እየሆነ ያለው አይተነው ሰምተነው የማናውቅ አይነት ክስተትና ፈተና አይደለም። የሚያሳዝነው ከታሪክ ሳንማር ችግርን መድገማችን ነው።
ኹሌ አንድ የፖለቲካ ሥርዓት እንበለው አሊያም የግለሰብ ሥልጣን ሲያበቃና ወደሌላ ቡድን ወይም ሰው ሥልጣኑ በሚሸጋገርበት ወቅት ይገጥሙ የነበሩ ውጣ ውረዶች የነበሩና ያሉ ናቸው። ሰላማዊ የሆነ የሥልጣን ሽግግርን ማካሄድ ገና የሚቀረን ነገር ነው።
የታሪክ አዙሪት ውስጥ እንደመሆናችን በምስራቅ አፍሪካ ላይ ያለውን የውጭ ተጽዕኖ እንዴት ይገመግሙታል?
በተለምዶ እንደሚነገረው፣ እንዳልቀና ዛር መስመር ያዘ ሲባል በየምክንያቱ ወዲያው ወዲያው ባህሪውን ይቀያይራል። በታሪክ የምናውቃቸው ዓለም አቀፍ ግንኙነትም ይባሉ ሌላም፣ በምስራቅ አፍሪካ ያለው በጣም ተለዋዋጭ ነው። በእርግጥ የማይለወጥ ቋሚ የሆነ አቋም ቢኖርም አብዛኛው ግን በፍጥነት የሚቀያየር ነው። ሊያስጠብቁት የሚፈልጉት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አሉ።
ከቅኝ ግዛት ጀምሮ አሁን ነጻ ወጥታችኋል ከተባለ ወዲህም፣ በየትኛውም የአፍሪካ አካባቢ ማለት ይቻላል፣ የፖለቲካ የበላይነት እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ። የበላይነቱ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እንደሚያስገኝላቸው ስለሚታወቅ ያንን ለማግኘት ምንም ከባድ ቢሆን በማንኛውም መንገድ አስጠብቀው መቆየት ይፈልጋሉ። ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚመጡበት መንገድ ግን በየጊዜው ይለያያል። ይህን መንገድ ደፈንን ስንል በሌላ አቅጣጫ ይመጣሉ። በተለያየ ምክንያት እየተቀያየሩ ቢመጡም ዋና ዓላማቸው ይታወቃል። አንዳንድ ጊዜ በርዕዮተ- ዓለም መቀያየር የሚመጡ ቢኖሩም፣ እንደወቅቱ ራሳቸውን እየለወጡ መምጣታቸው አይቀርም። በፊት ቀዝቃዛው ጦርነት የሚባለው ፈሊጥ በሶሻሊስትና ካፒታሊስት ተለይቶ በነበረ ሽኩቻ እኛን የመሳሰሉ አገራትን ሲደፈጥጡ ነበር። ቀጥሎም ሽብርተኛ የሚል ጽንሰ ሐሳብን በመያዝ እየፈጸሙ ያለውን የምንመለከተው ነው። ሽብርተኛን እንዋጋ እያሉ ሌላ ካርድ ይዘው በመምጣት ሕዝቡ ጎራ ለይቶ እንዲጋደል ያደርጋሉ። እንደምስራቅ አፍሪካ ነዋሪነቴ ታሪካችን የሚያሳየው ይህንን ነው።
ወደ ሱዳን ጉዳይ እንግባና፣ በአገሪቱ እየሆነ ያለው ከታሪክ አንጻር ለኢትዮጵያ ምን የሚፈጥር ይመስሎታል?
