የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በ 19/2/2014 ራሳቸውን የልደታ ክፍለ ከተማ አፍራሽ ግብረ-ኃይል ነኝ ባሉ የፖሊስና የደንብ አባላት ከጠዋቱ 12 ሰዓት መፍረሱን አዲስ ማለዳ በቦታው ተገኝታ መዘገብዋ ይታወሳል። አፍራሾቹ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ማዘዣ ሳያቀርቡ የጽሕፈት ቤቱን ጥበቃ በመሣሪያ በማስፈራራትና ጽሕፈት ቤቱን ገንጥለው በመግባት የጣሪያውን ቆርቆሮ አንስተው ማፍረሳቸውን አዲስ ማለዳ በወቅቱ ለአንባቢ አድርሳለች።
ቀይ መስቀል ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ማኅበር እንደመሆኑ መጠን በየአገሩ ቅርንጫፍ የሚከፈተው በዐዋጅ እና በደንብ በተቀመጠ ሕጋዊ መሠረት ነው። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በሐምሌ 8/1935 በነጋሪትጋዜጣ በተደነገገው ዐዋጅ መሠረት ኢትዮጵያ 48ተኛው የቀይ መስቀል አባል አገር ሆና መመዝገቧ በታሪክ ይነገራል። በኃይለሥላሴ ዘመን ከጣሊያን ወረራ በኋላ በዐዋጁ መሠረት እውን ያደረገችው ይህ ተቋም፣ዓለም አቀፋዊ የሰው ልጆችን በተለይ ከጤና ጋር በተያያዘ ለመድረስ ታስቦ የተቋቋመ ሰብዓዊ ድርጅት ነው።
ድርጅቱ የተቋቋመ በዋናነት በጣሊያን ወረራ ጊዜ ኢትዮጵያን ለመታደግ ለ 5 ዓመት ሲታገሉ እና ሲቆስሉ ለነበሩት ጀግኖች አባቶች የሕክምና ዕርዳታ እንዲደርሳቸው ለማድረግ ነበር። በወቅቱ የቀይ መስቀል አባላት በትግሉ የቆሰሉትን በማከምና የሞቱትን በመቅበር ከፍተኛ ሰብዓዊ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበረ የአሁኖቹ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ የቀይ መስቀል ማኅበር የቦርድ አባላት ይናገራሉ። ከተቋቋመ ወደ 86 ዓመት ያስቆጠረው ይህ ተቋም፣ በርካታ ሰብዓዊ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሆነ ይስተዋላል። የበላይ ጠባቂውም የአገሪቱ መንግሥት እንደመሆኑ መጠን፣ የኢትዮጵያ የቀይ መስቀል ማኅበር በኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ የበላይ ጠባቂነት እየተመራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በመላው አገሪቱ በሁሉም ክልሎች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ከፍቶ ለሕዝቡ የአምቡላንስ እና ሌሌች ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች እየሰጠ እስከ ዛሬ ድረስ ቆይቷል። 5 ሚሊዮን አባላት እንዳሉት የሚነገረው ይህ ተቋም፣ በአዲስ አበባ ብቻ ከ 130 ሺሕ በላይ አባላት አሉት። ከአባላቱ የተውጣጡ የቦርድ አባላት የተቋሙን ተግባራት በቅርብ እየተከታተሉ ሥራውን ያግዙታል።
በ19/2/2014 በአፍራሽ ግብረ ኃይሉ የፈረሰው የአዲስ አበባው የቀይ መስቀል ጽሕፈት ቤት ከ1973 ጀምሮ ለሕብረተሰቡ ዘርፈ ብዙ ሰብዓዊ ግልጋሎት ሲፈጽምበት ቆይቷል። በተለይ ነጻ የአምቡላንስ አገልግሎት በመስጠት ረገድ ለሕብረተሰቡ ፈጣን ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ ይስተዋላል። በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት አደጋ በሚደርስ ጊዜ በቦታው በመገኘት አስፈላጊውን ሰብዓዊ ዕርዳታ ያደርጋል። በዚህ አገልግሎቱ ለ 41 አመት ዘልቋል።
