ጌዴኦ – በደራሮ የደመቁ መልኮቿ

Views: 685

ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ነው ጌዴኦ ዞን ዘልቀን ዲላ ከተማ ያረፍነው። ከመንገድና ከሙቀት ድካም ያተረፈውን ሰውነታችንን አረፍ ከማድረጋችን ካረፍንበት ሕንጻ አልፎ ጩኸትና ጫጫታ እንዲሁም ጭስ አካባቢውን ሸፈነው። በኋላ ስንረዳ ዲላ በመላዋን በጭስ ታጠነች፣ ጩኸት ሞላት፣ የመኪና ጡሩንባ አጥለቀለቃት።

ምክንያቱ ለብዙዎቻችን በቶሎ የተገለጠ አይመስለኝም። እንደውም ዲላ እንድንገኝ ምክንያት የሆነው የጌዴኦ የዘመን መለወጫ የሆነው ‹ደራሮ› በዓል የዋዜማ ክዋኔ የመሰለው ጥቂት ተጓዥ አይመስለኝም። ነገር ግን ያ አልነበረም። በአገራችን ከጎደለው ሰላም ጎን ለጎን እኩል እያስጨነቀ ያለው የአንበጣ መንጋ ዲላ ሰማይ ላይ በማንዣበቡ ነው።

እውነት ለመናገር አንበጣውን ከአካባቢው ለማሸሽ የነበረው የአካባቢው ነዋሪ የትብብር ጩኸት፣ የተለያዩ ከፍ ያሉ ድምጾችን በሞተርና በመኪና ጡሩንባ የማሰማቱ ነገር ከጭሱ ጋር ተዳምሮ፣ እንኳን አንበጣ ሰው ያሸሻል። የጭሱ ሁኔታም ከበድ ያለ እንደነበር አዲስ ማለዳን ጨምሮ ብዙዎች ታዝበዋል። ይቃጠሉ የነበሩት በአብዛኛው ጎማዎች በመሆናቸው አየሩ የበለጠ ተበክሎ ነበር። ያም ሆነ ይህ አንበጣው ሊያደርሰው ከሚችለው ጉዳት የባሰ አልነበረም።

የምሽቱ የዲላ ጭስና ጩኸት አንበጣውን ካሳደደው በኋላ፣ ድምጽ ማሰማት ይደክማቸዋል ብሎ ይሁን ወይም የሚያቃጥሉት ያጣሉ ብሎ ባይታወቅም፤ በማግስቱ ማለዳና ረፋድ ላይም የአንበጣው መንጋ የዲላን ሰማይ ወረረው። የከተማዋ ነዋሪ አልደከመም፣ በጩኸት እንዲሁም በርችት አንበጣውን ደግሞ ከአካባቢው አባረረው።

‹‹የአንበጣ መንጋው በሌሊት ጌዴኦ ዞን ደርሶ ጥፋት ሊያደርስ ይችላል›› የሚል ትክክል ያልሆነ መረጃ ከዚህ ቀደም ደርሶት የነበረው የዲላ ዞን ነዋሪ፣ ይህ በተባለ እለት ሌሊቱን ሳይተኛ እንዳደረ የጌዴኦ ዞን እርሻ እና ተፈጥሮ መምሪያ ኃላፊ ተገኝ ታደሰ ያስታውሳሉ። ይሁንና አንበጣው በሌሊት አይንቀሳቀስም ነበር።

የመምሪያው ኃላፊ ተገኝ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ አስቀድሞ በየደረጃው እንዲሁም በመዋቅር ከክልልና ከፌዴራል መንግሥት በመናበብ የሚደረገው እንቅስቃሴ እንደ መምሪያ ተቋሙን አንቅቷል ይላሉ። ተቋሙም በየቀኑ ‹‹ጥንቃቄ ይደረግ›› እያለ ከሚያስተጋባው መገናኛ ብዙኀን በተጨማሪ ነዋሪው የአንበጣ መንጋው ሲከሰት ምን ማድረግ እንደሚገባው ግንዛቤን ሰጥቷል። በገጠሩ አካባቢም በእሳት ጭስ፣ በከተማው ደግሞ ከፍተኛ በሆነ ድምጽ አንበጣን ተባብሮ ማባረር ላይ ማንም ሰው አልሰነፈም።