እንደታሪክ ተማሪ እኔ የማውቀው፣ የአፍሪካ መፈንቅለ መንግሥቶች ብዙ ጊዜ የሚካሄዱት በወታደሮች ነው። መፈንቅለ መንግሥት ብዙ ጊዜ ከውስጥ ችግር የሚመነጭ ነው። የውስጥ ችግሩ ለአመጽ የለማ መሬትን ስለሚፈጥር የውጭ እጅ እንዲገባ ያመቻቻል። ሕዝቡ ብሶት ስለሚኖርበት ያንን አግዝፈው እየነገሩ ሥልጣን ላይ ያለው አካል በወታደሩ እንዲገለበጥ ያደርጋሉ።
መፈንቅለ መንግሥት የሚያደርጉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ከርቀት የሚመጡ ሰዎች አይደሉም። በአፍሪካ የተለመደው በወታደራዊ መኮንኖች ነው። ይህ የብዙ አፍሪካ አገሮች ልምድ እስከዛሬ ሲሠራበት የነበረ ነው። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከተቋቋመ ጀምሮ ይህን የመሰለ ድርጊትን የሚያግድበት አሠራር አልነበረውም። ወደ ሥልጣን የመጣ ኹሉ አገርን ወክሎ እስከመጣ ድረስ ተቀባይነት ይኖረዋል የሚለው አካሄድ በዛው አልቀጠለም። በተለይ ተቋሙ አፍሪካ ኅብረት ከተባለ ወዲህ ነገሮችን ለመቀየር እየተሠራ ይገኛል። አሁን ሱዳን ላይ እንደተደረገው ከአባልነት እስከማገድ የሚደርስ ዕርምጃ መውሰድ ተጀምሯል።
በሱዳን የተከሰተው ለኢትዮጵያ የሚኖረው አንድምታ ቀጥተኛ ነው የሚሆነው። እነሱ ሠላም ሲሆኑ እኛም ሠላም እንሆናለን። ሠላም ካልሆኑ ችግሩ ወደእኛም ይዛመታል። ይህ በተራ ሰው የሚታወቅ በአባቶች አባባልም የሚታወቅ ነው። ሠላም እስከጎረቤቴ የሚባል ነገር አለ። እንደእኔ እምነት፣ ሱዳን የሚከሰተው ችግር ወደእኛ ሊመጣ ይችላል።
አንዳንዶች እኛ አገር ጦርነት ሲነሳ ሱዳን መሬታችንን እንደመውረሯ፣ አሁን የእነሱ ሠላም አለመሆንን ልንጠቀምበት ይገባል እያሉ ኹኔታውን እንደጥሩ አጋጣሚ የሚያዩት አሉ። በዚህ ላይ ምን አስተያየት አሎት?
ከታሪክ አኳያ ካየነው ብዙ የአፍሪካ ጎረቤታም አገሮች ባለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን ብቻ አንዱ ለሌላው የቤት ሥራ እየሰጠ ነው የኖርነው። የአንድ አገርን የውስጥ ጠላት ጎረቤቶች እያስታጠቁ፣ እንዲያም የተደረገበት አገር በተራው የጎረቤቱን ጠላት እያስተናገደና እያስታጠቀ የአንዱን ውድቀት ሌላው ለማፋጠን ሲሠራ ነው የተኖረው። ጎረቤትን የማዳከም የፖለቲካ አካሄድን ነው ስንከተል የነበረው። ከጎረቤት ኪሳራ ለመጠቀም ነበር የሚሞከረው። ይህ የመደማማት መንገድ እንዳላስኬደ ተምረናል። ጎረቤታማሞች ተያይዘው እንዲወድቁ ስላደረገ የቀውስ ፖለቲካን መላላኩ እንደማያዋጣ ኹሉም ያውቀዋል።
ሱዳን ለእኛ ትሰጠን እንደነበረው ኢትዮጵያም ለሱዳን የቤት ሥራ ትሰጥ ነበር። በታሪክ የተለመደው ይህ ዓይነት ጨዋታ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ያስኬዳል ብለው ፖለቲከኞች አስተያየት ሊሰጡ ይችላሉ። በጋራ አብሮ የማደግን ዓላማ ከግምት ውስጥ ካስገባን ግን አካባቢያችን ሠላም መሆን አለበት።
እኛ ሠላም ብናስብም እነሱ እንደእኛ በጎ ስለማያስቡ የዋህ መሆኑ አያዋጣም የሚሉትንስ ምን ይላሉ?
