የመንገዶች መዘጋት የፈጠረው ውስብስብ ችግር እና መፍትሔው

0
979

አዲሱ በላይ ይባላል። ተወልዶ ያደገው በአማራ ክልል ውስጥ በምትገኘው ወልዲያ ከተማ ነው። ሆኖም ግን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ወልዲያን ከተቆጣጠረበት የሐምሌ ማገባደጃ ወር (2013) ጀምሮ ወደ ደሴ ከተማ በማቅናት ይኖር ነበር። የተፈናቀለው የህወሓት ታጣቂዎች ከሚሠነዝሩት ጥቃት ለማምለጥ እንደሆነ ተናግሯል።

አዲሱ፣ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን አያሌ ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፈ ያወሳል። ከእነዚህም መካከል የመንገድ መዘጋት ችግር አንዱ ነው። ወጣቱ እንደሚለው ከሆነ፣ ሰሞኑን ከደብረ ብርሃን ከተማ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ መዘጋቱን ተከትሎ በፈተና ውስጥ መቆየቱን ይናገራል። አዲሱ በላይ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ፣ መንገድ መዘጋጋቱ መልካም ጎን ቢኖረውም ለተፈናቃዮች ደግሞ ፈታኝ ችግር እንደሆነ ይገልጻል።

አዲሱ ገና ከመጀመሪያው አካባቢውን ለቆ የወጣው፣ “እባክህ ለዘር ትረፍልን” እያሉ ሰላም ወዳለበት አካባቢ እንዲሄድ በተደጋጋሚ ጥያቄ የሚያቀርቡለት የቤተሰቦቹ የዕለት ተዕለት ተማጽኖ ስለተደራረበበት ነው። ወጣቱ ወደ ደሴ ከተማ አቅንቶ ይኖር የነበረው ቤት ተከራይቶ የነበረ ሲሆን፣ ተከራይቶ ለመኖር የወሰነውም በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች በሰዎች ጢም ብለው በመሙላታቸው እንደሆነ ይናገራል።

የተከሰተውን ችግር ለመቋቋም የሚፍገመገመው አዲሱ በላይ፣ ከቤተሰቦቹ ጋር ተለያይቶ በደሴ ከተማ መኖር ከጀመረ ከሦስት ወር በላይ ሆኖታል። በመሆኑም የብር ዕጥረት ስለነበረበት፣ እንዲሁም በየጊዜው በማኅበራዊ ሚዲያ የሚለፈፈው “ንጹኃን ተጨፈጨፉ” የሚባለው ወሬ ሰላሙን ስለነሳው ወደ ቤተሰቦቹ መመለስ እንዳለበት ወስኖ ነበር።

ነገር ግን ወደ ወልዲያ ሊያስገባው የሚችል መንገድ ማግኘት ምኞት ብቻ ሆኖ ቀርቶበታል። ለዚህም ምክንያቱ የመንገዶች መዘጋት እንደሆነ አመላክቷል። በጭንቀትና በችግር እየተናጠ ያለው አዲሱ በላይ ውሎ አድሮ አንድ መረጃ ደርሶት ነበር። ይኸውም ከደሴ ከተማ በአፋር ክልል በኩል ተጉዞ ዞብል በሚባለው ተራራ አድረጎ ወደ ቆቦ ከተማ መግባት እንደሚችል ነው።

ወደ ቆቦ ከተማ መሄድም አንዱ መልካም አጋጣሚ እንደሆነለት ይናገራል። ለዚህም ምክንያቱ ባሳለፍነው ጰጉሜ 4/2013 በቆቦ ከተማ በህወሓት ታጣቂ ከተገደሉት ከ600 በላይ ንጹኃን መካከል በከተማው የምትገኝ አክስቱ የጥቃቱ ሰለባ ሆና ይሆን? የሚለውን ምላሽ ያላገኘለት ጥያቄ በአካል ተገኝቶ ለማረጋገጥ ስለሚያችለው ነው።

