የወንድሜና የእህቴ ጠባቂ ነኝ?

Views: 212

በተለያዩ ማህበረሰቦች ውስጥም ሆነ በተለያየ ጊዜ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ ያሉ አመለካከቶች ይቀያየራሉ፡፡ ቁስ አካላዊ አመለካከቱ እየጠነከረ በመጣው በዚህ ዘመን ማህበረሰብ ዘንድ ግለኝነት እየጠነከረ የመጣ እሳቤ ሆኖ ይታያል፡፡ ማህበራዊ ቁርኝቱ ጠንከር በሚልበት ማህበረሰብ ዘንድ ደግሞ እንዲህ ያለው አመለካከት ጎልቶ አይወጣም፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግለሰቦች ማህበራዊ ኃላፊነት አለባቸው ወይ፤ ካለባቸውስ እስከ ምን ድረስ ነው የሚለውን ጉዳይ ሙሉጌታ አያሌው (ዶ/ር) እንደሚከተለው ዳሰውታል፡፡     

በአንድ የኮንዶሚኒየም መንደር ውስጥ፤ መናገር ያቃታቸው ሽማግሌ ወድቀው ተገኙ። ሁለት ሴቶች ለፓሊስ ደወሉ። የተጠሩት ፓሊሶች፤ ሽማግሌውን ካይዋቸው በኋላ ጥለዋቸው ሄዱ። አንቡላንስ ጠሩ። ኃላፊነት የሚወስድ ከሌለ አንቡላንሱ እንደማይመጣ ተነገራቸው።

ኃላፊነት እንዳይወስዱ፥ ዝም ብለው ወደ ቤታቸው እንዲገቡ፥ ምንም እንደማያገባቸው፥ ችግር ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉና ሌላም ሌላም ነገር እያነሱ ሁለቱን ሴቶች የኮንዶሚኒየሙ ነዋሪዎች አስፈራሯቸው። ሴቶቹ ኃላፊነቱን በመውሰድ ሽማግሌውን ተከትለው በአንቡላስ ወደ ማዘር ቴሬዛ ሄዱ። ስማቸው የማይታወቁት ሽማግሌ ግን እዛ እንደደረሱ ህይወታቸው አለፈ። አስከሬኑን ወደ ምኒልክ ሆስፒታል አስወስደው፤ ለፓሊስ ቃል ሰጥተው ሁለቱ ሴቶች ተመለሱ። ሰውየው በሰዓቱ እርዳታ አግኝተው ቢሆንና ቢድኑ እንዴት ጥሩ ነበር። በሁለቱ ሴቶች ግን በጣም ደስ አለኝ። ኮራሁባቸው።

ስለሌላዉ ደህንነት ምን ያገባናል? የምንኖረው ለራሳችን ብቻ ነው? ስኬታችን፥ ውድቀታችን የየግላችን ነው? የአንድ ግለሰብ ስኬትና ውድቀት በሙሉ የግለሰቡ ነው? አደጋ ላይ የሆነን ሰው አለመርዳት፤ ምን ያህል የወንጀል ኃላፊነትን ማስከተል አለበት? እንደ ማህበረሰብና ሃገር ለድሆች፥ ለታመሙ፥ ለአረጋዊያን፤ ምን ያህል ኃላፊነት አለብን? በእነዚህ ዙሪያ የተለያዩ አመለካከቶች ይስተዋላል።

የገቢ ግብር ሕግ-መንግሥታዊ አይደለም ብለው የሚከራከሩ አሉ። የገቢ ግብር እንደ ዘረፋ መወሰድ አለበት ይላሉ። አንድ ሰው ላቡን አንጠፍጥፎ፥ ፍላጎቶቹን ገድቦ ካገኘው ውስጥ፤ ሸራፋ ሳንቲም ቢሆንም እንኳ፤ በምንም መልኩ መንግሥት መውሰድ እንደሌለበት ይከራከራሉ። መንግሥትም ቢሆን ድሆችን የመደገፍ፥ የታመሙና አረጋዊያንን የመደገፍ ኃላፊነት የለበትም። ይህ መንግሥታዊ ሥራ አይደለም። በጥረታቸዉ የተሳካላቸው ሰዎች፤ ከፈለጉ በበጎ ፈቃድ ሥራ ይሰማሩ። በአብዛኛውም መሰማራታቸው አይቀርም ይላሉ።

