“ኦነግ ሸኔ” በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ቦታዎች የሚሠነዝረው ጥቃት እየተባባሰ ነው ተባለ

0
884

“ኦነግ ሸኔ” በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በንጹኃን ሰዎች ላይ የሚሠነዝረው ጥቃት ከሰሞኑ እየተባባሰ መምጣቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ኃይል በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚያደርሰው ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት እየተባባሰ በመምጣቱ፣ በተለይም በአምስት ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ዙሪያ ገባውን እንደታገቱና በርካታ ሰዎች ጥቃት እየተሠነዘረባቸው መሆኑን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልጸዋል።

የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ፣ በአምስቱም ወረዳዎች ማለትም በጊዳ አያና፣ አቢ ደንጎሮ፣ ጉደያ ቢላ፣ ሐሮ ሊሞ እንዲሁም ትሪ በተሰኙት ወረዳዎች የሚገኙ ነዋሪዎች፣ “ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ ተከታታይ ጥቃት” እየተፈጸመባቸው ነው ብለዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ቆንዳላ ወረዳ የሚገኙ ቁጥራቸው በግልጽ ያልተወቀ በርካታ ንጹኃን ዜጎች መገደላቸውንና ከጥቃቱ የተረፉትም አካባቢያውን ለቀው ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መፈናቀላቸውን የአዲስ ማለዳ ምንጮች አመላክተዋል።

ጥቃቱ እየተሠነዘረብን ነው የሚሉት ለአዲስ ማለዳ ጥቆማ የሰጡት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ እየተባባሰ የመጣው “የኦነግ ሸኔ” ጥቃት ከእስካሁኑ ለየት የሚያደርገው አንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ተወላጆች ላይም ያነጣጠረ መሆኑ ነው ሲሉ አመላክተዋል።
“የአካባቢው ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ማጣት ሳይሆን የሚያሳስባቸው ሕይወታቸውን የሚያተረፉበት መንገድ አለማግኘታቸው ነው” የሚሉት የአዲስ ማለዳ ምንጮች፣ ነዋሪዎቹ ታጣቂ ኃይሉ ከሚሠነዝረው ጥቃት ለማምለጥ ቢሞክሩም እንዳይወጡ በየአቅጣጫው ያሉ

መንገዶች “ሆን ተብሎ” ተዘግተውባቸዋል ሲሉ ነው የጠቆሙት። አሁን ያለው ትልቁ ችግር የመንገድ መዘጋት መሆኑን የጠቆሙት ነዋሪዎቹ፣ የሚመለከተው አካል መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ሕይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ለመሸሽ ሙከራ ያደረጉ ሰዎች እንደታገቱ የተመላከተ ሲሆን፣ ለአብነትም ባሳለፍነው ሳምንት በሦስት የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ተሳፍረው ሠላም ወዳለበት አካባቢ ሲጓዙ የነበሩ ሰዎችን “ታጣቂ ቡድኑ” እንዳገታቸውና ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ አድራሻቸው እንዳልታወቀ ተገልጿል።

“ኦነግ ሸኔ” ሠላም ወዳለበት አካባቢ የሚሸሹ ሰዎችን ማገት ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል የሚሉት የአዲስ ማለዳ ምንጮች፣ “እስከዛሬ በታጣቂ ቡድኑ የታገቱ በርካታ ሰዎች ለሞት ተላልፈው ተሰጥተዋል እንጅ፣ አንዳቸውም የመመለስ ዕድል አላገኙም” በማለት ነው ያስተዋሉትን የመሰከሩት።

በተለይም በጊዳ አያና ወረዳ አንገር ጉትን እና ሐሮ ሊሙ ወረዳ የነበሩ ከሞት የተረፉ ነዋሪዎች፣ ሙሉ ለሙሉ አካባቢያቸውን ለቀው እንደወጡና ኑሯቸውን በጫካ ካደረጉ ከአንድ ወር በላይ እንዳስቆጠሩ ነው የተጠቆመው።
በሌላ በኩል፣ ትሪ ወረዳ በተሰኘው አካባቢ ቁጥራቸው በግልጽ ያልታወቀ በርካታ ሕፃናት እንደታገቱና ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ያሉበት ሁኔታ እንደማይታወቅ የአዲስ ማለዳ ምንጮች አመላክተዋል።

ወቅቱ የአዝመራ መሰብሰቢያ ወቅት እንደሆነ የሚገልጹት የጥቃቱ ሰለባዎች፣ የአማራ ብሔር ተወላጆች በሆኑ ዜጎች ማሳዎች የሚገኙ ሰብሎች በታጣቂ ቡድኑ ኃይሎች ታጭደው እንደተወሰዱና የቀሩትም እንዳልተሰበሰቡ ተጠቁሟል።


ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here