“በአንድ ድንጋይ ኹለት ወፍ” እንዲሉ በቆቦ ከተማ የምትኖር አክስቱን ጎብኝቶ በዚያውም እናትና አባቱ ወዳሚኖሩበት ወልዲያ ከተማ ለማቅናት አስቦ እንደነበር ነው የገለጸው።
አዲሱ ውሳኔውን ወደ ተግባር በመቀየር በመስከረም የመጀመሪያ ሳምንት መነሻውን ደሴ ከተማ በማድረግ ወደ ቆቦ ተጉዟል። የተሳፈረበት መኪና ለተፈናቃዮች ዕርዳታ የያዘ ተሸከርካሪ ስለነበር ዕቃ ጋር ተደርቦ ከመጫኑ በተጨማሪ በየኬላው ያለው ከመጠን ያለፈ ፍተሻ ጎዞውን አስልችና አድካሚ እንዳደረገው ደጋግሞ ያወሳል።

ቤተሰቦቹ ላይ የሰነቀው ተስፋ የጉዞውን ድካም እያረሳሳለት በእልህና በወኔ የተጓዘው ወጣቱ፣ የአፋር ክልልን አልፎ ከሰንሰላታማው የዞብል ተራራ ደረሰ። ለአፍታ ዕረፍትን ሳይሻ የእግር ጎዞውን ወደ ቆቦ ተያያዘው። ወደ ቆቦ ከተማ ሊገባ ሲል ወጣቶች በህወሓት ታጣቂዎች እየታደኑ እንደሆነ ወሬ ሰማና የያዘውን ስልክና 1ሺሕ ብር በማሽላ ውስጥ ደብቆ ጉዞውን ቀጠለ።

ወጣቱ ከእልህ አስጨራሹ የሦስት ሰዓት የእግር ጉዞ በኋላ ቆቦ ከተማ ገብቷል። የሰነቀው የጉዞ ተስፋ ግን ፍጻሜው አሳዛኝ እንደነበረ ተናግሯል። አክስቱን ከሙሉ ቤተሰቦቿ ጋር ሊያገኛት አልቻልም።
አድራሻቸው ወዴት እንደሆነ ጎረቤት ሲያጠያይቅ፣ “ወደየት እንደሄዱ ባናቅም ተሰባስበው ሲወጡ አይተናቸዋል። አንተ ከዚህ አካባቢ መታየት የለብህም፤ ወጣቶች እየታደኑ እየተረሸኑ ነው” የሚል ዜናን አበሰሩት።

በከተማው ወጣት ማየት አልቻለም፤ በአካባቢው የሚያስተውለው የፈራረሱ ሕንጻዎችን ከመሆኑም በላይ ወደ ወልዲያ ማለፊያ መንገድ አላገኘም። ሁኔታው ያስፈራው አዲሱ ወደ ወልዲያ የመሄድ ተስፋው ተሟጦ፣ በሄደበት መንገድ ተመልሶ ወደ ደሴ ከተማ መጥቶ የቀን ሥራ እየሠራ ኑሮውን መግፋት ጀምሮ ነበር።

ይህ በእንዲህ እያለ ህወሓት ውጫሌን፣ ውርጌሳን፣ ሐይቅን አልፈው ወደ ደሴ በሚያደርጉት ጉዞ ሕዝቡ ሲሸበር እንደተመለከተ ይናገራል። ባሳለፍነው ሳምንት (የጥቅምት ሦስተኛ ሳምንት 2014) ደሴ በከባድ መሳሪያ ተኩስ ስትታወክ ተመልክቻለሁም ብሏል።
ኹኔታው ያስፈራው ወጣቱ ወደ መዲናዋ ለመምጣት ወሰነ። ትራንስፖርት ከመወደዱም በላይ ማግኘቱ ከባድ ቢሆንም፣ ዕድል ገጥሞት 1ሺሕ ብር ከፍሎ ጉዞውን ጀመረ። ነገሮች ግን አሁንም ተወሳስበውበታል። ደብረ ብርሃን ከተማ እንደደረሰ፣ “ወደ አዲስ አበባ ማለፍ አይቻልም” ተብሎ መኪናው ከኬላ ማለፍ እንዳልቻለ የአይን እማኝነቱን ተናግሯል።