ለተሸናፊ ሽንፈቱ፥ ለአሸናፊ ድሉ

የዜጎችን ፍላጎት በላቀ ደረጃ በማሟላት ረገድ፤ ትልቁ ማነቆ የሃብት ውስንነት ነው። ያለን ሃብት የሁላችንንም ፍላጎት በሙሉ ማሟላት አይችልም። እና ምን ይሻላል? የሃብት ምደባና አጠቃቀም በውድድር ይወሰን። እነማን ናቸው የሚወዳደሩት? ዜጎች። እንዴት ነው የሚወዳደሩት? ነፃ ፍላጎታቸውንና ፈቃዳቸውን መሰረት በማድረግ አንድን ሃብት ለማግኘት በልዋጩ ማቅረብ በሚችሉትና በሚፈልጉት ነገር ይወዳደሩ። ከፍተኛ ዋጋ ያለው ልዋጭ ማቅረብ የፈቀደውና የሚችለው ሰው በፈቀደውና በቻለው ልክ ሀብቱን ማግኘት ይችላል። እንዲህ መሆኑ የሚከተሉት ውጤቶች ይኖሩታል ተብሎ ይታሰባል።

አንደኛ፤ አንድን ሀብት ለማግኘት የላቀ ዋጋ ያለው ልዋጭ ማቅረብ ስለሚገባ፤ ፍላጎታቸውን ለማሟላት ሲሉ ሰዎች በሥራና በምርት እንዲተጉ ይሆናል።

አንድ ዳቦ አለን እንበል። የሁላችንንም ፍላጎት ሊያሟላ አይችልም። ጥያቄው፤ ዳቦው ለማን ይሰጥ? በጣም ለራበው? እንዴት ይታወቃል? የሚሻለው፤ ለዳቦው ከፍተኛ ልዋጭ ማቅረብ የሚችለው ዳቦውን ይብላው ነው ተብሎ ይታሰባል። እንበልና ዳቦውን ለማግኘት አበበ አስር ብር መክፈል ይችላል፥ ይፈልጋልም። ከአስር ብር በላይ የሚከፍል ሰው የለም። ስለዚህ ዳቦው ለአበበ መሰጠት አለበት። ሌላ አንድ ሰው ተነስቶ ከአበበ ይልቅ እኔ ነኝ በጣም የራበኝ ቢልስ? ከአበበ የበለጠ የራበው ሰው ቢኖርማ ከአስር ብር በላይ ይከፍል ነበር። አንድን ነገር በጣም ስትፈልገው ነገሩን በልዋጭ ለማግኘት ትሠራ ነበር።

ሁለተኛ፤ ውድድር ምርታማነትን ያበረታታል። ብክነትን በመቀነስ፥ የተሻለ የሥራ ክፍፍል በማድረግ፥ እውቀትን በመጠቀም፥ በመተባበር፤ ሰዎች ትንሽ ግብአትን ተጠቅመው ብዙ ለማምረት ይሠራሉ።

ሶስተኛ፤ ውድድር የቴክኖሎጂ እድገትን ያመጣል።

አራተኛ፤ አንድ ሃብት ብዙ ዋጋ ያላቸውን ፍላጎቶች ለማሟላት ይውላል።

የውድድር ውጤት ፍትሃዊ ነው?

ውድድር አሸናፊና ተሸናፊን ይፈጥራል። ለማሸነፍ በሥራ፥ በምርት፥ በትብብር፥ ብክነትን በመቀነስ፥ እውቀትንና ልምድን በማካበት መትጋትን ይጠይቃል። የተሸነፈው በእነዚህ ነገሮች ያነሰ ትጋት ስላለው ነው። ስለዚህ አሸናፊው ድሉ ይገባዋል። ተሸናፊው ደግሞ ሽንፈቱ ተገቢው ደመዎዙ ነው።

የሃብት ክፍፍል እኩል አይሆንም። እያንዳንዱ በትጋቱ ልክ ያገኛል። ያነሰ የተጋው፤ ያነሰ ሃብት ይኖረዋል። የላቀ የተጋው፤ የላቀ ሃብት ይኖረዋል።