እኔ እንደታሪክ ሰው የሚገባኝ ከታሪክ መማር እንዳለብን ነው። እነሱ ለእኛ የቤት ሥራ ከሰጡን “እዚህም ቤት እሳት አለ” ብለን እኛስ የማንሰጥበት ምክንያት ምንድን ነው? ብለው የሚያስቡ ይኖራሉ። እነሱ የራሳቸው ካረረባቸው የእኛን ለማማሰል አይችሉም የሚል አስተሳሰብ ሊኖር ይችላል። እነሱ የቤት ሥራቸውን በደንብ መሥራት ባለመቻላቸው ነገሮች ፍርክስክሳቸው ስለወጡባቸው፣ የራሳቸውን ድክመት ለመሸፈን የእኛን ማንኛውንም ተግባር ሊያሳብቡበት ይችላሉ ብሎ ማሰብም ያስፈልጋል። ስለዚህ ጉዳዩ በጥንቃቄ መታየት ያለበት ነው።
ሱዳን ሙሉ በሙሉ ወደ ቀውስ ብታመራ ኢትዮጵያ የቤት ሥራ ሰጥታት ነው ሊባል ይችላል። ይህ የተለመደ አሠራርን የተመረኮዘ ስለሚሆን ታማኝነትንም ስለሚያገኝ ለወደፊት አብሮ ለመሥራት እንድንቸገር ሊያደርገን ይችላል።
ሱዳን ከተፈረካከሰች የተወሰነ የጎሳም ይሁን የኃይማኖት ቡድን ማንም ከልካይ ሳይኖርበት እንደፈለገ ሊያደርግ ይችላል። መቆጣጠር በሚያስቸግር ኹኔታ አደጋዎች ሊበዙብን እንደሚችሉ መገመት ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ አጠቃላይ የሱዳንን ሕዝብ ወክሎ የሚነጋገር ጋር ይሻላል እንጂ፣ ኹሉም ከተበታተነ ለውጭ ተጽዕኖም እንዲጋለጡ በማድረግ እኛው ልንጎዳ እንችላለን ብዮ ነው እንደግለሰብ የማምነው።
በሱዳኖች እየተደገፉ ችግር እንደሚፈጥሩ የሚነገርላቸው በቤኒሻንጉልና በትግራይ ያሉ ታጣቂ ቡድኖች ላይ ለውጡ ተጽዕኖ ይኖረዋል?
እዛ ያለው ቀውስ እዚህ ሊመጣ ይችላል። እዛ ሠላም ቢሆን ከዚህ ሆነን ለመከታተልም ቢሆን ይመቻል። አሁን እንደሚታየው መፈረካከስ የሚታይባቸው ከሆነ ኃላፊነት የሚወስድ አካል አይኖርም። ማንም የፈለገውን ማድረግ ይችላል። ከአንዱ ቡድን ጋር ሲስማሙ ሌላው ሊነሳ ይችላል። በርካታ ታጣቂ ቡድንም ሊፈለፈል ይችላል። አንድ ቀበሌን ማስተዳደር የማይችል ታጣቂ ቡድን፣ “ግድቡ የተሰራበት የኔ ቦታ ነው” ብሎ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ሊጋብዝ ይችላል።
ታሪክን በተመለከተ አንዳንዶች አሁን ላለንበት ውጥንቅጥ፣ የተዛባ የታሪክ ትርክት ምክንያት ሆኗል ብለው ይናገራሉ። ይህን ሐሳብ ይጋራሉ?
ታሪክ ለችግር አስተዋጽዖ አድርጓል ብሎ መናገር ስህተት ነው የሚሆነው። የተዛባ ታሪክ ግን ለግጭት ምክንያት መሆኑ የሚያወሻሽ ነገር የለውም። ያለፈን ክስተት እንደታሪክ ለምንድን ነው የምንማረው ብለን ዓላማውን መረዳት ያስፈልጋል። ይህ ታሪክን በተመለከተ ብቻ አይደለም፣ ኹሉንም ነገር ስንማር ቀድመን ዓላማውን ማወቅ አለብን። እንዲጠቅመን ነው ወይስ ለጥፋት እንዲሆነን ብለን መለየት ይጠበቅብናል። ዓላማው ከታወቀ ትምህርቱ ሲቀረጽም ሆነ ታሪኩ ሲዘጋጅ ከባድ አይሆንም። ታሪክ በሚገባ ከተሰናዳ ለሚፈለግ ዓላማ እየተመዘዘ የሆነ ክፍሉ እንደግብዓት ሊወሰድ ይችላል።
