በዓለማችን ከተከሰተ ኹለት ዓመት ሊያስቆጥር አንድ ወር ገደማ የቀረው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ ከመነሻው አንስቶ ብዙ ውዝግቦችን ሲያስተናግድ ቆይቷል። ከቤት አትውጡ የሚል መመሪያን ጨምሮ ሕብረተሰቡ የተለያዩ መከላከያ መንገዶችን እንዲጠቀም ሲገደድም ቆይቷል።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንደተከሰተ ሰሞን አንዳንድ የማኅረሰብ ክፍሎች እውነትነቱን ሲያጣጥሉትና አስጊነቱን ሲያሳንሱ፣ የተወሰኑት ደግሞ ከሚገባቸውም በላይ ሠግተው ጥንቃቄውን አድርገዋል። የጥንቃቄው መጠን እንደአገሩና ሕዝቡ የተለያየ እንደመሆኑ፣ የሥርጭት መጠኑም ከአገር አገርና ከማኅበረሰብ ማኅበረሰብ እንደሚለያይ ይታወቃል።
በወረርሽኙ ይበልጥ ይጎዳሉ የተባሉት አፍሪካውያን በአንፃራዊነት ከምዕራባውያኑ የተሻለ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። ወረርሽኙ የፈጠረው ሥጋት አሁንም ባለመቆሙ እስካሁን ባለበት ይቀጥላል ብሎ መናገር ባይቻልም፣ የሚወሰደው ጥንቃቄም ሆነ ለመከላከያው ያለ አመለካከትና አጠቃቀም የሥርጭቱን መጠን ይወስነዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የተለያዩ አገራት መንግሥታት ወረርሽኙ የዓለም ሥጋት መሆኑን ከተረዱ ጊዜ አንስቶ ሕዝባቸው በየጊዜው የሚወጡ ሕጎችንና ትዕዛዞችን ሰምተው በመቀበል ተግባራዊ እንዲያደርጉ ሲጥሩ ቆይተዋል። ሕግን ከማውጣት ጀምሮ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅን በማወጅ ጭምር ክልከላዎችን ሕብረተሰቡ እንዲያከብር፣ እምቢኝ ካለም እንዲቀጣ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ከገንዘብ ቅጣት እስከ እስር የሚደርስ፣ ቅጣቱ እንደጥፋቱ ግዝፈት የሚለያይ፣ መቀጣጫ የሆነ ውሳኔን የተለያዩ አገራት ሲወስኑ፣ አንዳንዶች ሠብዓዊ መብትን ይጋፋል እያሉ ሲቃወሙት የነበረ ቢሆንም፣ የወረርሽኙን ግዝፈት የተረዱት ቀስ በቀስም ቢሆን ወደ መቆጣጠሩ አዘንብለዋል።
ክትባት ከመገኘቱ በፊት መንግሥታት የውጭ አገር ዜጎች ወደአገራቸው እንዳይገቡ ከማገድ ጀምረው፣ ሕዝባቸው ካልተገደደ በስተቀር ከቤቱ እንዳይወጣ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ሲጀመር ወረርሽኙን በቶሎ መቆጣጠር ይቻላል የሚል ግምት ስለነበር ክልከላዎች ከ15 ቀናት ያልበለጡ ነበሩ። በኋላ ላይ አያያዙ እየታየ ጊዜው ሲራዘም ቆይቶ አንዳንድ ክልከላዎች አሁንም ድረስ በተወሰኑ አገራት እንደጸኑ ቆይተዋል። ሙሉ በሙሉ አትንቀሳቀሱ የሚል መመሪያ አሁን ላይ ባይኖርም፣ በትራንስፖርትና በአገልግሎት ሰጪዎች ዘንድ ተገድቦ የነበረ ክልከላ እንደጸና የቆየባቸው አገራት አሉ።
ወደ አገራችን ስንገባ ቫይረሱ አንድ ሰው ላይ ተገኘ ሲባል የነበረው የሕብረተሰቡ ሥጋትና ጥንቃቄ አሁን እንደሌለ መታዘብ ይቻላል። በፈቃደኝነት ሥራቸውን ዘግተው ከተቀመጡት ጀምሮ፣ አፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጨርቅ (ማስክ) የመሳሰሉ መከላከለያ መንገዶችን ኹሉም እንዲጠቀም የሚያስገድዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች በርካታ ነበሩ። አሁን አሁን ወረርሽኙ ከበፊቱ ጨምሮም እያለ፣ ማስክ ሳያደርጉ መጓዝ የተለመደ ሆኗል። በከተማና በክፍላተ-አገር የነበረው የጥንቃቄ መጠን ቢለያይም፣ ኹሉም ዘንድ የነበረውና አሁን ያለው የጥንቃቄ መጠን እንደሚለያይ መናገር ይቻላል።
የክትባት መገኘት
