ዳሸን ባንክ “ዳሸን አሜሪካን ኤክስፕረስ” የተሰኘ አለም ዓቀፍ የ“ዴቢት” አገልግሎት ካርድ ሥራ ላይ ማዋሉን አስታወቀ።
ዳሸን ባንክ ከአሜሪካን ኤክስፕረስ ጋር በመተባበር ዳሸን አሜሪካን ኤክስፕረስ የተሰኘ አለም ዓቀፍ የዴቢት አገልግሎት ካርድ ለደንበኞቹ ማቅረቡን ገልጿል። የአገልግሎት ካርዱ ከኢትዮጵያ ዉጭ በተለያየ የአለም ክፍል ለንግድ ሥራ የሚጓዙ ደንበኞች ግብይታቸዉን በዉጭ ምንዛሬ ለመፈጸም የሚያስችል መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ለተጠቃሚ ደንበኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው ተብሏል።
ዳሸን አሜሪካን ኤክስፕረስ ለአለም ዓቀፍ ተቋማትና ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሬ ፍሰት ለሚያስተናግዱ ተቋማት ቀልጣፋ አገልግሎት የሚሠጥ ካርድ ነዉ ተብሏል። ደንበኞች ከኢትዮጵያ ዉጭ ሆነዉ ከዉጭ ምንዛሬ አካዉንታቸዉ በቀላሉ ገንዘብ በማዉጣት ግብይት መፈጸም እንደሚችሉ ባንኩ ገልጿል። እንዲሁም ከጥሬ ገንዘብ ዉጭ ግብይት ለመፈጸም ዕድል እንደሚፈጥር የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ከሥጋት ነጻ ሆነዉ የፈለጉትን ያህል ገንዘብ በመጠቀም በአለም ዓቀፍ የአሜሪካን ኤክስፕረስ የኤቲኤም ኔትወርክ በኩል የንግድ ሥራዎቻቸዉን ማከናወን ያስችላል ተብሏል።
ማንነቱን የሚገልጽ ሕጋዊ ማስረጃዎችን ማቅረብ የሚችልና አለም ዓቀፍ የገንዘብ ዝዉዉር ማዕቀብ ያልተጣለበት ማንኛዉም ግለሰብም ሆነ ተቋም ካርዱን መጠቀም እንደሚችል ተጠቁሟል።
ዳሸን ባንክ የዘርፉ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ዕድገትና የሕግ ማሻሻያዎች የፈጠሩትን ዕድል በመጠቀም ጥራት ያለዉ አገልግሎት በመስጠት እና የዘርፉን የፈጠራ ዉጤቶች በማቅረብ ሁሌም ቀዳሚ ሆኖ እንደሚቀጥል የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስፋዉ አለሙ ገልጸዋል።
ባንኩ ያስተዋወቀው የአገልግሎት ካርድ በዉጭ ለሚጓዙ ኢትዮጵያዉያን በቀላሉ ክፍያ ለመፈጸም እንዲችሉ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ካርዱ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ከዚህ በፊት ጥሬ ገንዘብ ይዞ ወደ ዉጭ አገራት ከሚደረግ ጉዞ ጋር የተያያዙ ስጋቶችንም እንደሚያስቀር ገልጸዋል። ዳሸን ባንክ በአለም ዓቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ዕዉቅና ካለዉ አሜሪካን ኤክስፕረስ ጋር በመሆን ካርዱን ማስተዋወቁ መልካም ዕድል መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአፍሪካ የአሜሪካን ኤክስፕረስ ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ጄምስ ዋይናይ በበኩላቸዉ፣ ካርዱ ኢትዮጵያዉያን ይበልጥ አስተማማኝና ቀላል በሆነ መንገድ አለም ዓቀፍ ክፍያ መፈጸም እንዲችሉ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አመልክተዋል። ካርዱ በአለም ዓቀፍ ዝዉዉር ወቅት ከፖስ ማሽኖች ክፍያ ለመፈጸም የሚያስችል በመሆኑ ይበልጥ አመች እንደሚያደርገዉም ጠቁመዋል።
አለም ዓቀፍ ግብይት ለመፈጸም፣ የሆቴል አገልግሎት ለማግኘትና የአየር በረራ ትኬት ለመቁረጥ አመች መሆኑም የተገለጸ ሲሆን፣ አሜሪካን ኤክስፕረስ እስካሁን ከዳሸን ባንክ ጋር በትብብር ሲሠራ መቆየቱ ተመላክቷል።
ደንበኞች ካርዱን በየትኛዉም የባንኩ ቅርንጭፍም ሆነ የዉጭ ምንዛሬ ቢሮ በማመልከት በአጭር ጊዜ ዉስጥ ማግኘት እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
ዳሸን ባንክ እንደ አሜሪካን ኤክስፕረስ፣ ቪዛ፣ ማስተርካርድና ዩኒየን ፔይ ከተሰኙ ታዋቂ አለም ዓቀፍ የኤሌክትሮኒክ ክፍያ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ጋር፣ እንዲሁም እንደ ዌስተርን ዩኒየን፣ መኒግራም፣ ኤክስፕረስ መኒ፣ ዳሃብሺል፣ ኢዝረሚት፣ ትራንስፋስት፣ ወርልድሬሚትና ሪያ ከሚባሉ ታዋቂ አለም ዓቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ተቋማት ጋር በትብብር በመሥራት ላይ ይገኛል ተብሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014



