ሲዘነጉት የማይዘነጋው ኤች አይ ቪ ኤድስ

0
1121

ኢትዮጵያ በየዘመኑ አያሌ ውስብስብ ችግሮችን እንዳስተናገደች የታተመ ታሪኳ ኅያው ምስክር ነው። ጦርነትን፣ የፖለቲካ አለመረጋጋትን፣ ርሃብን ድርቅን እንዲሁም ወረርሽኝን ተቋቁሞ ማለፍ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም። ስለ ርሃብ እንኳን ቢወሳ የ1977ቱ ድርቅ የማይረሳ እና አገራዊ ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ነው። በየዘመኑ ጦርነቱ፣ ድርቁ፣ ርሃቡ፣ ወረርሽኙ፣ወዘተ. ተግተልትለው በመምጣት አገራችንን ሲፈትኗት ኖረዋል።

ይህ ዘመን ያሰቆጠረ ችግር ታዲያ አሁንም አልጠፋም። አንዱ ችግር ሌላኛውን እየሳበና ኢትዮጵያን እያዳከመ እንዳለ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ሕያው ምስክር ነው።

ከእነዚህ ችግሮች መካከል ከተከሰተ ዓመታትን ያስቆጠረው የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ አንዱ ነው። የሌላ ወቅታዊ ችግር መከሰት ለነበረው ችግር የተሰጠን አትኩሮት ጠቅልሎ እየወሰደ፣ የቆየው የጠፋ እየመሰለ ውስጥ ለውስጥ የመንሰራፋት ዕድል ያገኛል። ብዙዎች በዚህ ወቅት የዘነጉት ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ አሁንም ድረስ የብዙዎችን ሕይወት የሚቀጥፍ አንዱ የወቅቱ አሳሳቢ ችግር መሆኑን በርካቶች ይናገራሉ።

የኤች አይ ቪ ኤድስ የውስጥ ለውስጥ የሥርጭት መጠን ለመጨመሩ ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል የብዙኅኑ አትኩሮት ወደ “ኮቪደ-19” ወረርሽኝ መሆኑ አንዱ ነው። ከተጀመረ ዓመት የሞላውና ሕዝቡን በጭንቀት እየናጠ ያለውም ጦርነት በግንባር ቀደምትነት ከሚመዘዙ ምክንያቶች ሌላው መሆኑ እየተነገረ ነው።

በዚህ ጉዳይ ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ከሰጡት ግለሰቦች መካከል አማረ ምስጋን የተባሉ ወጣት፣ የኮቪድ -19 መከሰት ኤች አይ ቪ ኤድስ እንዲዘነጋ በር በመክፈት ለዜጎች ሌላ ተጨማሪ ፈተና እንደሆነ ይናገራሉ። በተለይም በመዲናችን ያሉ ሰዎች የዕለት ተዕለት አትኩሮታቸውን ሙሉ ለሙሉ ኮሮና ቫይረስ ላይ በማድረጋው “ኤች አይ ቪ ኤድስ ጠፍቷል” የተባለ በሚመስል መልኩ በሽታው እየተዘነጋ መጥቷል በማለት ነው ያስተዋሉትን የተናገሩት።
ግለሰቡ ሌሎች ምክንያቶችንም የጨመሩ ሲሆን፣ ይኸውም በተለይም በመዲናችን ውስጥ ያሉ ሴተኛ አዳሪዎች የሚያሳዩት ጥንቃቄ እምብዛም እንደሆነ ነው የጠቆሙት።

በተለይም፣ በከተማ አካባቢ ያሉ ሥራ አጥ ሴቶች ሴተኛ አዳሪነትን የገቢ ምንጭ ማግኛ አድርገው በማስብ፣ በየጊዜው የተለያዩ ወንዶችን በግብረ ስጋ ግንኙነት እንደሚያስተናግዱና ምርመራም እንደማያደርጉ የጠቆሙ ሲሆን፣ ምርመራ ቢያደርጉ በርካቶች የቫይረሱ ሰለባ ይሆናሉ በማለት ነው ከተገነዘቡት ተነስተው ያላቸውን ግምት ያስቀመጡት።

ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ በመዲናችን የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ለተመለከ ሰው በርካታ ሴተኛ አዳሪዎች መንገድ ዳር ጥግ ይዘው የገቢ ምንጭ የሚያስገኝ ተባዕትን ሲጠብቁ ይስተዋላሉ የሚሉት አማረ ምስጋን፣ መንግሥት ለኮሮና ቫይረስ “በግዴታ” ክትባት እንደሚያሰጠው ሁሉ፣ ሴተኛ አዳሪዎችንም በአሰሳ ሰብስቦ እንዲመረመሩ ማድረጉ የተሻለ ነው ሲሉ ነው ጥቆማቸውንና አስተያየታቸውን የተናገሩት።

