የቅመማ ቅመም ግብይትና ጥራት ቁጥጥር መመሪያ መዘጋጀቱ ተገለጸ

0
946

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የቅመማ ቅመም ግብይት እና ጥራት ቁጥጥር አፈጻጸም ረቂቅ መመሪያ ማዘጋጀቱን አስታወቀ።
ረቂቅ መመሪያው በዋናነት የተዘጋጀው የቅመማ ቅመም አምራች አርሶ አደሮችን እና የግብይት ተዋንያንን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ከኤክስፖርት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ታሳቢ ተደርጎ እንደሆነ ባለሥልጣኑ ገልጿል።

በዚህም በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆነና ዕሴት የጨመረ የቅመማ ቅመም ምርት በጥራትና በከፍተኛ መጠን፣ ቀጣይነት ባለው አስተማማኝ ሁኔታ እንዲቀርብ ለማድረግ የወጣው መመሪያ ያግዛል ተብሏል። በተጨማሪም የቅመማ ቅመም ግብይትን ዘመናዊነት፣ ሕጋዊነት እና ፍትሐዊነት በማስፈን የቅመማ ቅመም አምራቶች፣ የግብይት ተዋንያንና የአገሪቱ ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ እንዲያድግ ያስችላል ነው የተባለው።

ባለሥልጣኑ ለአዲስ ማለዳ የላከው ረቂቅ መመሪያ ጠቅላላ ድንጋጌዎች፣ የቅመማ ቅመም ምርት ዝግጅት እና የጥራት ደረጃ፣ የቅመማ ቅመም ግብይትና ጥራት ቁጥጥር አሠራር፣ የግብይት ተሳታፊ ግዴታዎች፣ የብቃት ማረጋገጫ የቴክኒክ መስፈርቶች እና የምስክር ወረቀት አሰጣጥ፣ የቅመማ ቅመም ጥራት እና ግብይት ተቆጣጣሪዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ ደንጋጌዎችን የያዘ ነው።

በመመሪያው ጠቅላላ ድንጋጌ ላይ በተቀመጠው መሠረት ቅመማ ቅመም ማለት የተለያየ ጠንካራ መዓዛ፣ የሚሰነፍጥና የሚለበልብ ባህሪ የያዙ ሆነው ከተለያዬ የተክል ክፍሎች እና ከቅርፊት የሚገኙ ሲሆን፣ ለምግብ ማጣፈጫነት፣ ለመድኃኒትነት፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት ወይም ለጥሩ መዓዛ ሰጪነት የሚያገልግሉ ናቸው።

እንዲሁም በረቂቁ ውስጥ እንደ በርበሬ፣ ዝንጅብል፣ ዕርድ፣ ሔል፣ ነጭ እና ጥቁር አዝሙድ፣ ኮረሪማ፣ ቁንዶ በርበሬ፣ ድንብላል፣ ጥምዝ፣ አብሽ፣ ሚጥሚጣ፣ ሮዝመሪ፣ በሶብላ፣ ሚንት፣ ጦስኝ እና ሰናፍጭ የመሳሰሉ ቅመማ ቅመሞች ትርጓሜ ተካቷል።
የቅመማ ቅመም ጥራት ቁጥጥር ትርጓሜም፣ ቅመማ ቅመም የተፈጥሮ ባህሪውንና ጣዕሙን እንደጠበቅ ለተጠቃሚው ለማቅረብ ከምርት መሰብሰብ ጀምሮ በግብይት፣ በምርት ዝግጅት፣ በአከመቻቸት፣ በማሸግና በማጓጓዝ ሒደት በተፈቀደ የአሠራር ሥርዓትና የጥራት ደረጃ መስፈርት መሠረት ስለመከናወኑ በየደረጃው ባለ ሥልጣን በተሰጠው አካል የሚፈጸም የቁጥጥር ተግባር ማለት ነው።

የቅመማ ቅመም ግብይት ማለትም እንዲሁ፣ ሕጋዊ የግብይት ሥርዓትን በመከተል በመጀመሪያ ደረጃ ገበያ፣ በኹለተኛ ደረጃ ገበያ እና በውጭ ገበያ በቅመማ ቅመም አምራቾች፣ በጅምላ ነጋዴዎች፣ ቸርቻሪዎች፣ ላኪዎች፣ አቀናባሪዎቸና በውጭ አገር ገዥዎች መካከል የሚከናወን የቅመማ ቅመም ግዥና ሽያጭ ሒደት የሚል ትርጓሜ ተሰጥቶታል።

የመጀመሪያ ደረጃ ገበያ ማለት ለቅመማ ቅመም መገበያያነት እንዲሆን አግባብ ባለው የክልል አካል የተከለለ አዲስ ወይም ነባር ተለምዷዊ መገበያያ ስፍራ ሲሆን፣ ኹለተኛ ደረጃ ገበያ ማለትም በቅመማ ቅመም ጅምላ ነጋዴ ወይም ኅብረት ሥራ ማኅበር የቅመማ ቅመም ማዘጋጃና ማከማቻ ቦታ የሚከናወን የቅመማ ቅመም ግብይት ነው።

በረቂቅ መመሪያው ላይ እንዲሁ የእያንዳንዱ ቅመማ ቅመም አዘገጃጀት፣ የጥራት ደረጃ፣ የጥራት መስፈርት፣ አከመቻችትና አጓጓዝ በስፋት ተብራርቷል። የቅመማ ቅመም ግብይትና ቁጥጥር አሠራርን የሚገልጹ ድንጋጌዎችም በመመሪያው ተካተው ይገኛሉ። የቅመማ ቅመም ግብይት ተሳታፊዎች ግዴታ፣ የጥራትና ግብይት ተቆጣሪዎች አመዳደብ ሥልጣንና ተግባር በረቂቁ ከመካተቱ በተጨማሪ፣ በልዩ ልዩ ድንጋጌዎችም የቅመማ ቅመም ሽኝት አሠራር፣ የናሙና አወሳሰድና አፈቃቀድን የሚገልጹ መመሪያዎች ሰፍረዋል።
የዚህን መመሪያ ድንጋጌዎች የሚቃረን ማንኛውም መመሪያ ወይም ልማዳዊ አሠራር በዚህ መመሪያ በተመለከቱት ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው የወጣው ረቂቅ ይገልጻል።

ይህ መመሪያ ከወጣ ከስድስት ወር በኋላ ማንኛውም የቅመማ ቅመም ንግድ ያለብቃት ማረጋገጫ ወረቀት እንደማይካሄድ ረቂቁ የሚገልጽ ሲሆን፣ ይህ መመሪያ ከመውጣቱ በፊት የተሠጠ የብቃት ማረጋገጫ ሠርተፍኬት በባለሥልጣኑ ወይም አግባብ ባለው የክልል አካል በሚሰጠው አዲስ የብቃት ማረጋገጫ ሠርተፍኬት መመሪያው ጸድቆ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስድስት ወራት ውስጥ ይተካል ሲል ይደነግጋል።

በመጨረሻም፣ የተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ ወደ አጽዳቂ አካል ከመላኩ በፊት ባለድርሻ አካላት እንዲያውቁትና አስተያየት እንዲሰጡበት ከተደረገ በኋላ የጸና ይሆናል ተብሏል።


ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here