በመሆኑም ለወራት ያስተናገደው የሽሽት ሕይወት መጨረሻው ትርፉ ድካም እንደሆነበት ተናግሮ፣ “አሁንስ መሰደድም አይቻልም እንዴ? እዚሁ ታፍነን እንድንሞት የተፈቀደ ይመስላል። እስከመቼ ነው ይህ የሚሆነው?” ሲል ጠይቋል።
ወጣቱ በመጨረሻም የመንገዶቹ መዘጋጋት፣ “የህወሓት ታጣቂ ሰላዮች ተመሳስለው ወደ ከተማ እንዳይገቡ” ለማድረግ በመታሰቡ እየተፈጸመ እንደሆነ በመስማቱ፣ የሚፈጸምን ጥቃት ለመቀነስ መፍትሔ ቢኖረውም፣ “ወደ አዲስ አበባ አታልፉም” የተባሉት በርካታ ተፈናቃዮች ባሉበት የሚመለከተው አካል ጥበቃና እርዳታ ሊያደርግላቸው ይገባል ሲል ነው አስተያየቱን የሰጠው።

አገራችን ኢትዮጵያ ጦርነት ማመስ ከጀመራት ባሳለፍነው ጥቅምት 24/2014 ድፍን አንድ ዓመት አስተቆጥራለች። በዚህም ምክንያት በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች በተለይም በኦሮሚያ፤ በአፋርና በአማራ ክልል አካባቢዎች የሚገኙ በርካታ ዜጎች ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ ቤት ንብረታቸውን እንደተዘረፈና በርካቶችም አካባቢያቸውን ለቀው እንደተፈናቀሉ ከተሰማ ሰንበትበት ብሏል።

የገፈቱ ቀማሾች የሚናገሩት፣ እንደዋዛ ከቤታቸው ተፈናቅለው በመውጣት እየከፈሉት ያለው መስዋዕትነት ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መምጣቱን ነው። ለችግራቸው መባባስ እንደምክንያት የሚያነሱት መካከል አንዱ የመንገዶችን መዘጋጋት ነው። ይህ ለሕይወታቸው አስጊ ከመሆኑም በተጨማሪ ባሉበት ቦታ የመሠረታዊ ፍጆታዎች ዕጥረት እንዳስከተለባቸው ይናገራሉ።

መንገድ ተዘጋብን ከሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች መካከል ሻምበል ዘውዱ የተባሉት ግለሰብ አንዱ ናቸው። ሻምበል ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ቢያስቡም ከደብረ ብርሃን ወዲህ ማለፍ እንዳልቻሉ የጠቆሙ ሲሆን፣ አታልፉም የተባሉበት ምክንያትም “ሠርጎ ገቦች” ተመሳስለው ሰላም ወዳለበት አካባቢ እንዳይገቡ ታስቦ መሆኑን ግልጸዋል።

“ሠርጎ ገቦችን” ለመከላከል የተወሰነው ውሳኔ የሚያስከፋ አይደለም የሚሉት ሻምበል፣ ወደ መዲናዋ ለማቅናት መጥተው አታልፉም የተባሉ በርካታ ተፈናቃዮች እንዳሉ ጠቁመዋል። አያይዘውም “አታልፉም ከተባልን ቢያንስ እንኳ የሚመለከተው አካል የመጠለያና የምግብ ዕርዳታ ሊያደርግልን ይገባል” ሲሉ ነው ያሳሰቡት።