የአንበጣ መንጋው አዲስ ማለዳ በስፍራው ከደረሰችበት ቀን (ጥር 14/2012) ቀደም ባሉት ቀናትም በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ተንቀሳቅሶ እንደነበር ተገኝ አስታውሰዋል። ‹‹የወረራው ሁኔታ ዘግናኝና መሬት የሸፈነ ነበር።›› ያሉት ተገኝ፣ የከፋ ጉዳት ባያደርስም በዞኑ የጥፋት አሻራውን ያኖረባቸው አካባቢዎች ነበሩ።

‹‹በዐይናችን እንዳየነው፤ ከብዛቱ የተነሳ [የአንበጣ መንጋው] ያረፈባቸው ዛፎች ወድቀዋል፤ ስሩ የጠበቀ ነው የሚባለው ባህር ዛፍ ሳይቀር። የንብ ቀፎዎችም እንደዛው። አንዳንድ አካባቢ ላይ የአቮካዶ ፍሬ የተራገፈ አይተናል። መብላት የጀመሩባቸው አካባቢዎችና ወረዳዎች አሉ።›› ያሉት ተገኝ፤ ከብዛቱና ያስከትላል ተብሎ ከሚጠበቀው ጉዳት አንጻር ሲታይ ግን የከፋ ጥፋት እንዳላደረሰ ነው የጠቀሱት።

‹‹ከዚህ በኋላስ ተመልሶ የአንበጣው መንጋ ቢመጣስ?›› የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ተገኝ፤ የዞኑ ነዋሪ በተመሳሳይ መልኩ አንበጣውም ከማሸሽ አይቦዝንም ብለዋል። አስቀድሞም በክልሎች መካከል መናበብ በመኖሩ፣ በመነጋገር አንበጣውን ቀድመው ተዘጋጅተው እንዲጠብቁት እንደሚያስችልም አንስተዋል። እንደው ሰላም ማጣትንና ኢትዮጵያን እየጎዱ ያሉ አስተሳሰቦችን እንዲህ በጩኸትና በጭስ ነቅሎ ማስወጣት በተቻለ ስትል አዲስ ማለዳ መመኘቷ አልቀረም።

በነገራችን ላይ፤ አንበጣውን ለማባረር የአካባቢው ነዋሪ በተግባር ካደረጋቸው እንቅስቃሴዎች ጎን ለጎን የገዳ አባቶችን ጸሎት እውቅና እንደሚሰጡና ለተደረጉ የእምነት ጸሎቶች በሙሉ አድናቆት እንዳላቸው የመምሪያው ኃላፊ ገልጸዋል። ‹‹እንዲህ ያለ ክፉ ነገር ሲከሰት ወደ ፈጣሪ የመጮኽ የእምነትና ባህላዊ ስርዓት አለ። ይህን ተከትሎ አንበጣ መንጋ፣ ድርቅ፣ የበሽታ ወረርሽኝም ቢሆን ሲከሰት አባ ገዳ ወጥቶ ፈጣሪን ይማጸናል። መንግሥት የሠራው እንዳለ ሆኖ በጸሎት የተደረገው ሚና ቀላል አይደለም።›› ሲሉ ተናግረዋል። ይህም የጌዴኦ አንዱ መልክ ነው።

የጌዴኦ መልኮች
የጌዴኦ ብሔር ‹ባሌ› የሚባል ባህላዊ ስርዓት አለው፤ ከዘመናዊው የአስተዳደር ሥራ ጎን ለጎን አባቶች በሚኖራቸው ድርሻ በዚህ ባህላዊ ስርዓት ይተዳደራል። በቀደሙ ጊዜያትም ‹አኮማኖዬ› እንዲሁም ‹ጎሳሎ› በሚል መጠሪያ ተመሳሳይነት ያላቸው የገዳ ስርዓቶች በጌዴኦ ሕዝብ ታሪክ ሰፍረው ይገኛሉ።

በዚህ ላይ ሰፋ ያለ መረጃ ያላቸው በኃይሉ በየነ፣ በባሌ ስርዓት ላይ ተከታዩን ብለዋል። የመጀመሪያው የጌዴኦ ባህላዊ የአስተዳደር ስርዓት ‹አኮማኖዬ› የሚባለው በሴቶች መሪነት ይተዳደር የነበረ ነው። ይህን ስርዓት የቀየረው ወይም የተካው ደግሞ ‹ጎሳሎ› የተሰኘ ጎሳሎ ሙርጋ እና ጎሳሎ ያያ በተባሉ ወንድማማቾች እየተፈራረቁ ይመሩበት የነበረበት አስተዳደር ነው።