የሴተኛ አዳሪዎች የቫይረሱ ሰለባ መሆን፣ ለኤች አይ ቪ ኤድስ መጨመር አንደኛው ምክንያት መሆኑንም የፌዴራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መካላከልና መቆጣጠር ጽ/ቤት ኃላፊዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የፌዴራል የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጣር ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ዳንኤል በትረ እንደተናገሩት፣ ለቫይረሱ መጨመር መንስኤ ሴተኛ አዳሪዎችን በዋናነት የጠቀሱ ሲሆን፣ አያይዘውም 18 በመቶ የሚሆኑት ሴተኛ አዳሪዎች የኤች አይ ቪ ቫይረስ ተጠቂ መሆናቸውን ነው ያመላከቱት።

በሌላ በኩል፣ ለኤች አይ ቪ ኤድስ መስፋፋት እንደምክንያት ይሆናል ተብሎ በግለሰቦች ዘንድ እየተነገረ ያለው ጉዳይ በአገራችን ከተከሰተው ጦርነት ጋር የተያያዘ ነው።

በዚህ ጉዳይም ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ የሚዲያ ተቋማትም ጭምር በሚያዘጋጁት ዘገባ የጦርነቱ ሰለባ በሆኑ አካባቢዎች የኤች አይ ቪ ኤድስ ሥርጭት የሚጨምርበትን ሁኔታ ማመላከታቸውን መመልከት ይቻላል።
አንድ የአዲስ ማለዳ ምንጭ እንደሚሉት ከሆነ፣ ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው የህወሓት ቡድን በተቆጣጠራቸው የሰሜኑ አካባቢዎች፣ “ኤች አይ ቪ ኤድስ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ግለሰቦችን ከትግራይ ክልል እያስመጣ ሴቶችን እያስደፈረ” ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ከምንጮቻችን መካከል ሰሞኑን ከሰሜን ወሎ አካባቢ ወደ ባህር ዳር ያቀናው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ግለሰብ፣ ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው የህወሓት ቡድን “ንጹሐንን ከመግደላቸው፣ ንብረት ከመዝረፋቸው፣ በተጨማሪ ሴቶችን መድፈራቸውን በተደጋጋሚ ተናግሯል። አያይዞም፣ የሚገርመው ነገር ግን መድፈር ሲባል እንዲሁ በድንገት ሳይሆን፣ ከትግራይ ክልል ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎችን መርጦ በማምጣት ሆን ብሎ በተለይም ልጃገረዶችን እንዲደፍሩ በማዘጋጀት ነው” በማለት ነው ያስተዋለውን በመገረም የገለጸው።

ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው የህወሓት ቡድን በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የኤች አይ ቪ ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር እንደሚጨምር መገመት አይከብድም የሚለው ግለሰቡ፣ ይህ ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ የሚመለከተው አካል “ከሞት የሚተርፉ” የአካበቢው ነዋሪዎችን አንድ ባንድ ምርመራ ሊሰጥ ይገባል ሲል አሳስቧል።

የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደሚያመላክቱት ከሆነ፣ በጦርነቱ ቀጠና ውስጥ ያሉ ሰዎች ሰለባ የሆኑት ለሞት፣ ለርሃብ፣ ለመደፈር እንዲሁም ለመድኃኒት ዕጥረት ብቻ ሳይሆን፣ “ሆን ተብሎ” ለኤች አይ ቪ ቫይረስም መሆኑን ሲሆን፣ ይህም ጦርነቱ ያስከተለው ሌላኛው ለኤች አይ ቪ መጨመር ምክንያት እንደሚሆን ነው መረዳት የተቻለው።

በሌላ በኩል፣ የኤች አይ ቪ ቫይረስን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በየፈርጁ የተሰማሩት ባለ ድርሻ አካላት አትኩሮት እንደሚገባው እያሳሰቡ ነው። እንደሚሉት ከሆነም፣ ከጦርነቱ ጋር የመተባበር ውል የተፈራረሙ የሚመስሉ እንደ ኮሮና ቫይረስ አይነት ወረርሽኝ፣ ሞት፣ ርሃብ እንዲሁም የዜጎች መፈናቀል፣ ከተከሰተ ሰንበትበት ያለውን የኤች አይ ቪ ወረርሽኝ ሕዝቡ እንዲዘነጋው በማድረጋቸው፣ ሲዘነጉት የማይዘነጋው ቫይረሱ (ኤች አይ ቪ) ለመስፋፋት ዕድል እያገኘ መሆኑን ነው ያመላከቱት።

ኮቪድ -19 ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ አገራችን ኢትዮጵያ በርካታ ዜጎችን ስለማጣቷና አሁንም እያጣች ስለመሆኗ የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት በየዕለቱ የምርመራ አገልግሎት ከሚሰጡ ዶክተሮች ተቀብለው የሚያስተጋቡት ዜና ምስክር ነው።

የፌዴራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል ጽ/ቤት እንደሚያመላክተው ከሆነ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ዜጎች ለኤች አይ ቪ ኤድስ ይሰጡት የነበረው ጥንቃቄና አትኩሮት እንዲቀንስ ምክንያት መሆኑን እና ለቫይረሱ መስፋፋት በር ከፋቺ ሆኖ መቆየቱንና መቀጠሉን ነው።
የተለያዩ የሚዲያ ተቋማት በኮቪድ-19 ዙሪያ በተደጋጋሚ በመዘገብ መረጃ እንደሚሰጡትና ትምህርት እንደሚለግሱት ሁሉ፣ የተረሳው የኤች ኤች አይ ቪ ሥርጭት ላይም ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ሕዝቡን ማንቃት ይገባል የሚሉት የፌዴራል ኤች አይ ቪ አድስ መካላከል ጽ/ቤት የሕዘብ ግንኙነት ኃላፊ ዳንኤል በትረ ናቸው።

ኃላፊው አያይዘውም፣ የሚዲያ ተቋማቶች እያተኮሩ ያሉት ኮቪድ19 ላይ፣ እንዲሁም አገሪቱ በገባችበት ጦርነት ጉዳይ ላይ ቢሆንም፣ ሚዲያዎች በተመሳሳይ የኤች አይ ቪ ጉዳይንም ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩበት ይገባል ብለዋል።

ዳንኤል ለቫይረሱ መስፋት ከጠቀሷቸው ምክንያቶች መካከል ከፍቺና ከሞት ጋር የተያያዙ ችግሮች ተጠቃሽ ናቸው። የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው እንደሚሉት ከሆነ፣ ባሎቻቸውን በሞትና በፍቺ ምክንያት ያጡ ሴቶች ለኤች አይ ቪ ኤድስ ሥርጭት መጨመር መንስኤ መሆናቸውን ነው መረዳት የተቻለው።

በኃላፋ ገለጻ መሰረትም፣ ባሎቻቸው የሞቱባቸውና በአንድም በሌላም ምክንያት ፍቺ በፈጸሙ ሴቶች የቫይረሱ ሥርጭት ከ20 በመቶ በላይ መሆኑ የተመላከተ ሲሆን፣ ባሎቻቸው ከሞቱባቸው ወይም ከተፋቱ መቶ ሴቶች ውስጥ ከ20 በላይ የሚሆኑት የቫይረሱ ሰለባ የሆኑ ናቸው ብለዋል።

የቫይረሱ ሥርጭት ከገጠሩ ክፍል ይልቅ በከተማ በከተሙ ዜጎች ከፍ ያለ ነው የሚሉት ዳንኤል፣ ገጠር ላይ 0.4 በመቶ ሲሆን፣ ከተማ ላይ ሦስት በመቶ መሆኑን ገልጸዋል። በአጠቃላይ በአንድ ዓመት ውስጥ 10ሺሕ ሰዎች ለቫይረሱ ሰለባ እንደሚሆኑና በዓመት ውስጥ 12 ሺሕ የሚሆኑ ዜጎች በኤድስና ተያያዥ በሽታዎች እንደሚሞቱ አመላክተዋል።

አያይዘውም፣ ይህ የሞት መጠን በዝርዝር ሲተነተን በቀን ከ30 በላይ ሰዎችን የሚያሳጣ እንደሆነና፣ ምንም እንኳ ከ19 ዓመት በፊት በአንድ ዓመት ውስጥ ከ105 ሺሕ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲጠቁ የነበረ ቢሆንም፣ በዚህ ወቅት ወደ 10ሺሕ ሰዎች ዝቅ ብሏል። ከእነዚህ በቫይረሱ ከተያዙት መካከል 95ሺሕ ሰው በሞት እየታጣ ቢቆይም፣ አሁን ላይ ወደ 12ሺሕ ዝቅ ማለቱ፣ እንዲሁም ከ12.6 የሥርጭት መጠን ወደ 0.9 የሥርጭት መጠን ዝቅ ማለት ትልቅ ለውጥ ቢሆንም፣ በዓመት 12ሺሕ ሰው ማጣት ቀላል አይደለምና በዚህ ወቅቱ የሚታየው መዘናጋት ሊታሰብበት ይገባል ሲሉ ነው ያሳሰቡት።

ዳንኤል በመጨረሻም፣ የሚዲያ ተቋማት እስካሁን ጉዳዩን በተመለከተ እየሠሩ ቢሆንም፣ በቂ ስላልሆነ ከዚህም በላይ መሥራት እንዳለባቸውና ይህን ለማድረግም የመንግሥትም የሕዝብም ትብብር እንደሚያስፈልግ አውቆ ሁሉም ሰው አትኩሮቱን ማጠናከር አለበት ሲሉ ነው ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ምክራቸውን የለገሱት።

የፌዴራል የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ጽ/ቤት የሥርጭቱን አሳሳቢነት ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ከመንግሥት ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሔ ለማምጣት አቅዶ እየሠራ መሆኑን ኃላፊው አመላክተዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here