የጦር አውሮፕላኖቹ ከፍታ

0
658

ሠሞኑን መነጋገሪያ ከነበሩ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ አየር ኃይል ቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ አደረግኳቸው ያላቸውን ድብደባዎች ተከትሎ የተሰነዘሩ ሐሳቦች ናቸው። አየር ኃይሉ ጀቶችንና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ተጠቅሞ ለህወሓት ታጣቂ ቡድን መሠረታዊ የሆኑ የመሣሪያና ሎጀስቲክስ ማከማቻ፣ የማሰልጠኛና መሰል ካምፖችን በቦንብ ማጋየቱን በምስል ጭምር እያቀረቡ ብዙዎች ሲነጋገሩበት ቆይተው ነበር።
ወታደራዊ መኪኖች የሚጠገኑበትን ተቋም፣ እንዲሁም ተመሳሳይ ወታደራዊ ዩኒፎርም እያመረቱ የሚያሳስቱበት ነው የተባለ ፋብሪካን ጨምሮ በተደጋጋሚ ድብደባ መፈጸሙን በርካቶች እንደስኬት ወስደው አስተያየታቸውን ሲሰጡ ቆይተዋል። በአንፃሩ ድብደባው ዕርዳታ የማሰራጨት ተግባሩን እንዳወከ በማድረግ፣ ስሞታቸውን አሸባሪ ተብሎ ተፈርጆ ከሚደበደበው አካል ቀድመው ያሰሙ ነበሩ።
የአየር ድብደባው ያደረሰው ጉዳትን ማንም በምስል ማየት የሚችል ቢሆንም፣ በታጣቂ ቡድኑ ላይ ያሳደረውን አካላዊ፣ ቁሳዊና ሥነ-ልቦናዊ ተጸዕኖን ግን በእርግጠኝነት ማወቅ ከባድ ነበር። ይህ ሒደት በተደጋገመ ጊዜ የቡድኑ አመራር የሆኑ ግለሰብ በዓለም አቀፍ ሚዲያ ላይ ቀርበው የተናገሩት ብዙዎችን ዘና ሲያደርግ ለአንዳንዶች ደግሞ መቀለጃ ሁኗል። “አውሮፕላኖቹ ዝቅ ብለው ቢሆን ኖሮ በአየር መቃወሚያችን እንመታቸው ነበር” በማለት የተናገሩት ብዙ አስብሏል።
አውሮፕላኖቹን እንዳንመታቸው ከፍ ብለው ነው የሚበሩት አሉ ተብሎ፣ “ዝቅ ብሎ እንዲበርላቸው ፈልገው ይሆናል”፣ “ገጥመን መስሎን” የሚሉና ተመሳሳይ ቀልድ አዘል ምላሾች ተሠንዝረዋል። በእርግጥ ጦርነት እንደመሆኑ አንደኛው በሌላኛው ዒላማ ውስጥ ላለመግባት መጣሩ አንዱ የውጊያ መርህ ነው። ይህ ቢሆንም፣ እሳቸው ግን ዝቅ ብሎ እንዲበርላቸው የፈለጉ ይመስል የማይጠበቅ አስተያየታቸው መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
የጋዜጠኛው ጥያቄ ለምን አልመታችኋቸውም የሚል ይዘት ቢኖረው እንኳን፣ ከፍ ብለውብን ነው የሚል መልስን የጠበቀ አይመስልም እያሉ ሐሳባቸውን የሰነዘሩ አሉ። ዝቅ ብለው ቢበሩ አቅሙ ነበረን ለማለትና የብቃት ማነስ ጉዳይ አይደለም ለማለት ቢያስቡ እንኳን የአስተያየታቸው ዓላማ ግልጽ ያልሆነላቸው፣ “እባካችሁ እንድንመታችሁ ዝቅ በሉ” የሚል መልዕክትን ምን አመጣው ሲሉ አሹፈዋል።
በሌላ በኩል፣ የቡድኑ መሪ የሰጡት አስተያየት ላይ የተሰነዘረ ቀልድ ሳያባራ፣ አሸባሪ የተባለው ቡድን ደጋፊዎች ለተቃውሞ ባሉበት ውጭ አገር አደባባይ መውጣታቸው ሌላ አግራሞትን የፈጠረ ተግባር ነበር። አመራሮቹ አሸንፈናል እያሉ ወታደር መመልመያ እንዲሆናቸው ሕዝባቸው ላይ ቅስቀሳ እያደረጉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በቀይ ቀለም የተለወሰ ጨርቅ ተጠቅልለው በዓለም አደባባይ እንደተበደሉ ሠልፍ መውጣታቸው ግርምትን ፈጥሯል። ተንበርክከው የቡድኑን ባንዲራ ይዘው የሚታዩበትን ምስል እየለጠፉ፣ “ምነው እንደልባችን እንውረር፣ እንዝረፍ፣ እንግደል ነው!” በሚል የምዕራባውያኑን ልብ ለመስረቅ ደረጉትን ጥረት እያነጻጸሩ መሪዎቻቸው ከሚናገሩትና ታጣቂዎቹ ከሚያደርጉት ተግባር ጋር እያስተያዩ ሙከራቸውን የተቹ በርካቶች ናቸው።


ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here