ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች በርካታ ቅርሶች ላይ ጉዳት የደረሰ በመሆኑ፣ ከጠፉት እና ከወደሙት የተረፉትን ለመጠገን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ወደፊት ጦርነቱ ባለባቸው አካባቢዎች ሠላም እና መረጋጋት ሲሰፍን ከሌሎች አካላት ጋር ወደ ቦታው በማቅናት የተጎዱትን እንደሚጠግን እና የተረፉትንና የጠፉትን ለመለየት የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያከናወነ መሆኑን ነው የገለጸው።
በቅድመ ዝግጅት ሥራው ምሁራንን ያቀፈ ብሔራዊ ኮሚቴ እና የቴክኒክ ቡድን ተቋቁሞ ሥራውን ለመሥራት መታቀዱንም ለማወቅ ተችሏል።
ሠላም ሰፍኖ የሥራው ክንውን በሚጀመርበት ወቅትም ከተጎዱ ቅርሶች ውስጥ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የሚጠገኑትን ለመለየትም ከተለያዩ አካላት ጋር የሚሠራ ይሆናል ነው የተባለው።
ባለሥልጣኑ በአሁኑ ወቅት ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ቅርሶች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የምችለውን እያደረኩ ነው ብሏል። በዚህም ጦርነቱን ለሚመሩ አካላት ቅርሶች የሚገኙበትን ቦታ ለይቶ በዚያ አካባቢ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማድረጉ ነው የተነገረው።
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስ ጥገናና እንክብካቤ ዳይሬክተር ሰላማዊት ጌታቸው እንደገለጹት፣ ቅርሶች በሚገኙባቸው ቦታዎች የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ከባድ መሣሪያ እንዳይጠቀሙ ስምምነት ላይ መደረሱን አንስተዋል። እንዲሁም በቅርሶች መገኛ አካባቢ ከባድ መሣሪያም ሆነ የእግረኛ ጦር እንዳያልፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሆኖም ዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በጥንታዊ የኃይማኖት ተቋማት ውስጥ ከባድ መሣሪያዎችን እንደሚያከማችና ንጹኃንን እንደሚያጠቃ በተደጋጋሚ የሚነገር በመሆኑ መንግሥት ይህን ቢያደርግም የመንግሥት ውሳኔን ህወሓት ማክበር አለማክበሩን ዳይሬክተሯ መመለስ አልችልም ብለዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በጦርነት ወቅት የቅርሶችን ደኅንነት ለመጠበቅ በሚል በ1946 የፈረመችውን ዓለም አቀፍ ስምምነት እየተከበረ ስለመሆኑ አዲስ ማለዳ በጠየቀችው መሠረት፣ ስምምነቱ ተግባራዊ የሚሆነው በተፈራረሙ አገራት መካከል ጦርነት ሲካሄድ ነው። ቢሆንም ግን መንግሥት አሁንም ስምምነቱን አክብሮ ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው፣ ህወሓት ግን እንደ መንግሥት ሆኖ ስምምነቱን ባለመፈረሙ ለቅርሶቹ ኃላፊነት ይወስዳል ብሎ ማሰብ አይቻልም ነው ያሉት።
ዳይሬክተሯ አክለውም፣ ቅርሶችን ለመጠበቅ ዓለም አቀፍ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች እገዛ እንደሚያደርጉ ገልጸው፣ የላሊበላን ደኅንነት ለመጠበቅ የፈረንሳይ መንግሥት ዕገዛ ያደረገ ሲሆን፣ አሁን ለሚደረገው ቅርሶችን ከጉዳት የመከላከል ተግባርና ወደፊት ለሚኖረው ጥገና ከዩኔሰኮ አዲስ አበባ ማስተባበሪያ (ላይዘን) ጽሕፈት ቤት ጋር በትብብር እንደሚሠሩ ተናገረዋል።
ህወሓት ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ጥንታዊ ቅርሶች በብዛት የሚገኙባቸው ጥንታዊ ቤተክርስትያኖችን እና መስጊዶችን ከማፍረሱ በተጨማሪ፣ የበርካታ መድፍ እና ከባድ የጦር መሣሪያዎች ማከማቻ እያደረጋቸው በመሆኑ የተዘረፉና የተጎዱ በርካታ ቅርሶቸ መኖራቸው በተለያዩ ጊዜያት ሲገለጽ መቆየቱ ይታወቃል።
ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ በጦርነቱ ምክንያት በአማራ ክልል ከወደሙና ከተጎዱ ቅርሶች በተጨማሪ፣ ትግራይ ክልል ውስጥ ይገኙ የነበሩ በርካታ ቅርሶችም ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ አጋጥሟቸዋል። ለአብነትም መቀሌ ከተማ ውስጥ ይገኝ በነበረው የአጼ ዮሐንስ አራተኛ ሙዚየም ቤት ውስጥ የነበሩ ቅርሶች በሙሉ የተወሰዱና የጠፉ መሆናቸው ተገልጿል። ቅርሶቹ እንደ መስቀል ሥዕላት ያሉ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ሲሆኑ፣ ቁጥራቸው ወደ ኹለት መቶ ይደርስ ነበር ተብሏል። ኹሉም ቅርሶች የጠፉት መከላከያ ሠራዊቱ ትግራይ ክልልን ለቆ ከመውጣቱ በፊት ሲሆን፣ ማን እንደወሰዳቸው አይታወቅም ነው የተባለው።
ቅጽ 4 ቁጥር 160 ሕዳር 18 2014



