የኢትዮጵያ ጤና መድን ኤጀንሲ በ60 ሚሊዮን ብር ወጭ 300 ሞተር ሳይክሎችን ለመግዛት በሒደት ላይ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።
አጠቃላይ የመግዣ በጀቱ በጤናው ዘረፍ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ከሚሠራ የውጭ ግብረ ሰናይ ድርጅት በዕርዳታ እንደተገኘም ኤጀንሲው ጨምሮ ገልጿል። ኤጀንሲው ግዥው በመንግሥት ግዥ አገልግሎት በኩል እንዲፈጸም በጻፈው ደብዳቤ መሠረት፣ ሞተር ሳይክሎችን ለመግዛት የሚያስችለው ሕጋዊ የጨረታ ማስታወቂያ መስከረም 14/2014 በአየር ላይ መዋሉ ነው የተገለጸው።
የጨረታ ማስታወቂያው ለአገር ውስጥ ተጫራቾች 15 ቀን ብቻ የሚቆይ ቢሆንም፣ ጨረታው ላይ ዓለም አቀፍ ተጫራቾች የሚሳተፉበት በመሆኑ ለ40 ቀን በአየር ላይ እንደሚቆይም ተገልጿል። በዚህም ጨረታው ትላንት ጥቅምት 26/2014 ተከፍቷል። ከጨረታው መጠናቀቅ በኋላ የዋጋና ቴክኒካል ጥናት የሚደረግ በመሆኑ ይህ ሒደት አንድ ወር ገደማ ሊፈጅ እንደሚችልም ተጠቁሟል። በመቀጠልም ጨረታው ተጠናቆ፣ የመንግስሥት ግዥ አገልግሎት ከአሸናፊው ጋር ውል ተዋውሎ ከደብዳቤ ጋር ሲልክ የኢትዮጵያ ጤና መድን ኤጀንሲ የመግዣ በጀት እንደሚለቅ ነው የተገለጸው።
የኢትዮጵያ ጤና መድን ኤጀንሲ ከፍተኛ የግዥ ባለሙያ የሆኑት ዳዊት ሻረው ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ግዥውን የሚፈጽመው የመንግሥት ግዥ አገልግሎት መሆኑን አስታውሰው፣ ከጨረታው በኋላ በግዥ ሒደቱ ላይ የውጭ ምንዛሪ ችግር ሊያጓትተው ቢችልም፣ የመንግሥት ግዥ አገልግሎት እስከ ታኅሳስ 30/2014 የግዥ ሒደቱን አጠናቆ ሞተር ሳይክሎችን ለኢትዮጵያ ጤና መድን ኤጀንሲ ማስረከብ እንዳለበት አሳውቋል ሲሉ ገልጸዋል።
ግዥው መስፈርቱን ከሚያሟሉ የአገር ውስጥ የሞተር ሳይክል አስመጭዎች ወይም ከውጭ አገር ኩባንያዎች እንደሚፈጸምም ጠቁመዋል።
ግዥው ከተከናወነ በኋላ 300 የሚሆኑት ሞተር ሳይክሎች በአገሪቱ ላሉ ኹሉም የኤጀንሲው ቅርንጫፎች ተሰጥተው፣ ለየወረዳዎች በመከፋፈል ለድጋፍ አገልግሎት የሚውሉ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በፊት ተገዝተው የተከፋፈሉ ሞተር ሳይክሎች ቢኖሩም፣ ኤጀንሲው ያለበት የተሸከርካሪ ዕጥረት ስላልተቀረፈ የአሁኑ ተጨማሪ ግዥ እንደተከናወነ የግዥ ባለሙያው ዳዊት ሻረው ጨምረው ተናግረዋል።
የሚገዙት ሞተር ሳይክሎች ከተማ ውስጥ የሚነዱ ሳይሆኑ ለመስክ ሥራ አግልግሎት የሚውሉት “ያማኀ (YAMAHA)” ሞተር ሳይክሎች መሆናቸው ተጠቁሟል። አሁን ላይ ያለው አገራዊ ኹኔታ ከበጀት አንጻርም ከባድ በመሆኑ እንጂ፣ የኢትዮጵያ ጤና መድን ኤጀንሲ ያለበትን የተሸከርካሪ ዕጥረት ለመቅረፍ ወደፊት ባለ አራት እግር ተሸከርካሪዎችን ለመግዛት ዕቅድ እንዳለው ዳዊት ሻረው ገልጸዋል።
የመንግሥት ግዥ አገልግሎት ለኢትዮጵያ ጤና መድን ኤጀንሲ ከሚገዛቸው 300 ሞተር ሳይክሎች በተጨማሪ፣ ለገቢዎች ሚኒስትር 60 ሞተር ሳይክሎችን በኹለት ‹ሎት› ግዥ ለመፈፀም ዓለም አቀፍ ግልፅ ጨረታ አውጥቶ፣ የጨረታ ሠነዱ እየተሸጠ መሆኑን ከመንግሥት ግዥ አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ቅጽ 4 ቁጥር 157 ጥቅምት 27 2014