በግብረ ኃይል እንዲፈርስ የተደረገው ቤት የጀነራል ታደሰ ብሩ መሆኑን በሥሩ የሚገኙ ሠራተኞች ይናገራሉ። ታዲያ ተቋሙ ለምን እንዲፈርስ ተፈለገ በሚለው ጉደይ ላይ አዲስ ማለዳ ሠራተኞቹን እና የቦርድ ሰበብሳቢዎቹን ለማነጋገር ሞክራለች።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአዲስ አበባው የቀይ መስቀል ሠራተኛ፣አፍራሽ ግብረ ኃይሉ በ 19/2/2014 ከጠዋቱ 12 ሰዓት በመምጣት ቤቱን ማፍረሱን ይናገራሉ። ጋራዡን፣ የሥልጠና ማዕከሉን፣ የዕርዳታ ቁሳቁስ ማስቀመጫዉን ካፈረሱ በኋላ በሕዝቡና በሠራተኛው ተቃውሞ አፍራሽ ግብረ ኃይሉ ወደመጣበት ሊመለስ መቻሉን ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። አክለውም፣ “በዚሁ ዕለት ከቀኑ 6 ሰዓት ተመልሰው መጥተው ለማፍረስ ሲሞክሩ በተመሳሳይ ተቃውሞ ስለገጠማቸው ለኹለተኛ ጊዜ ሳይሳካላቸው ቀርቷል” በማለት ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል። ቀይ መስቀል ማኅበር ግቢ ውስጥ ምንም ዓይነት የጦር መሣሪያ ይዞ መግባት እንደማይፈቀድ ዓለም አቀፍ ሕግ እንደሚደነግግ እየታወቀ፣ ፖሊሶች እና የተደራጁ የአፍራሽ ግብረ ኃይሉ አባላት ጥበቃውን በጦር መሣሪያ በማስፈራራት ሲገቡ እና የሕንጻውን ጣሪያ ሲገነጥሉ አዲስ ማለዳ በቦታው ተገኝታ ለመታዘብ ችላለች።
አስተያየት የሰጡን የማኅበሩ ባልደረባ እንደሚሉት፣ ቀይ መስቀል ማኅበሩ በተለይ ከተለያዩ አረብ አገራት ተባርረው ለሚመጡ ወገኖች አልባሳት፣ ጫማዎች፣ ብርድልብስ፣ ፍራሽ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመለገስ አለኝታነቱን ከ 2009 ጀምሮ በሥራ አስመስክሯል። ይሁን እንጂ፣ ለሠራተኞቹ መረጃ ባልተሰጠበት ኹኔታ፣ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ባልቀረበበት መንገድ፣ እንደ ወንበዴ ሌሊት መጥቶ ቤቱን ማፍረሱ በጣም አሳፋሪ እና ኃላፊነት ከሚሰማው አካል የማይጠበቅ ድርጊት እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አክለውም ‹አልሳም ግሩፕ› ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ማስፋፊያ ቦታውን ስለፈለገው ብቻ የሰብዓዊ ድርጅትን ማፍረስ አግባብ እንዳልሆነ አጽንዖት ሰጥተው ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።
አልሳም ግሩፕ የተባለው ድርጅት ከዚህ ቀደም፣ ከቀይ መስቀል ጽሕፈት ቤት ጀርባ ያለውን ቦታ ለመኪና ማቆሚያ ተከራይቶት የነበረ ቢሆንም፣ ቦታውን ይህ ድርጅት እንደወሰደው ሠራተኛው ለአዲስ ማለዳ አልደበቁም። “ኃላፊነት የማይሰማው ባለሀብት ትርፉን ለማጋበስ ብቻ የሆነ ቦታ ፈልጌአለሁ ባለ ቁጥር ከተሰጠው፣ ለድሀው የሚቆመው መሪ ማን ነው?” በማለት ይጠይቃሉ። “ይሄው ድርጅት ከዚህ በፊት የወሰደው ቦታ ሳይበቃው፣ አሁን ደግሞ ዋናውን ቀይ መስቀል ለመውሰድ በግብረ ኃይል አስፈረሰ” በማለት ትዝብታቸውን ተናግረዋል። የጀነራል ታደሰ ብሩ ቤት መሆኑ የሚነገርለት ቀይ መስቀል ጽኅፈት ቤት እንደቅርስ ተቆጥሮ መጠበቅ ሲገባው፣ ባለሀብት ስለፈለገው ብቻ መስጠት ከታሪክ ተወቃሽነት አያድንም በማለት ሠራተኛው ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። አያይዘውም፣ “የኢትዮጵያ የባህልና የቅርስ ጥናት መሥሪያ ቤቶች ምንድን ነው ሥራቸው?” ሲሉ ይጠይቃሉ።
“ጽሕፈት ቤቱ በሚፈርስበት ወቅት ስልኩ በመቆረጡ ምክንያት፣በወቅቱ የሐና ትምህርት ቤት ተማሪዎች በምግብ መበከል በሚል ምክንያት በታመሙበት እና አምቡላንስ ባስፈለገበት ወቅት በጊዜው ለመድረስ እንዳልቻሉ፣ነገር ግን ዘግይቶም ቢሆን ሰዎች በአካል በመምጣት ስለነገሯቸው 10 አምቡላንሶች ወደ ቦታው ልከው ልጆቹን ወደ ሕክምና ማድረስ መቻላቸውን” በማንሳት የጥፋቱን ጥግ በምሳሌ አስረድተዋል። ታዲያ ይሄን ለትርፍ ያልተቋቋመ የሰብዓዊ አገልግሎት ተቋም ለማጥፋት መሮጥ ምን የሚሉት ኃላፊነት የጎደለው ምግባር ነው? በማለት ትዝብታቸውን ለአዲስ ማለዳ አካፍለዋል።