ድርሻን ማብዛት ይቻላል። ብዙ በመትጋት። በሥራ፥ በምርት፥ በትብብር፥ ብክነትን በመቀነስ፥ እውቀትንና ልምድን በማካበት ነው። በእነዚህ አብዝቶ በመትጋት፤ ድርሻን ማብዛት ይቻላል። ስለዚህ፤ ሃብትን በውድድር መመደብና ማከፋፈል አዋጭና ውጤታማ ብቻ ሳይሆን ፍትሃዊም ነው።

የውድድር ፍትሃዊነትን አስመልክቶ ከዚህ በላይ የተራመደው ሃሳብ የአሜሪካን ድሪም እየተባለ የሚጠራው ነው። ዲሞክራቶቹም፥ ሪፐብሊካኖቹም በአሜሪካን ድሪም ያምናሉ። ብዙ ፊልሞች ይሰሩበታል። ብዙ ዜናዎች ይዘገቡበታል። ዋናው መልእክቱ ይሄ ነው፤ “ጠንክረህ ከሠራህ ህይወትህን መለወጥ ትችላለህ። እስከዚ ድረስ ብቻ ብሎ የሚገድብህ ሰው የለም። ብቸኛው ገደብ አንተ ነህ። ለትጋትህ የምታስቀምጠው ገደብ ብቻ ነው የህይወትህን ስፍራ የሚወስነው”።

ተሸናፊዎች እና እድል ፊት የነሳቻቸው

ሃሳቦችን በብዙ መልኩ መገምገም ይቻላል። አንደኛው በፍሬያቸው ነው። የውድድር ፍትሃዊነት ሃሳብ ምን አይነት ውጤቶች አሉት?

አንደኛ፤ ማንኛውም ሰው ያለውን ማህበራዊ ስፍራ ይገባኛል ብሎ እንዲቀበል ያደርጋል። ድሃው ድህነቱን አሜን ብሎ እንዲቀበል ያደርጋል። እንዲሁም የሃብታሙ ሃብት ይገባዋል ብሎ ያስባል።

እንዴት ታዲያ 1 ከመቶ የሚሆነው ሰው 99 ከመቶውን ሃብት ይዞ ሊቀጥል ይችላል? 99 ከመቶው የሚሆነው ሕዝብ ያለውን አሜን ብሎ ካልተቀበለና ሌላው የያዘውን ሃብት ደግሞ ይገባዋል ብሎ ካላመነስ?

ሁለተኛ፤ ሃብታሙም ሃብቴ ይገባኛል ብሎ ያስባል። እንዲሁም ድሃው ድህነቱ የስንፍናው ደመወዝ ነው ብሎ ያስባል።

ድህነት ጨቋኝ እንዲሆን ያደርጋል። ድህነቱን ሙሉ ለሙሉ የግሉ አድርጎ በመውሰድ፤ ለራሱ ያነሰ ዋጋ እንዲሰጥ ያደርገዋል።

ሃብታሙን እንዲኮራ፥ እንዲመካ ያደርገዋል። በላቤ፥ በድካሜ ያገኘሁት ነው ብሎ እንዲያስብ ይሆናል። እንዲህ ሲያስብ ሃብቱን ለማካፈልም አይፈቅድም።

በዘመናዊዋ አሜሪካ፤ ድሆች “ተሸናፊዎች” ይባላሉ። ሀብታሞች ደግሞ “አሸናፊዎች”። ሀብታሞቹ ስኬታችን ሙሉ ለሙሉ የእኛ ነው ብለው ያምናሉ። ድሆቹም ውድቀታቸውን ሙሉ ለሙሉ የእኛ ነው ብለው ያምናሉ። ኩራትና መሸማቀቅ ከፍተኛ ደረጃ ይደርሳል። ግለሰባዊነት ይነግሳል። በስነልቦና መቃወሶች ሰዎች ይሰቃያሉ። መረዳዳት ይቀንሳል።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና አስተማሪ የሆነው ዲበተን እንደሚለው፤ በድሮዋ ብሪታንያ ድሆች “ያልታደሉት”፥ “እድል ፊቷን ያዞረችባቸው” ተብለው ይጠራሉ። እድል ፊቷን ካዞረችባቸው፤ ሀብታሞቹ ሊደኽዩ፥ እድል ፊቷን ከመለስችላቸው፤ ድሆቹ ሊበለፅጉ ይችላሉ። እንዲህ አይነት እምነት የመረዳዳትን ባህል ያበረታታል።

