የአጎዛ ገበያ ማዕከል ማኅበር ነጋዴዎች ወደ ሥራ ቦታቸው ዕቃ ለማስገባት የሚያስችል የመኪና መንገድ ስለተዘጋባቸውና በምትኩ ስላልተገነባላቸው ሥራቸውን በአግባቡ ለማከናወን እየተቸገሩ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ፡፡
ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደተናገሩት ከሆነ፣ የንግድ ማኅበሩ ሥራውን ከጀመረ ከ126 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን፣ የንግድ ዕቃዎችን ጭኖ ለማስገባት የሚያስችል የመኪና መንገድ እንዲገነባላቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም እስካሁን አገልግልቱን ማግኘት አለመቻላቸውን ነው ያሳወቁት፡፡
ወደ መገናኛ የተዘረጋው ባቡር ሐዲድ የገበያ መንገዱን እንደዘጋባቸው ወደ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቢሮ ቅሬታ በማቅረብ አራት ዓመት እንዳስቆጠሩ የአጎዛ ገበያ ማዕከል ምክትል ሰብሳቢ አበባው በየነ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡
ምክትል ሰብሳቢው አክለውም፣ በአጎዛ ገበያ ማዕከል አካባቢ ያሉ ቦታዎች መንግሥት በተደጋጋሚ ሲያለማ የገበያ የልማት ዝርጋታ እያገኙ አለመሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡
የአጎዛ ገበያ አክሲዮን ማዕከል በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ካዛንቺዝ 33 ቀበሌ አካባቢ የሚገኝ የንግድ ማዕከል ሲሆን፣ የተለያዩ የንግድ ሥራዎች በማንቀሳቀስ የሚገኙ 319 የተደራጁ ማኅበሮችን አቅፎ የያዘ ነው፡፡
ገበያ ማዕከሉ የተጀመረው በኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ሲሆን፣ አጎዛ የሚለው ሥያሜ የተሰጠው ከተለያዩ ቦታዎች የበግ ቆዳ እየተሸከመ እያመጣ ለንግድ ሲያቀርብ በነበረው የቀድሞ የገበያው አንቀሳቃሽ ሰው እንደሆነ አበባው በየነ አመላክተዋል፡፡
ገበያ ማዕከሉ የተጀመረው በጉልት መልኩ ነው የሚሉት አበባው፣ ማኅበሩ ብር አውጥቶ ቆርቆሮ በቆርቆሮ የሆኑ ሱቆችን በመሥራት እየተንቀሳቀሰ የቆየ ነው ብለዋል፡፡
አያይዘውም የገበያ ልማቱ እንዲበረታታ የመንገድ ዝርጋታ ለማግኘት ለረጅም ጊዜ ጥያቄ አቅርበው ካርታና ፕላን አቅርቡ ተብለው ማቅረብ ቢችሉም ሥራው እንደተጓተተባቸው ነው የገለጹት፡፡
ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል አፀደ ምላሹ የሚባሉት እናት፣ “አካባቢው ጫካ ነበር፤ ለዛውም ስናረፍድ ኅያ ኀያ ብር እየተቀጣን ሰባት ወር ቆፍረናል፡፡ መሬቱን የሚደለድለውን ዶዘር ሌሊት ሌሊት 11 ቀን ጠብቀናል፤ ቦታውን ለማጽዳት ድንጋይና የሚመነጠረውን ባህር ዛፍ በወገባችን ተሸክመናል፤ እናም እርዱንና መንገዱ ተደራጅቶ ሰው እንሁን” ብለዋል፡፡
እምዬ ፀጋዬ የተባሉት እናት በበኩላቸው፣ 1989 ጥቅምት ወር ጀምረው በሶ፣ ሽሮ፣ በርበሬ እያስፈጩ የባልትና ውጤቶችን በማቅረብ አጎዛ ገበያ ማዕከል ይሠሩ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ኑሮው እየተወደደ በመምጣቱ የባልትና ሥራቸውን ትተው አሁን ብቅልና ጌሾ እየነገዱ እንደሚገኙ የገለጹት እምዬ፤ ወደ ገበያ ማዕከሉ የሚገባ መንገድ አለመኖሩ ለሥራቸው ከባድ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም “በፊት ደህና ነበር፣ አሁን ግን ይከብዳል፤ የባቡር መንገድ ከተሠራ ወዲህ ሰው አይገባልንም መንገድ የለም፡፡ በዛ ምክንያት ችግር አለ” በማለት ነው ቅሬታቸውን ያቀረቡት፡፡
ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መረዳት የተቻለው መንገድ አለመኖሩ ለሽያጭ የሚያቀሩቧቸው ምርቶችን የሚገዛቸው ስለሌለ ሥራው ፈታኝ እንደሆነባቸው ነው፡፡
ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ካቀረቡት ሰዎች መካከል ከ1971 ጀምሮ በገበያ ማዕከሉ እንደሚሠሩ የገለጹት ወይንሸት ደገፋው የተባሉት ነጋዴ ናቸው፡፡
ወይንሸት እንዳመላከቱት ከሆነ፣ ወደ አጎዛ ገበያ ማዕከል ተዘርግተው የነበሩ በፕላዛ በኩል ያሉ መንገዶች የባቡር ሐዲዱ መገንባቱን ተከትሎ በመዘጋታቸው፣ ምርቶቻቸውን የሚገዟቸውን ሰዎች ማግኘት እንዳልቻሉ ነው፡፡
አክለውም “ይሰራላችኋል” የተባለው ድልድይ ቢገነባለቸው ችግራቸውን መቅረፍ እንደሚችል የገለጹ ሲሆን፣ መንገዱ ግን እንዳልተገነባላቸው አመላክተዋል፡፡
አያይዘውም “እኛ ያስቸገረን የመንገዱ ጉዳይ ነው፡፡ በጣም ችግር አለ፤ ምርቶቹን የሚገዛን የለም፤ መንገድ አለመኖሩ ነው ተጽዕኖ ያሳደረብን፡፡ መንገድ ከሌለ ምርቶችችንን ማን ይገዛናል? አስፓልት ግዴታ ያስፈልገናል” ሲሉ ነው ቅሬታቸውን ያቀረቡት፡፡
የመኪና ብቻ ሳይሆን በእንደራሴ በኩል ብቻ ያለው መንገድ እንጅ ሌላው ስለተዘጋ የሰው መንገድም የለም የሚሉት ወይንሸት፤ መንገዱ ቢከፈት ለውጥ እንደሚያገኙ አብራርተዋል፡፡
አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት ወደ አዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር እያሱ ሰለሞን ስልክ የደወለች ሲሆን፤ ዳይሬክተሩ እስካሁን በዚህ ጉዳይ ቅሬታ ያቀረበልን ኣካል የለም በማለት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ጥያቄያቸውን ያቅርቡና እንደማንኛውም ዜጋ ለችግራቸው መፍትሔ እንሰጣለን ብለዋል፡፡
ቅጽ 3 ቁጥር 156 ጥቅምት 20 2014