በኋላ ግን የቤተሰብ አስተዳደር፣ ጾታዊ ግንኙነትና የእርስ በእርስ መስተጋብርን በስርዓት አስተባብሮ ለመኖር የሚያስችል ስርዓት አስፈለገ። ይሄኔ ነው የ‹ባሌ› ስርዓት የተመሠረተው። ‹‹ኹለቱ ስርዓቶች የሕዝብን ፍላጎት መሸከም ሲሳናቸው ሁሉን አቃፊና አማካይ ወደ ሆነው የጌዴኦ ብሔር ዛሬም ወደሚተዳደርበት ባሌ የተባለ የአስተዳደር ስርዓት መቀየር ግድ ሆነበት›› ያሉት በኃይሉ ናቸው።

ይህ የሆነው በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደሆነ ይነገራል። ስርዓቱ ዘጠኝ ደረጃዎች ያሉት ነው። የስርዓቱ ውሳኔ ሰጪና የሕዝቡ የበላይ ጉባኤ ‹ያኣ› ተብሎ ይጠራል፤ ይህም ምልአተ ጉባኤ እንደማለት ነው። ታድያ አስተዳደሩ ስብሰባ ሲያደርግ ተሳትፎ ከሚያደርጉት መካከል ከ‹ሀዩ› እና ‹ዋዩ› የተውጣጡ አባቶች ይገኙበታል። ‹ሀዩ› የተባሉት በኃይሉ ‹ነገር አዋቂ› በማለት ያስቀመጧቸው አባቶች ሲሆኑ፣ ‹ዋዮ› የሚባሉት ደግሞ መንፈሳዊ መሪዎችን ነው።

በጥቅሉም የባሌ ስርዓት መሠረታዊና ዋነኛ ዓላማ፣ በኃይሉ እንዳስቀመጡት፣ ማጌኖ (እግዚአብሔር/አምላክ)ን ማመስገን፣ ለማጌኖ መገዛት ነው። የአስተዳደሩ መሪዎች ልመናና ምስጋናም መሠረቱ ሰላም እንደሆነ በኃይሉ ጠቅሰዋል። ጌዴኦ በሰላምታው ‹ናጌ› አትጠፋም፤ ‹ሰላም› የምትል ቃል። ደኅንነትን ሲጠይቅ ‹ናጌኣንጌ?› ይላል። ሲመራረቅም፣ ‹ናጌስ› እያለ ወደ ማጌኖ ድምጹን ያሰማል። ሰላምን ለሰው ብቻም አይደል፣ ለሳር ቅጠሉ ይመኛል።

ይህ አንዱ የጌዴኦ መልክ ነው፤ ጥንታዊ የሆነው የባሌ ስርዓት። ሌላው የጌዴኦ መልክ ደግሞ ዞኑ ለዓለም ያበረከታቸው ቅርሶች ናቸው። የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ባሰናዳው 6ኛ ቁጥር መጽሔት ላይ ካሰች ደምበል በዚህ ላይ ሰፋ ያለ ዳሰሳ አድርገዋል። 134 ሺሕ 700 ሄክታር ስፋት ያለው ዞኑ፣ ትክል ድንጋዮች፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች እንዲሁም ጥምር የግብርና ስርዓት በስፋት የሚገኝበት ነው።

በዚህ መሠረት በምሥራቅ አፍሪካ ይገኛሉ ተብሎ ከሚገመተው ዐስር ሺሕ የሚጠጋ ትክል ድንጋይ ውስጥ ከስድስት ሺሕ በላዩ በጌዴኦ ይገኛሉ። ዓለም ካወቃቸው በጌዴኦ ከሚገኙ ቅርሶች መካከልም የ‹‹ቱቱፈላ›› አርኪኦሎጂያዊ ስፍራ፣ በይርጋ ጨፌ ወረዳ የሚገኘው የጨልባ-ቱቲቴ የትክል ድንጋዮች መካነ ጥናት፣ የሠዴ ትክል ድንጋዮች መካነ ጥናት፣ ሣካኖ ሦዶ የትክል ድንጋዮች መካነ ቅርስ እንዲሁም የአዶላ ጋማ የድንጋይ ላይ ቅርጽ መካነ ቅርስ ተጠቃሽ ናቸው።