አንደኛ፤ ነግ በኔ የሚል እሳቤ ዛሬ ላይ በጎ እንድንሆን ይረዳናል። የስኬታችን ሙሉ ባለቤቶች አለመሆናችን፥ ከስኬታችን እንድናካፍል ያበረታታል። ሁለተኛ፤ የተሳካለት እንዳይኮራ፥ እንዳይታበይ፥ እንዳይመካ፤ ያልተሳካለት ደግሞ እንዳያፍር ያደርጋል። ኩራትና መሸማቀቅ በመጠን ይቀንሳሉ። ይሄ በራሱ በግለሰቦች አዕምሮ ደህንነት ላይ ትልቅ ሚና አለው።

አራተኛውን ጮርናቄ ማን በላው?

በርክሌይ ባለው የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የተሠራ ጥናት ለምርምሩ የተመረጡ በጎፈቃደኞች ሦስት ሦስት ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው ቡድኖች ተከፋፍለው የተለያዩ ክፍሎች እንዲገቡ ተደረጉ።

ውስብስብ የሞራል ኃላፊነት ጥያቄን የሚያስነሱ ጉዳዮችን በውይይት እንዲፈቱ ትእዛዝ ተሰጣቸው። ለምሳሌ፤ ለፈተና ኩረጃ ምን አይነት ቅጣት ይደንገግ?

ተመራማሪዎቹ፤ በየቡድኑ ካሉት ሦስት አባላት ውስጥ አንዱን ወይም አንዷን የቡድኑ መሪ አድርገው መረጡ። ምርጫው የተከናወነው በዘፈቀደ ነው።

ቡድኖቹ ውይይታቸውን በጀመሩ በሰላሳ ደቂቃ ውስጥ፤ ተመራማሪዎቹ እያንዳንዳቸው አራት ብስኩት ያሉባቸው ሰሃኖች ወደ የክፍሎች አስገቡ።

አራተኛውን ብስኩት ማን በላው? በሁሉም ቡድኖች አራተኛውን ብስኩት የበላው የቡድኑ መሪ ነው። ከሰላሳ ደቂቃ በፊት የቡድኑ መሪ ሆኖ ሲመረጥ የተለየ እውቀትና ብቃት ስላለው አልነበረም። በዘፈቀደ ነበር። የእድል ጉዳይ ነው። መሪ በመሆኑ፤ አራተኛው ብስኩት ይገባኛል ብሎ አመነ።

አዎ፤ ትጋት ወሳኝ ነው። መስዋእት፥ ትጋት፥ ብቃት፥ ትኩረት ወሳኝ ነገሮች ናቸው። ግን ስኬት የእነዚህ ብቻ ውጤት አይደለም። እድል፣ ትንሽ የማይባል፤ ሚና ይጫወታል። ለውድቀትም። ለስኬትም።

እኛ ግን፤ በተለይ የስኬታችን ብቸኛ ባለቤቶች ነን ብለን እናምናለን። አምነንም አናካፍልም። ትምክህት ይሞላናል። ይገባኛል የሚል ስሜታችን ይገዝፋል።

እድል እና ትጋት

በተሰማሩበት መስክ፤ እጅግ የላቀ ስኬት ያስመዘገቡ ሰዎችንና ድርጅቶችን በሚመረምርበት መፅሃፉ፤ ማልኮም ግላድዌል፤ ስለ ዐስር ሺህ ሰዓታት ደንብ ያብራራል። በማንኛውም መስክ፤ ማንኛውም ሰው፤ ለዐስር ሺህ ሰዓታት ብቃቱን ለማሻሻል አተኩሮ ቢለማመድ፤ በመስኩ ከተሰማሩ ፕሮፌሽናል ባለሙያዎች ጋር የሚቀራረብ አቅምን መገንባት ይችላል። ዐስር ሺህ ሰዓታት ማስመዝገቡ አይደለም፤ ዋናው ነገር። እያንዳንዱን ሰዓት ብቃቱን ለማዳበር ግብ ሲጠቀምበት ነው። መልህቅ ዝንት አለም ውሃ ላይ በኖረ ተዘፈዘፈ እንጂ መች ዋና ተማረ!