በፖለቲካ ታሪካችን ውስጥ ብዙ ገዳዮች ነበሩ፤ ብዙ ሟቾችም ነበሩ። በታሪክ ኹሉም ማኅበረሰብ ውስጥ ገዳዮችም ሟቾችም አሉ። በዘመኑ ቋንቋ እኔ የወጣሁበት አንድ ብሔረሰብ ገዳይም ነበር ሟችም ነበረ። በዚህ ሒደት ውስጥ ሟቹን ለራሱ ወስዶ መግደሉን ለሌላ አካል ብቻ ሰጥቶ እንዲተረክ ካደረገ፣ መዘዝ ይዞ ይመጣል። ይህ አገር እንዲቀጥል ሞቼም ገድዬም ሚና ነበረኝ ብሎ ማሰብን ይጠይቃል። ስለዚህ የሆነው ኹሉ ለጋራ ዓላማ ነው ተብሎ ነው ተማሪዎችም መማር ያለባቸው። መሬት ላይ ያለው አንጻራዊ እውነታ የሚያሳየው ይህን ነው።
ሰው ለራሱ ዓላማ ብሎ የሚመዛቸው ክስተቶች የምንፈራውን መከራ ይዘው ሊመጡ ይችላሉ። ስለዚህ፣ የትኛውንም ታሪክ ቢሆን ለምን ዓላማ ተጠቀምንበት የሚለው ጥያቄ ነው መነሳት ያለበት።
አንዳንድ የትግራይ ልኂቃን ብቻቸውን አገር ሲያስተዳድሩ እንደነበር ለማሳመን የአክሱምን ሐውልት በመጠቀም ሲቀሰቅሱበት ይሰማል። ይህንን እንዴት ያዩታል?
በአክሱም ዘመን ትግራይ የሚባል ብሔረሰብ ነበር እንዴ? ትግርኛ ተናጋሪ ማኅበረሰብ እንደብሔር አይደለም በአክሱም ዘመን፣ በጣም በጣም ቆይቶ ነው ‹ኢቮልቭ› ያደረገው። እንደዛ ከተባለ ሉሲ የወጣችበት አካባቢ ያለ ማኅበረሰብ እሷ የእኛ ብሔር አባል ናት ሊል ነው ማለት ነው። የትኛው የአክሱም ንጉስ ነው ትግርኛ ይናገር የነበረው? የትኛው የአክሱም ዘመን ላይ ነው ትግርኛ ቋንቋ ጥቅም ላይ ውሎ የሚያውቀው? እንደታሪክ ባለሙያነቴ የትግራይ ማኅበረሰብ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። በፖለቲካ መነሻነት በኋላ ላይ የተፈጠረ ማንነት ነው።
በጆግራፊ አቀማመጥ ምክንያት ከመሀል ፖለቲካ በተራቀ ቁጥር የሚሰማ የባይተዋርነት ስሜት ሊኖር ይችላል። ትግራይ የምንለው አካባቢ የፖለቲካ ማዕከል ነበር። ማዕከልነቱ ወደ ደቡብ ሲመጣ አካባቢው ዳር እየሆነ መጥቷል። ይህ ሲሆን፣ የዳር ማኅበረሰብ ሥነልቦና ይዳብራል። ባይተዋርነትን የሚፈጥረው ይህ ስሜት ሕዝቡን ለውጭ ወራሪዎች የተመቸ ያደርገዋል። በዚህ ምክንያት ለመሀል ፖለቲካው ጠንቅ እየሆነ ይመጣል። ይህ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮችም የሆነ ነው።
እንዲህ አይነት የተዛቡ አተራረኮችን ደፍሮ የሚያርም ስላልነበረ ብዙዎች ተሰናክለዋል ብለው የሚያስቡ መኖራቸውን እንዴት ይገመግሙታል?