አዲስ ማለዳ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ቀይ መስቀል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ የሆኑትን አቶ እስራኤል ገሰሰ በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ጠይቃቸዋለች። በምላሻቸውም፣ ጉዳዩ ከመንገድ የወጣ እና የሕግ አግባብ የሌለው መሆኑን ገልጸው፣ በ ቀን 23/2/2013 ከአዲስ አበባ መስተዳደር ጋር በመነጋገር እስከ ሰኔ 30/2014 ድረስ ግቢውን ለቅቀን መውጣት እንዳለብን ተስማምተናል ብለዋል። “በምትኩ የአዲስ አበባ መስተዳድር ተተኪ እና በርካታ አምቡላንሶችን ሊይዝ የሚችል ቦታ እንደሚሰጠን ተስማምተን ጉዳዩን ቋጭተነዋል” በማለት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ቦታው የቀድሞው የኢትዮጵያ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ አዛዥና ኔልሰን ማንዴላን የወታደር ትምህርት በመስጠት የሚታወቁት ጉምቱው የአገራችን ባለውለታ ጀነራል ታደሰ ብሩ የነበረ በመሆኑ መፍረስ የለበትም በማለት የቦርድ ሰብሳቢው አቶ አዳሙ አግድ ከሌሎች አባላት ጋር በመሆን ውሳኔውን ለመቀልበስ አዲስ ኮሚቴ በማዋቀር ላይ እንደሚገኙ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
በ 24/2/2014 የጽሕፈት ቤቱ የቦርድ አባላት ለ 4 ሰዓት የቆየ ስብሰባ አካሂደው የአዲስ አበባ አስተዳደር ውሳኔ በሥራ አስኪያጁ በአቶ እስራኤል በኩል ቢነገራቸውም፣ ቅርስ እንዲፈርስ ፍጹም እንደማይስማሙ ለሥራ አስኪያጁ በመንገር ስብሰባውን ለማቋረጥ እንደተገደዱ አቶ አዳሙ አግድ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። አዲስ ማለዳም ቀጣይ ዕቅዳቸው ምን እንደሆነ ጠይቃ ተከታዩን መልስ አግኝታለች። “አዲስ የተቋቋመው ኮሚቴ በየ 3 ቀኑ እየተገናኘ ዕቅድ ያወጣል፤ ለሚመለከተው አካል ጉዳዩን ያደርሳል፤ በመቀጠል መሻሻሉን ለኮሚቴው ያስረዳል” በማለት ገልጸዋል። ቀጥለውም በአዲሱ ኮሚቴ የተዘጋጀ ደብዳቤ ለኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለአዲስ አበባ ምክር ቤት፣ ለመሬት አስተዳደር፣ ለባህል ሚኒስቴር፣ ለሰላም ሚኒስቴር፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለሌሎች ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በማስገባት እስከመጨረሻው እንደሚታገሉ እና ቅርሱን ከመፍረስ እንደሚታደጉት በአጽንዖት ገልጸዋል።
በአንድ ወቅት የጀነራል ታደሰ ብሩ ልጆች ከአሜሪካ መጥተው ቤቱን ለመውሰድ ሲሞክሩ፣ ቀይ መስቀል እየተጠቀመበት መሆኑን በመረዳታቸውና ቤቱ ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት መዋሉ የአባታቸውን ስም የሚያስጠራ ተግባር በመሆኑ ተደስተው እንደተመለሱ አቶ አዳሙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አክለውም አገር ወዳድ እንኳን የአገር ቅርስ ለማፍረስ ይቅርና የራሱንም ለሰብዓዊ አገልግሎት ይሰጣል። ሌሎች ደግሞ የራሳቸውን ትርፍ ለማበርከት ከራሳቸው ቦታና ድርሻ አልፈው የአገር ቅርስ ለማጥፋት ሌት ተቀን ይሠራሉ በማለት በአልሳም ግሩፕ ባለቤትና በጀነራል ታደሰ ብሩ ልጆች መካከል ያለውን የሰብዕና ልዩነት ለማስረዳት ሞክረዋል።
ሌላው የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ሠራተኛ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ሲገልጹ፣ የአልሳም ግሩፕ ባለቤት የጋራ መኖሪያ ሕንጻው ከቀይ መስቀል ቢሮ ራቅ ያለ ከመሆኑ የተነሳ በመሀል የካቶሊክ ቤተክርስቲያን እና ወንዝ እንዳለ ተናግረው፣ ቀይ መስቀልን በምን ስሌት መውሰድ እንደፈለጉ እስካሁን ድረስ እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው አስረድተዋል። የአገር ዕድገት ዕውን የሚሆነው ቅርስን በማጥፋት ሳይሆን የነበረውን ከትውልድ ትውልድ በማስተላለፍ፣ቅርስ ወይም ታሪክ የሚሆን አዲስ ሥራ በመሥራት ብቻ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በዚህ ጉዳይ አዲስ ማለዳ የቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ተጠሪን ዶ/ር ሰለሞንን ለማነጋገር ቢሮ ድረስ ብትሄድም ማግኘት አልቻለችም።በተደጋጋሚ በእጅ ስልካቸውም ለማናገር ብትሞክርም አልተሳካላትም።
ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014