ብዙ ግለሰቦችና ድርጅቶች፤ ስኬታቸው በይፋና በሰፊው ከመናኘቱ በፊት፤ ያለምንም እውቅናና የላቀ ጥቅም ለብዙ ሺህ ሰዓታት፤ ሲለፉ እንደነበር ፀሃፊው ያሳየናል። የማልኮም ግላድዌልን መፅሃፍ ያነሳሁት ስለ ዐስር ሺህ ሰዓታት ደንብ ለማብራራት አይደለም። ይልቅስ በመፅሃፉ የተዳሰሰውን ሁለተኛ ቁምነገር ለማንሳት እንጂ። እርሱም እድል ነው። ዐስር ሺህ ሰዓታት መለማመድ ትልቅ ዲሲፕሊንና ትጋት ይጠይቃል። ይሄ ብቻ ግን በቂ አይደለም። እድልም ወሳኝ ነው።

እንደ ፀሐፊው እምነት ቢል ጌትስ አንድ ዓመት ቀድሞ ወይም ዘግይቶ ቢወለድ ኖሮ፤ እንዲህ እንደ አሁኑ ስኬታማ ላይሆን ይችል ነበር። ለስኬቱ መነሻ የሆነውን፤ የማይክሮሶፍት ኦፕሬቲንግ ሲስተም፤ ከመገንባቱ ዓመታት አስቀድሞ፤ የኮምፒውተርና ፕሮግራሚንግ እውቀቱንና አቅሙን እንዲገነባ የረዳው የተማረበት ትምህርት ቤት ነው።

ቢል ጌትስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲገባ፤ ፓራለል ኮምፒዩቲንግና ፕሮግራሚንግ የሚባለው አሠራር ለገበያ ቀረበ። ከፍተኛ አቅም ያላቸውን ኮምፒዩተሮች የተለያዩ ሰዎች ለፕሮግራሚንግ የሚጠቀሙበት አሠራር ነው። ይህ ሲስተም በገበያ ያለው ዋጋ ለግለሰቦች የማይቀመስ ነበር። ለአብዛኞቹ ትምህርት ቤቶችም ቢሆን ዋጋው ውድ ነበር። ቢል ጌትስ የሚማርበት ትምህርት ቤት ግን፤ የተሻለ አቅም ስለነበረው፤ ለተማሪዎቹ መማሪያ ስርአቱን ዘረጋ። የቢል ጌትስ ውሎና አዳር በኮምፒዩተር ቤተ ሙክራው ውስጥ ሆነ። ቢል ጌትስ የዐስር ሺ ሰአታት ልምምዱን ያደረገው ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነበር።

እንዲህ እንደ አሁኑ የቴክኖሎጂው ዋጋ እጅግ በጣም ቀንሶ ሰዎች የግል ኮምፒዩተር ባለቤትና የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ከመሆናቸው በፊት የቢል ጌትስ ትምህርት ቤት ግን ለተማሪዎቹ እንዲህ አይነት እድል አቀረበ። ቢል ጌትስ ሌላ ትምህርት ቤት ተምሮ ቢሆን ኖሮ፥ ወይም አንድ አመት ቀድሞ ወይም ዘግይቶ ተወልዶ ቢሆን ኖሮ፤ ከሌሎች ቀድሞ የፕሮግራሚንግ ብቃቱን አዳብሮ እንዲህ ቢሊየነር ላይሆን ይችል ነበር። እንደ ፀሃፊው አባባል።

ማልኮም ግላድዌል የትጋትንና የዲስፕሊንን ዋጋ እያሳጣ አይደለም። “ይልቅስ ትጋት ብቻውን በቂ አይደለም፤ በእድል ሲታገዝ ነው፤ እጅግ ከፍተኛ ስኬት ላይ የሚያደርሰው” ነው አባባሉ። እድልም ብቻውን በቂ አይደለም። በመፅሀፉ እንደ ቢል ጌትስ አይነት ብዙ ታሪኮችና የጥናት ፅሁፎች ተጠናቅረው ቀርበውበታል።