ሌላኛው ጥላሁን በላይ የተባለው ወጣት፣ ‹‹በእርግጥም መታገዳችን ሠርጎ ገቦችን ለመከላከል ከሆነ መልካም ነው። ሲጀመርም ጥቃቱን መከላከል ነበረብን እንጂ፣ ቀያችን አስረክበን መምጣት አልነበረብንም›› በማለት ነው የተናገረው። ወጣቱ በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ አበባ የሚኖር ወንድሙ ሰሞኑን ወደ ደብረ ብርሃን በማለፍ ቤተሰብ ሲጠይቅ ቆይቶ ባሳለፍነው ሳምንት (የጥቅምት አራተኛ ሳምንት) ወደ ቤቱ ለማቅናት የአዲስ አበባ ነዋሪነቱን የሚገልጽ መታወቂያ ቢያሳያቸውም ኬላ ላይ ማለፍ እንዳልቻለ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

ጥላሁን፣ አክሎም መንገድ የተዘጋው “ሠርጎ ገቦች” እንዳይገቡ ታስቦ ከሆነ፣ ነዋሪነታቸው የታወቀ ግለሰቦች ለምን ይታገዳሉ? በማለት ጠይቋል። ነዋሪነታቸው የተረጋገጠ ግለሰቦች እንዲያልፉ ቢደረጉ፣ ቀሪዎቹ ሰዎች ደግሞ ጥበቃና ድጋፍ ቢደረግላቸው የተሻለ ነው ሲል ነው አስተያየቱን የሰጠው።

ሌላኛው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ እናት፣ “ይህኮ በሕይወት የመቆየት ጉዳይ ነው። ልጆች ይዘን ከወደ ኋላ ጥቃት እየተሰነዘረብን፣ ከወደፊት መንገድ ተዘግቶብን፣ እንዴት እንሁን?” ሲሉ ጠይቀዋል። አክለውም፣ እንዳያልፉና ባሉበት እንዲቀመጡ መደረጉ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ መንግስት፣ መከላከያ፣ ልዩ ኃይል እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብ ጥበቃና ዕርዳታ ይለግሳቸው ዘንድ በተስፋ እንደሚጠባበቁ ገልጸዋል።
በአካባቢው ያሉ ቅሬታ አቅራቢዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ ከደብረ ብርሃንና ከሸኖ ወደ አዲስ አበባ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ወደ ሸኖ ማለፍ እንዳልቻሉ ነው ያመላከቱት።

በሌላ በኩል፣ ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ ሰዎች መንገድ ተዘግቶብናል በማለት የድረሱልን ጥሪ ቢያቀርቡም፣ ገፈቱን ከመቅመስ እንዳልዳኑ አዲስ ማለዳ ስትዘግብ መቆየቷ የሚታወስ ነው። ታዲያ አሁንም ቢሆን መንገድ መዘጋቱን በማስመልከት ተመሳሳይ ቅሬታ የሚያነሱ ሰዎች አሉ።

“አታልፉም ተብሎ መንገድ መዘጋቱ ጥላትን ለመለየት የማያሻማ ምርጫ ነው። እስካሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ሲታይ ቤታችንን አንለቅም ብለው ለጥቃቱ እራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ሰዎች ተገቢው ጥበቃ አልተደረገላቸውም” የሚሉት እያሱ አያሌው ናቸው።
አይይዘውም፣ ባሳለፍናቸው የክረምት ወራት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን የሚገኙ የአንገር ጉትን፣ የኪረሙ እና የሌሎች አካባቢ ነዋሪዎች ሰላም ወዳለበት አጎራባች ቦታ እንዳያልፉ “በኦነግ ሸኔ” መንገድ እንደተዘጋባቸው ቢያመላክቱም፣ መፍትሔ ሳያገኙ ለጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎችን አውቃለሁ በማለት ነው ዕማኝነታቸውን የተናገሩት።