ይህን እኔ አልቀበለውም። ትክክለኛ የሚባል ታሪክ ሙሉ በሙሉ ባይኖርም በአንጻራዊነት ግን የተሻለ እንዳለ ይታወቃል። የታሪክ ዓላማው ነው ሁሌም መታየት ያለበት። ኹሉም ስለራሱ ያለውን አመለካከት ማስተካከል አለበት። ከሰው በታች ነኝ ብሎ የሚያስብ ከታሪክ እንደዛ አይነት ትርክቶችን እየመዘዘ ማውጣቱ አይቀርም። ተበድያለሁ ብሎ የሚያስብም ለዛ አስተሳሰቡ የሚሆነውን ታሪክ መፈለጉ አይቀርም። ኢትዮጵያ ረጀም ታሪክ ያላት እንደመሆኗ ማንኛውንም ዓይነት ታሪክ ማግኘት ይቻላል።
የፖለቲካ ሥልጣን በጆኦግራፊ ብቻ ሳይሆን በሌላም ምክንያት ከአንድ ማኅበረሰብ ወደ ሌላው ሊተላለፍ ይችላል። ከአንድ አካባቢ ወይም ጎሳ ብቻ የወጡ አይደሉም በኹሉም ቦታ እየነገሱ የኖሩት። ኹሉም ማኅበረሰብ ለዚህች አገር አስተዋጽዖ እንዳለው ማመን አለበት። ኢትዮጵያ አገሬ ናት ብለው ዕውቅና ለመስጠት የሚተናነቃቸው ወገኖች ሊኖሩ ይችላሉ። ፊትለፊት መናገር ሲከብዳቸው በጎን ዕውቅና መንፈጊያ ብለው የሚመጧቸው ነገሮች አሉ።
በተለይ ከቅኝ ግዛት መጀመሪያ አንስቶ እነዲህ አይነት ያልተወጣናቸውን የቤት ሥራዎች እያነሱ የሚጠቀሙ አሉ። የአገሪቱን የሥልጣን ማዕከልነትን አጣሁ በሚል የተሸናፊነትን ሥነልቦና የሚያዳብሩ አሉ። የባይዋርነትን ሥነልቦና በቀላሉ ለማስወገድ ከባድ ሊሆን ይችላል። ጠቅላይ ሚኒስትር ተሁኖም የባይተዋርነት ስሜት ሊሰማ ይችላል። ከእገሌ ቀጥሎ እገሌ መንገሥ ሲገባው እገሌ ነገሠ የሚሉ አስተሳሰቦች የሚመጡት ከእንዲህ አይነት አመለካከቶች ነው።
ስለመጽሐፍዎ እናንሳና፣ በራስ ጎበና ዳጬ ታሪክ ዙሪያ የሚታዩ ሠፊ ልዩነቶች አሉ። ስለእሳቸው ታሪክ ሲነሳ የሚከሰተው ውዝግብን እንዴት ያዩታል?
ስለራስ ጎበና ያለውን ውዝግብ ፖለቲከኞች ናቸው ያመጡት። በእሳቸው ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ሕይወት ውስጥ ከየትኛውም ማኅበረሰብ ይውጡ ኹሉም ኢትዮጵያዊ የተለየ ነገር የለውም። የእሳቸው ስኬት ብቻ ነው ያለው። ከተራ ቦታ የተነሳ አንድ ሰው ሊደርስበት የሚችለውን ትልቁን ስኬት ደርሰውበታል። በእኔ አመለካከት ከንጉሠ ነገሥቱ ቀጥሎ ያሉ ሰው ነበሩ። አንዳንዶች እኩል ሆነው ቀንበሩን ከንጉሡ እኩል ሊስቡ የሚችሉ ሰው ነበሩ እያሉም ይገልጿቸዋል።
በታሪክ አጋጣሚ ከሆነ አንድ ብሔረሰብ ነው የተወለዱት ተብሎ ስለሚታሰብ የተወሰኑ የአንድ ዘመን ልጆች ማለት የሚቻል የዛ ብሔረሰብ አባላት የፖለቲካ ዓላማ ለማግኘት ብለው ተጠቅመውባቸዋል። ዓላማቸው ልክ ነበር አይደለም የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው። ይህ ዓላማቸውና ጥያቄያቸው በራሳቸው ስህተት ሲወድቅ ሰበብ መፈለግ ነበረባቸው።
በመጽሐፉም የኔ ዋና ዓላማ እኚህ ሰው ለፖለቲካ ወድቀትና ሽንፈት የፖለቲካ የጦስ ዶሮ የሆኑበትን ታሪክ መሞገት ነው ብዬ ነው የጀመርኩት። ራስ ጎበና በዘመናቸው አገር ለመገንባት ያካሄዱት ተግባር አብዛኛው ያለቀው በንግግርና በዲፕሎማሲ ነው። በተለየ የፖለቲካ ብስለት የሠሯቸው ሥራዎች ናቸው። አፈንጋጭ ሆነው ያስቸገሩ ጥቂት አካባቢዎች ናቸው እንጂ አብዛኛው በሠላም ነበር የተስማማቸው።
በመጽሐፉ ያሰፈርኩት በእኛ ምክንያት የአገሪቱን ወጣቶችና ጎልማሶች ምሳሌ የሚሆንለት የተሳካለት ባለታሪክ እንዲያጣ መደረጉን በመቃወም ነው። ነገ እንደእገሌ እሆናለሁ ከሚባልላቸው ሰዎች አንዱ ራስ ጎበና ናቸው።
ስማቸው እንዲጠፋ ስለመደረጉ የሚሉት አለ?