***

ማይክል ሳንዴል በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ፕሮፌሰር ነው። በገበያ ስርዓት ፍትሃዊነትና የሞራል ገደብ ዙሪያ ብዙ ንግግሮችን አድርጓል፥ ፅሁፎችን አሳትሟል። በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ከሚያስተምራቸው ኮርሶች ውስጥ አንዱ “ፍትህ” ይባላል። በዚህ ኮርስ ብዙ ጉዳዮችን ከተማሪዎች ጋር ይወያያል። አንደኛው ጉዳይ “በኑሮ የተሳካላቸው ሰዎች፥ ሀብታሞች፤ ምን ያህል ግብር ሊከፍሉ ይገባል?” የሚለው ነው።

አንዳንዶቹ እንደሚያምኑት፤ ሰዎች በድካማቸው፥ በላባቸው ያገኙትን ገንዘብ፤ መንግሥት በግብር መልክ መሰብሰብ ቅሚያ፥ ዝርፊያ ነው። በተለይ ደግሞ፤ መንግሥት ይህን ገንዘብ የሚጠቀመው እንደነርሱ ለማይደክሙት፥ ለማይተጉት ሌሎች ሰዎች አገልግሎት ለማቅረብ ከሆነ። እንዲህ አይነት አስተሳሰብ የሚመነጨው “የገንዘቤ፥ ስኬቴ ባለቤት እኔ ብቻ ነኝ” ከሚል እምነት ነው። ከዚሁ ጋር የሚያያዘው እምነት “የውድቀትህ ባለቤት አንተ ብቻ ነህ” የሚለው ነው። እውነት ግን እንደዛ ነው? በስኬታችን ወይም በውድቀታችን፤ እድል ምን ያህል ቦታ አለው?

ፕሮፌሰር ማይክል ሳንዴል በአንድ ወቅት በዚሁ ጉዳይ ለሚያስተምራቸው ተማሪዎች ያነሳው ነጥብ፤ እድል ወይም ከትጋታችን፥ ምርጫችን ጋር የማይያያዙ ጉዳዮች ምን ያህል ስኬታችንን እንደሚወስኑት ነው። ለምሳሌ፤ ለወላጆቻችን ስንተኛ ልጅ እንደሆንን የምንወስነው እኛ አይደለንም። ከኛ ፍላጎት፥ ምርጫ፥ ትጋት ጋር አይያያዝም። እድል ነው። ነገር ግን ብዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የመጀመሪያ ተወላጆች የበለጠ ስኬታማ ናቸው። በአሜሪካን ካሉ ምርጥ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከቀዳሚዎቹ አንዱ ተብሎ በሚቆጠረው ሃርቫርድ ትምህርት ቤት፤ በተለይ ደግሞ ፕሮፌሰር ሳንዴል በሚያስተምረው በዚሁ “ፍትህ” የተባለውን ኮርስ የሚከታተሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ውስጥ የመጀመሪያ ተወላጆች የሆኑት እጃቸውን እንዲያወጡ ሲጠይቃቸው፤ እጅግ ብዙዎቹ እንዳወጡ ከቪዲዮው መመልከት ይቻላል።

በገበያ ውድድር ብንሸነፍ ወይም ብናሸንፍ፥ የድላችን ወይም ሽንፈታችን ሙሉ ባለቤቶች አለመሆናችንን ያሳያል። እድልም ከፍተኛ ድርሻ አለው። ወላጆቻችንን፥ ያደግንበት ቦታን፥ የተወለድንበትን ጊዜ፥ በቤተሰብ ውስጥ ያለን የውልደት ደረጃ፥ የህይወት አጋጣሚዎችን፥ እና ብዙ ነገሮችን በትጋታችን የምናገኛቸው አይደሉም። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ግን የህይወት ስፍራችን ላይ ተፅእኖ አላቸው።