እያሱ አክለውም፣ ባሳለፍናቸው ወራት በሽብርተኝነት የተፈጀው ህወሓት (በአፋርና በአማራ ክልል)፣ እንዲሁም “ኦነግ ሸኔ” ኦሮሚያ ክልል ወረዳዎች ባደረሱት ጥቃት ዜጎች ቀድመው ድረሱልን ቢሉም የገፈቱ ቀማሾች ከመሆን አልዳኑም ነው ያሉት።
ለአብነት ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ወረዳዎች ወደ አማራ ክልል እንዳንሄድ መንገድ ተዘግቶብናል ሲሉ የነበሩ ዜጎች ምንም መፍትሄ እንዳላገኙ ያመላከቱ ሲሆን፣ አሁንም ቢሆን ጥቃት የሚሰነዘርበት አካባቢ ያሉ ሰዎች “ጦርነቱ እየተቃረበ ነው” በሚለው ወሬ በመሸበር አካባቢያቸውን ለቀው የሚሰደዱት፣ ጥበቃ ያላገኙ ሰዎች ዕጣ ፈንታ እንዳይደርስባቸው በመሥጋት ነው ሲሉ ነው የተገነዘቡትን የተናገሩት።

እያሱ አያሌው በመጨረሻም መንገድ መዘጋቱ ከሚያመጣው መፍትሔ በተጨማሪ፣ እንዳያልፉ ለታገዱ ሰዎች ጥብቅ ጥበቃ ማድረጉም ሊሰመርበት ይገባል ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡት።
በሌላ በኩል መንገድ መዘጋቱ፣ ተመሳስለው የሚመጡ የህወሓት ሰላዮችን ዕድል ለመዝጋት ታስቦ ከሆነ፣ እስካሁንም መደረግ የነበረበት ወሳኝ ተግባር ነበርና አሁንም መወሰኑ መልካም ነው የሚሉት የእናት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ጌትነት ወርቅነህ ናቸው።
ሽብርተኛ የተባለው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የማይከረክመው ዘዴ፣ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም የሚሉት ጌትነህ ወርቅነህ፣ ሰላዮች ተመሳስለው በመግባት ጥቃት ለመሰንዘር እንደሚያስቡ የማያሻማ እውነታ መሆኑን በመግለጽ፣ መንገዶችን ዘጋግቶ ማጣራቱ መልካም ተግባር ነው ብለዋል።

አያይዘውም፣ ህወሓት አሁን ካለበት ደረጃ ለመድረሱ፣ እስካሁንም ቢሆን ሰላዮችን ቀድሞ በመላክና መቆጣጠር የሚፈልጋቸውን ቦታዎች በእጁ ከማስገባቱ በፊት “ዛሬ ተቆጣጥሬአለሁ” ብሎ ሕዝቡን ማሸበር ከእኩይ ተግባሮቹ መካከል የሚጠቀስ መሆኑን አመላክተው፣ መንገድ የተዘጋው ይህን ሴራውን ለማክሸፍ ከሆነ ተመራጭ ውሳኔ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ መንገድ መዘጋጋቱን የሚነቅፉ ያሉ ሲሆን፣ ለዚህም እንደምክንያት ያቀረቡት ሰላም ወዳለበት አካባቢ “አታልፉም” የተባሉት ዜጎች ባሉበት ቦታ በቂ የምግብ፣ የመጠለያ፣ እንዲሁም የመድኃኒት ዕርዳታ እየደረሳቸው አለመሆኑን በማስተዋላቸው ነው።
በወቅቱ የሚስተዋለው የዜጎች መፈናቀል “በሕይወት የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው” የሚሉት ጌትነት ወርቅነህ፣ ችግር ደርሶብናል ብለው አካባቢያቸውን ለቀው የሚመጡ ሰዎች አታልፉም ተብለው ከታገዱ፣ መንግስት፣ መከላከያ ሠራዊት፣ ጋዜጠኛ፣ በአገር ውስጥም ውጭም ያሉ የዕርዳታ ድርጅቶች እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብ ተፈናቃዮች ባሉበት አካባቢ ሁሌም ድጋፍ ሊያደርጉላቸውና ሊጎበኟቸው ይገባል ሲሉ ነው ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ የመፍተሔ ሐሳብ ያሉትን ያካፈሉን።


ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here