የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት ከሆስፒታሎች ጋር በነበረው ውል ለአገልግሎቱ በቂ ክፍያ ባለመፈጸሙ፣ በአማራ ክልል በሚገኙ የተወሰኑ ሆስፒታሎች የጤና መድን አገልግሎት እንደተቋረጠ የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ። አገልግሎቱ የተቋረጠው የፋይናንስ ዕጥረት በማጋጠሙ ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።
የጤና መድኅን ከጤና ተቋማት ጋር ውል ሲዋዋል፣ ለአንድ ዓመት ሙሉ የአባላቱን የሕክምና አገልግሎት ወጭ ለመሸፈን መሆኑን የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድን ቡድን መሪ እንዳላማው ክንዴ ተናግረዋል። ይሁን እንጅ አሁን ላይ ያለው የሕክምና ወጭ በመጨመሩ ምክንያት፣ ጤና መድኅን ለጤና ተቋማቱ የከፈለው ዓመታዊ በጀት ዓመት ሳይሞላ እንዲያልቅ አድርጓል። በዚህም በጀቱን በጨረሱ የክልሉ የተወሰኑ ሆስፒታሎች የጤና መድኅን አገልግሎት ከኹለት ወር በፊት ጀምሮ መቋረጡን ጠቁመዋል።
የጤና መድኅን የሕክምና አገልግሎት ከተቋረጠባቸው የክልሉ የጤና ተቋማት መካከል የደብረ ማርቆስ ሆስፒታል እና ምሥራቅ ጎጃም የሚገኘው ቢቡኝ ሆስፒታል እንደሚገኙበት ቡድን መሪው ለአዲስ ማለዳ ገለጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ፣ የጤና መድን የአባልነት ክፍያ ዝቅተኛ እና የአባላቱ ቁጥርም አነስተኛ መሆኑ ለበጀት ዕጥረቱ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል። አንድ የጤና መድን አባል ዓመታዊ የአባልነት መዋጮው ከ350 እስከ 400 ብር ሲሆን፣ በዚህ ዓመታዊ መዋጮ ግን እስከ አንድ መቶ አንድ ሺሕ ብር የሚደርስ የሕክምና ወጭ የተሸፈነለት አባል መኖሩን ጠቅሰዋል። ይህም ጤና መድን ለጤና ተቋማቱ የሚያሲዘውን ዓመታዊ በጀት በቶሎ እንዲያልቅ እንደሚያደርገውና ይህ ሲሆን በጤና መድህን እና በጤና ተቋማቱ መካከል የተደረገው ስምምነት ሊቋረጥ እንደሚችል ነው የገለጹት።
በክልሉ በሚገኙ በእነዚህ ሆስፒታሎች የተቋረጠው የጤና መድን አገልግሎት እስከ ጥር ወር ሊዘልቅ እንደሚችልም ተመላክቷል። ይህ የሆነውም የጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚዎች በአብዛኛው አርሶ አደሮች በመሆናቸው፣ ገንዘብ የሚያገኙበት ወቅትም የአዝመራ መሰብሰቢያ በሆነው በጥር ወቅት በመሆኑ የአባልነት ክፍያ የሚፈጽሙት በዚያን ሰሞን ስለሆነ ነው።
ችግሩ በጥር ወር እንደሚፈታ የገለጸው ቢሮው፣ አሁን ላይ አገልግሎቱ በኹሉም ጤና ጣቢያዎች እየተሰጠ በመሆኑ፣ ታካሚዎች አግልግሎቱን ወደ ጤና ጣቢያዎች ሔደው እያገኙ መቆየት እንደሚችሉ ገልጿል። አሁን ላይ በአብዛኛው በክልሉ በሚገኙ ሆስፒታሎች አግልግሎቱ እየተሰጠ ቢሆንም፣ ሆኖም ግን ጥር ሳይደርስ ከጤና መድን የተበጀተላቸውን በጀት የሚጨርሱ ሌሎች ሆስፒታሎች ካሉ አግልግሎቱን ሊያቋርጡ እንደሚችሉ ነው የተጠቆመው።
የጤና መድን አገልግሎትን ለማስጀመር ተብሎ በዝቅተኛ የአባልነት ክፍያ የተጀመረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ የሚዋጣው ገንዘብ እና የሚሰጠው አገልግሎት የማይመጣጠን መሆኑም ተመላክቷል። በቀጣይም በጤና መድን እና በጤና ተቋማት መካከል የሚደረገው የበጀት ስምምነት የዓለም ጤና ድርጅት አንድ ሰው በዓመት ቢያንስ ሦስት ጊዜ ወደ ጤና ተቋማት መሔድ ይኖርበታል የሚለውን የሕክምና ወጭ የሚሸፍን መሆን ይኖርበታል ሲሉ ነው ያብራሩት።
ጤና መድን ከመንግሥት በጀት ፈሰስ ስለማይደረግለት ወደፊት የአባላት ቁጥር እንዲጨምር፣ የአባልነት ገንዘብ መዋጮ እንዲሻሻል እና ሌሎች የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራዎች እንዲሠሩ ቢደረግ ችግሩ በቋሚነት ሊፈታ እንደሚችል ጤና ጥበቃ ቢሮው ሐሳብ አስቀምጧል። በዚህም የጤና መድን ጠቅላላ ጉባኤ ኹሌም እንደሚያደርገው፣ በጥር ወር በዓመቱ ያጋጠሙ ችግሮች ላይ በመወያያት ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን የገለጹ ታካሚዎች በበኩላቸው፣ መዋጮ የከፈሉት ለአንድ ዓመት ለሚሆን የሕክምና አገልግሎት የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ በክልሉ የጤና መድን አግልግሎት በተቋረጠባቸው ሆስፒታሎች በገንዘብ ዕጥረት ምክንያት መታከም እንዳልቻሉ ገልጸዋል። በጤና ጣቢያዎች የማይሳኩ ሕክምናዎች በመኖራቸው አገልገሎቱ እስከ መጪው ጥር ድረስ ተቋርጦ እንዲቆይ ከማድረግ ይልቅ ሌላ መፍትሔ ፈልጎ የሚመለከተው አካል ችግሩን በቶሎ እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 158 ሕዳር 4 2014