ትናንት ለኔ

በዓለም ላይ ከሚታወቁት ቢሊየነሮች መካከል ዋረን በፌት አንዱ ነው። በ2000 የዓለም ኢኮኖሚ ከፍተኛ ቀውስ ሲያጋጥመውና የብዙዎቹ ቢሊየነሮች ሀብት ሲቀንስ፤ የዋረን በፌት ሀብት ግን አልቀነሰም። እንደውም በወቅቱ በዓለም አንደኛው ሃብታም ለመሆን ችሏል። የዚህን ሚስጥር ለማወቅ አንድ የቢቢሲ ጋዜጠኛ በዋረን በፌት ላይ ዘገባዊ ፊልም አዘጋጅቶ ነበር።

ዋረን በፌት የሚኖረው ከአርባ ዓመት በፊት በገዛው ባለ ሶስት መኝታ ቤት ውስጥ ነው። ለምን ተብሎ ሲጠየቅ፤ “ለኔ የሚያስፈልገኝ አንድ መኝታ ቤት ነው። እንግዳ ቢመጣ ደግሞ ተጨማሪ ሁለት መኝታ ቤት አለኝ። ከዚህ በተረፈ ለምን ብዙ መኝታ ቤት ያለው ቤት ያስፈልገኛል። ማስተዳደሩም ትልቅ ድካም ነው”። የዋረን ልጆች ከአባታቸው ምንም ነገር በውርስ እንደማያገኙ አስቀድሞ ነግሯቸዋል። አንደኛዋ ልጁ የእለት ጉርሷን የምታገኘው የሀብታሞችን ውሾች በማዝናናት ነው።

ዋረን የሚታወቀው በሀብቱ ብቻ አይደለም። በለጋስነቱም ጭምር ነው። ሙሉ ሀብቱን ለበጎ አድራጎት ሥራዎች መድቧል። በተጨማሪም ሀብታም ጓደኞቹ (እንደ ቢል ጌትስ ዓይነቱን) ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ ያበረታታል። ለምን ብሎ ጋዜጠኛው ሲጠይቀው፤ የዋረን በፌት መልስ እንዲህ የሚል ነው፤ “ለምሳሌ እኔ የተወለድኩት ሌላ ሀገር ነው እንበል። በተወለድሁበት አገር፤ አሁን የተጋሁትን ያህል ብተጋ፤ እንዲህ ሃብታም መሆን እችል ነበር ወይ ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ። መልሱም አልሆንም ነው። ስለዚህ ለእኔ ስኬት የአሜሪካ አገራዊ ስርአት ትልቅ ሚና አለው። የሀብቴ ሙሉ ባለቤት እኔ ነኝ ብዬ አላምንም”።

የዋረን ደግሞ የተለዬ ነው። በእርግጥ እርሱ አሜሪካዊ ሆኖ ለመወለድ አልመረጠም። ግን ደግሞ ብዙ አሜሪካዊያን ነበሩ። የዋረን ታሪክ የሚያሳየን አገራዊ ስርአቱ (ባህል፥ ሕግ፥ መዋቅር፥ ሌሎች ሰዎች) ለሥራህ ፍሬ ያላቸውን ሚና ነው።

ትናንት ለኔ እና ነግ በኔ

ከሰዎች ጋር በሚኖረን መስተጋብር፤ ባህሪዎቻችንን መሰረት ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል “ነግ በኔ” የሚባለው ነገር ነው።

ነገ በእርሱ ቦታ ልሆን እችላለሁ። ስለዚህ፤ ለየኔቢጤ ስትመፀውት፤ ነግ በኔ እያልክ ነው። ሌላ ሰው ጋር ጉዳት ሲደርስበት፤ የምታዝነው፥ የምትሟገተው፥ የምትከላከለው፤ ነግ በኔ በሚል ነው።

በነግ በኔ ውስጥ፤ ሁለት መልክቶች አሉ። አንደኛ፤ ነገ በእርሱ ቦታ ራሴን ላገኘው እችላለሁ የሚለው ነው። ሁለተኛው፤ ነገ ብድራቴ ይመለስልኛል የሚለው ነው። ዛሬ ያጣሁትን ጊዜ፥ ገንዘብ፥ ደስታ፥ መረጋጋት፤ ነገ በተመሳሳይ ሁኔታ ስሆን፤ በዛሬው የኔ በጎነት የተጠቀመው ሰው ብድራቱን ይመልስልኛል የሚል ነው።