ስለእሳቸው የምትባለው አንዲት ነገር ናት። “የኦሮሞን ሕዝብ ሸጠ” ወይም “የኦሮሞን ሕዝብ ለባዕድ አሳልፎ ሰጠ” የሚል ነው። የት ጋር፣ በምን ሁኔታ፣ ብሎ ምላሽ ለመስጠት የተዘጋጀ ሰው የለም። “ካራክተር አሳሲኔሽን” እንደሚባለው ስማቸውን ለማጠልሸትና ለማጥፋት የሚሞክሩ ናቸው። እሳቸው ላይ የተከፈተው ይህ ዘመቻ ጫፍ ደርሶ ማንም ሰው እውነታውን ለማዳመጥ ዝግጁ አይደለም።
እዚህ ቦታ፣ በዚህ ጦር ሜዳ፣ ይህ ሲደረግ ብለው ማስረጃ ለማቅረብ የሚችሉ የሉም። ትልቁ ወንጀላቸው ተደርጎ የሚወሰደው ከአፄ ምኒልክ ጋር ተባብረው መሥራታቸውን ነው። ያ ሥራቸው አሁን ያለው አገር እንዲኖረን አስተዋጽዖ በማድረጉ እንደውም እኔ እንደማስበው ትላቁን ሚና ተጫውተናል ወደሚል አስተሳሰብ እንዲያመሩ ማድረግ ነበረበት።
አፄ ምኒልክና ራስ ጎበና ሊተጋገዙ ቃል ተገባብተው ነበር ይባላል። ኦሮሞ ኬኒያ እንደቀረው ተከፋፍሎ እንዳይቀር፣ እንዲሁም ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ እርስ በርስ ሊተባበሩ ተማምለው ነበር የሚባለውን እንዴት ያዩታል?
መደበኛ በሆነ መልኩ ቃልኪዳን ስለማድረጋቸው የማውቀው የለም። ነገር ግን፣ ግንኙነታቸው የሚጀምረው ገና አንኮበር እያሉ ነው። ከረጅም ጊዜ ትብብር በኋላ ተከዱ የሚባል ታሪክ አለ። የመጨረሻ ዘመን ታሪካቸው የሚድበሰበሰው የኹለቱ ታላላቅ መሪዎች ተከታዮች ፉክክር ውስጥ ስለገቡ ይመስለኛል።
ስለአሟሟታቸው ያለውን አለመግባባት እንዴት ያዩታል?
ዕድሜያቸው እየገፋ ሲመጣ ሠበር ሰሚ ሆነው ከነገሮች ራሳቸውን እያገለሉ እንደሄዱ የሚነገር አለ። ታሪካቸውን ለመጠቀሚያ የሚያደርጉ የሚያነሱት አንድ ጉዳይ አለ። ተመርዘው ሞቱ የሚሉ ናቸው። በዚህ ጉዳይ አንድ ምዕራፍ ሙሉ ጨርሻለሁ። ሆን ተብሎ ፖለቲካውን ለማጠልሸት የተደረገ ነው። እንጦጦ እንደሞቱ ቢታወቅም፣ አንዳንዶቹ ግብር ላይ የተለየ ነገር ሰጥተው ገደሏቸው ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ በአገልግል ምግብ ሰጥተው ነው የመረዟቸው ይላሉ። ስለዚህ ጉዳይ አንድም ተጨባጭ ማስረጃ የለም። እኔ በመጽሐፌ ስለመጨረሻ ዘመናቸው ያሰፈርኳቸው ሐሳቦች አሉ።
በወቅቱ በመርዝ መገዳደል የነበረ ቢሆንም፣ ራስ ጎበናን ባረጁበት ዘመን መርዞ ለመግደል የሚያበቃ በቂ ፖለቲካዊ ምክንያት የለም። ቀን ችሎት ሲያዳምጡ ውለው ምሽት ላይ ራሴን አመመኝ ብለው ነው በዛው ያረፉት። ይህንን የውጭ ሰዎችም ጽፈውታል።
ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014