በተመሳሳይ በተፈጥሮአዊ ቅርሶች የታደለችው ጌዴኦ፣ የቡለሎጮ ተራራ ጥብቅ ስፍራ፣ የቢርቢሮታ ጥብቅ ደን፣ ወጊዳ አምባ አግሮ ፎረስተሪ፣ ባሱራ መካነ መቃብር ይገኙባታል።
‹ደራሮ›

ይህ ሁሉ የጌዴኦ መልክ በደራሮ ደምቆ ይታያል። ቡናዋ፣ ገብስና ማሯ፣ ቆጮዋ ይቀርባል። እንሰት የሞላው ለምለም ምድሯ ለአባቶች መረማመጃ የኮባ ቅጠሎችን ያነጥፋል። ወጣትን ከአዛውንት ያስተሳሰረ ‹ባሌ› የተባለው የገዳ አስተዳደር ስርዓቷ፣ ትጋት ብርታቷን ያሳብቃል። አዲስ ማለዳ ደግሞ ተከታዩን ታዘበች።

ጥር 16/2012 የጌዴኦ ከተማ ዋና ዋና መንገዶች አገልግሎት መስጠት ያቆሙት ማልደው ነው። ወጣቶችም የኮባ ቅጠልና ሌሎችም የዛፍ ቅርንጫፎችን ይዘው በመኪና ተጭነውና እየጨፈሩ መንገዱ ላይ የበዓል ድባብ ፈጥረዋል። ‹‹ለደራሮ ያልሆነ ቀሚስ›› የተባለ ይመስላል፤ በባህል ልብስ ያጌጡ የዲላ ከተማ ነዋሪዎችና ከጌዴኦ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የተገኙ ሰዎች ጎዳናውና መንገዱን በውበት ሞልተውታል። የዞኑ ማርች ባንድም ኢትዮጵያን የሚያነሱ ሙዚቃዎችን እየተጫወተ ለበዓሉ የበለጠ ድባብን አላብሶታል።

የዲላ ቀይ አፈር የደስታው ተካፋይ ይመስላል። በደስታ ለሚረግጡት ሁሉ፣ ከመሬት ተነስቶ ወደላይ ሲቦን ይታያል። በቀላሉ ‹‹አቧራው ጨሰ!›› ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ የታየበት ነው። ቀዩን አፈር የለበሰው ስታድየም እስከ እኩለ ሌሊት የደራሮ ዋዜማ የሙዚቃ ደግስ አስተናግዶ ጠዋቱንም መደበኛ የበዓሉን ክዋኔ ለማስተናገድ አልጠበበም/አላነሰም።

ከስታድየሙ መግቢያ ጀምሮ በተነጠፈው ኮባ ላይ ማንም እንዳይራመድ ተደርጎ የገዳ አባቶች ብቻ ተሻግረውበታል። ቤቱ የቀረውና ለበዓል አደባባይ ያልወጣው ጥቂት ነው። የከተማዋ ሰው በነቂስ ወጥቷል። ደመናው ቀኑን ያወቀ ይመስል ፀሐይ ከማቃጠሏ ጋብ እንድታደረግ ጋርዷታል። እለቱ ደራሮ ነው፤ የጌዴኦ የዘመን መለወጫ።

በዓሉ ከመድረሱ ቀደም ብሎ ነው ዝግጅትም የሚጀምረው። ይህም ‹ፉጬኤ› የሚባል ሲሆን፣ የመንጻት ስርዓት ነው ይሉታል። ንስሀ የሚገባበት፣ የአካባቢው ማኅበረሰቦች ኃጢአታቸውን ለዋዮዎች (ለመንፈሳዊ ሽማግሌዎች) በመግለጽ የመንፈስ ፈውስ የሚያገኙበት ነው።

የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዮሐንስ አሰፋ፤ ደራሮ አሮጌ የምርት ዘመን እና አሮጌው አበባ አልፎ አዲስ የምርት ዘመንና አዲስ አበባ ለመቀበል ዝግጅት ተደርጎ የሚከበር በዓል ነው ይላሉ፤ ደራሮ። በዓሉ የነጻነት በዓልም ይባላል፤ እንደ ዮሐንስ ገለጻ። በደራሮ ጌዴኦ የምትሰጣቸው ምርቶች፤ ከቡና ከማር እና ከገብስ የሚሠራ ምግብ ይቀርባል። የገዳ አባቶችም ምርቃት የሚሰጡት ይህን ምግብ በማቅመስ ነው።