ለመልካምነት ከሚቀርቡ ምክንያቶች ውስጥ አንደኛው ነግ በኔ ነው። ግን ደካማ ምክንያት ነው። አንደኛ፤ መልካምነትህ ነገ አገኘዋለሁ በምትለው ሰው ብቻ እንዲወሰን ያደርጋል። ሁለተኛ፤ ስለ ነገ መኖርህ እርግጠኛ ስትሆን ወይም ሟችነትህን ስትረሳው ብቻ መልካም እንድትሆን ያደርጋል። ሟቾች ነን ብቻ ሳይሆን፤ መቼ እንደምንሞትም አናውቅም። ምንም እንኳ፤ “በፍርሃታችን ሟቾች በፍላጎታችን ዘላለማዊያን ብንመስልም”።

ከነግ በኔ የሚሻለው የመልካምነት መሰረት “ትናንት ለኔ” የሚለው ነው። መልካምነትህ፤ እንደሚመጣ እርግጠኛ ባልሆንከው ነገ ሳይሆን፤ በእርግጠኛው ትናንት እንዲመሰረት ይደርጋል። ስለዚህ በትናንትህ የሰዎች መልካምነት ተጠቃሚ አልነበርክም? ሌላው ቢቀር በወላጆችህ ወይም አሳዳጊዎችህ መልካምነት አይደለም እንዴ እዚህ የደረስከው? እነርሱስ ቢሆን ነግ በኔ በሚል ነው ለአንተ መልካም የሆኑት? አይመስለኝም። ስለዚህ፤ ትናንተ ለኔ፤ ከነግ በኔ የተሻለ፤ የመልካምነት መሰረት ነው። ቢሆንም የራሱ ጉድለት አለበት። መልካምነታችን በማስታወስ ብቃታችን እንዲወሰን ያደርጋል።

የተሻለው ነግ በኔም ትናንት በኔም አይደለም። የተሻለው እይታ፤ የዛሬው መልካምነት የራስ ጥቅም በዛሬ መጉደል ሳይሆን የዛሬው መልካምነትህ የዛሬውን ህይወትህን ማበለፀግ እንደሆነ መቀበል ነው። መልካምነት ራስ ወዳድነት ነው። መልካምነት ለራስ ነው። ለራስና ለነገ አይደለም። ለራስና ለዛሬ ነው።

አዎ፤ የወንድሜ ጠባቂ ነኝ። ምክንያቱም፤ ወንድሜን ለመጠበቅ ከማወጣዉ ወጪ በላይ ተጠቃሚ ስለምሆን። ያንተን እምነት፥ ባህልና፥ ቋንቋ ያንተ ብቻ ያደረገው ማን ነው? የእኔም ነው። እምነቴ፥ ባህሌ፥ ቋንቋዬ፥ እውነቴ የሚጠቅመኝ ያንተን እምነት፥ ባህል፥ ቋንቋና፥ እውነት ለመጠበቅ፥ ለመቅረብ ስሠራ ብቻ ነው። ያለዚያ፤ የእምነቴ፥ ባህሌ፥ ቋንቋዬ፥ እውነቴ ተካፋይ፥ ተቆርቋሪ፥ ወይም መሪ ነን ባሉ ሰዎች ስገዛ እኖራለሁ።

ለአገዛዛቸው እንዲመቻቸው፤ ከእምነትህ፥ ባህልህ፥ ቋንቋህ፥ እውነትህ የሚለዩትን፤ እንደ ጠላት እንድትፈርጅ ይተጋሉ። እምነትህ፥ ባህልህ፥ ቋንቋህና፥ እውነትህ፤ ብቸኛ፥ ፍፁምና፥ ሰማያዊ እንደሆኑ ይደሰኩሩልሃል። የተፈጥሮህ ክፋይ እንደሆኑ ያስተምራሉ። ያለዚያ እንዴት ይገዙሃል።

አዎ፤ ያንተ፤ የእኔም ነው። የእኔ፤ ያንተም። የወንድሜ፥ የእህቴ ጠባቂ ነኝ። ነፃነት ያለው በዚህ ነው።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com