በእለቱ ታድያ ምርቃት ብቻ አይደለም የሚሰጠው፤ ከዛ በፊት የየአካባቢው ነዋሪዎች ለአባ ገዳው ስጦታ ያበረክታሉ። በዚህ ላይ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ዞኑ ካወጣው መጽሔት ላይ ጥቂት እናክል። እንዲህ ነው፤ የስርዓቱ መሪ ዋና አባ ገዳ ለሕዝብ ከሕዝብ የተወለዱና ለሕዝብ የሚኖሩ ተብሎ ስለሚታመን የራሴ የሚሉት ነገር አይኖራቸውም።

ይልቁንም ወደ ተዘጋጀላቸው መኖሪያ በመሄድ በዛ ይኖራሉ፣ የሕዝብን ሥራ ይሠራሉ። ለሚበሉት፣ ለሚጠጡት፣ ለሚለብሱት፣ ለሚያወርሱት አይጨነቁም። የአባ ገዳ ደጅ ከእንግዶችና ከስጦታ ነጻ ሆኖ አያውቅም። እናም በደራሮ ንጋት ወይ በጌዴኦ አዲስ ዓመት ማለዳ ነዋሪዎች ቀደም ብለው ለቀናት ያሰባሰቡትን ሁሉ ለአባ ገዳ ያደርሳሉ/ያስረክባሉ። ይህም በዲላ ስታድየም በተከናወነው የደራሮ በዓል ሲፈጸም አዲስ ማለዳ ታዝባለች።

እናም ስጦታውን የተቀበሉት አባ ገዳ ሕዝባቸውን በደረቁ ‹ሂድ› አይሉም። ከተሰጣቸው ማር፣ ገብስና ቆጮ ያቃምሳሉ። በቀደመው ስርዓት ደግሞ እንደውም ከሰንጋው መካከል ተመርጦ ታርዶ በእለቱ ለሚገኙ ሁሉ ይቀርብ ነበር።

የ2012 የጌዴኦ ዘመን መለወጫ ደራሮ በዓልም የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የዞኑና የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም በዋናነት አባ ገዳዎቹ በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል። የዞኑ አስተዳዳሪ ገዙ አሰፋ በእለቱ ባደረጉት ንግግር፣ በዓሉ የጌዴኦ የማንነት መገለጫ ነው ብለዋል። በዓሉን በየወረዳው ከማክበር በተጨማሪ በዞን ደረጃ በጋራ መከበሩ፣ እሴቱን ለማጉላት እንደሚጠቅምም አንስተዋል።
በ2011 በዞኑ ባዓሉን ለማክበር በጸጥታ ምክንያትን ብዙ ወገኖች በመፈናቀላቸው በድምቀት ማክበር አለመቻሉን ያስታወሱት አስተዳዳሪው፣ ‹‹የነበረውን ፈተና በመንግሥት አቅም መወጣት ብቻ ይከብድ ነበር። ያንን ፈተና ማለፍ የቻልነው በእናንተ ድጋፍ ነው›› በማለት የኢትዮጵያን ሕዝብ ሁሉ አመስግነዋል።

የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊው ዮሐንስ በበኩላቸው፣ ይህ ባህላዊ እሴት የሚከወንበት በዓል እንዲታወቅ የማስተዋወቅ ሥራው በስፋት እየተሠራ መሆኑን አውስተዋል። በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት ተመዝግቦ እንዲጠበቅ ለማድረግም በከፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ነው የገለጹት። በቅድሚያ በአገር ውስጥ እንዲታወቅ ማድረጉ ይቀድማልና ያንን በመተግበር ላይ ነን ብለዋል።
በዓሉም በድምቀትና በሰላም ተጠናቀቀ። የዲላ ነዋሪ፣ የዞኑ ማኅበረሰብ ‹አንድ ያድርገን! የዓመት ሰው ይበለን!› እያለ ወደየቤቱ አቀና። ቆይታውንም ከባህር በቅርፊት እንዲሉ፣ አዲስ ማለዳ በዚህ መልክ ከተበችው።

ቅጽ 2 ቁጥር 65 ጥር 23 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com