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ያለማንም ከልካይ እየተስፋፋ በነበረበት ወቅት ተመራማሪዎች ሕክምናውንም ሆነ ክትባትን ለማግኘት ሲጣደፉ ከርመዋል። ድካማቸውም መና ሳይቀር ክትባቱን አግኝተዋል። ለሕክምናው መድኃኒት የሚሆንን ለማግኘትም ጫፍ መድረሳቸውን እያሳወቁ ይገኛሉ። ክትባቱ ተገኘ፣ የሙከራ ፍተሻውን ወደቀ፣ እየተባለም ለብዙ ጊዜ ልብ አንጠልሎ በኋላ ላይ ክትባት መገኘቱ ይታወሳል። አገራት እሽቅድምድም ውስጥ ገብተው ስለነበር በርካታ አምራቾች በተመሳሳይ ጊዜ መከላከያ ክትባቱን ይፋ ማድረግ ችለዋል።
ክትባቱ ይፋ ከሆነና የዓለም ጤና ድርጅት ፈቃድንም ካገኘ በኋላ አነጋጋሪ የነበረው የሥርጭቱ መንገድ ነበር። ሀብታም አገሮች ከሕዝብ ብዛታቸው በላይ እያዘዙ ድሃው ምን ይሁን በሚል በተለይ ለአፍሪካውያን ሥጋታቸውን ሲገልፁ በርካቶች ተደምጠዋል። በለጋሾች ድጋፍ እንዲሁም በአገራቱ በጀት የሚገዙ ክትባቶች ለበርካታ ወራት ቆይተው ሠሞኑን አፍሪካን በብዛት እያዳረሱ መሆናቸው ተዘግቧል።
ምዕራባውያን ከ80 በመቶ በላይ ዜጎቻቸውን ከትበው ተቀረው አልከተብም ሲላቸው ክትባቱን ድሃ ወደሚሏቸው አገሮች በብዛት መላኩን ተያይዘውታል። አፍሪካ 5 በመቶ የማይሞሉ ነዋሪዎቿን ብቻ ከትባ፣ ድጋፍ እየጠበቀች ትገኛለች። ኹሉም ካልዳነ ዓለማችንን ከወረርሽኙ ነጻ ማድረግ እንደማይቻል የተረዱት አሁን አሁን ርብርቡን ማድረግ ጀምረዋል።
ዓለም በታሪኳ አይታው በማታውቅ መልኩ በተሳሰረችበት በዚህ ወቅት፣ ወረርሽኙ እኛ ጋር አይደርስም ብሎ እንደሰሜን ኮሪያ ድንበር ዘግቶ ለረጅም ዘመን መቀመጥ እንደማያዋጣና እንደማይቻል የተረዱት ምዕራባውያኑ፣ ልገሳቸውን በማጠናከር አፍሪካውያን እንዲከተቡ እየጣሩ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ የዚህ ዓላማ አካል በሆነ ልገሳ ወደ 10 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎቿን ለመከተብ የ10 ቀን ዘመቻ በያዝነው ሳምንት መጀመሯ ይታወቃል። ይህን ያህል የክትባት መጠን ሲገኝ የመጀመሪያ ቢሆንም፣ ክትባቱን በተመለከተ በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለ የተዛባ አመለካከትን መጀመሪያ መቀየር እንደሚገባ ባለሙያዎች ሲናገሩ ደደመጣል። የማኅበረሰቡን አመለካከት ቀይሮ በተቀመጠው ጊዜ ሕብረተሰቡ እንዲከተብ ለማድረግ በየመንገዱ ጭምር ቅስቀሳ ሲደረግ ተሰምቷል።
ጎረቤት አገር ኬንያም፣ በርካታ መጠን ያለው ክትባት በማግኘቷ እሷም ሰሞኑን በዘመቻ መልክ እየከተበች ትገኛለች። ‹ሰንዴይ ታይምስ› የተሰኘው ጋዜጣ በማኅበራዊ ሚዲያው እንደዘገበው፣ አገሪቱ የክትባቱን ዓላማ ለማሳካት የሄደችበት መንገድ ከኢትዮጵያ እንደሚለይ ነው። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ኹኔታዎች ካላስገደዱ በስተቀር ክትባቱ አስገዳጅ እንደማይሆን መናገራቸውን ባለፈው ሳምንት ዕትማችን ላይ አስነብበናችሁ ነበር። ኬንያ ግን የማይከተብ ሰው መንግሥታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ደጃፍን መርገጥ አይችልም ስትል አስጠንቅቃለች። ትምህርተ ቤት፣ መዝናኛ ቦታዎችም ሆነ ፓርኮች ውስጥ፣ እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎትን የመሳሰሉትን ያልተከተቡ ሰዎች መጠቀም አይችሉም ስትል ማወጇ ተሰምቷል። ይህ ውሳኔዋን አንዳንዶች በጸጋ ሲቀበሉት፣ የተወሰኑት ደግሞ ተችተውታል። 10 በመቶ ዜጋ ባልተከተበበት ሒደት ይህ መወሰኑ የንግድ ተቋማቱን ይጎዳል ያሉ የተወሰኑ ሲሆኑ፣ ቢያንስ ግማሽ ሕዝቡ እስኪከተብ ቢጠበቅ መልካም ነበረ በማለት የተቻኮለ ውሳኔ ነው በማለት ተችተውታል።
የተጭበረበረ የክትባት ምስክር ወረቀት (ሠርተፍኬት)
በተለያዩ አገራት ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች መከተባቸውን የሚያረጋግጥ የምስክር ወረቀት ሲጠየቁ ካላቀረቡ በበርካታ ተቋማት መገልግል አይችሉም መባሉ ለሕገ-ወጦች በር እየከፈተ መሆኑ እየተነገረ ነው። ግሪክን በመሳሰሉ የምዕራባውያን አገራት ይህን መሰሉን አስገዳጅ የምስክር ወረቀት ለማግኘት በነፃ ከመከተብ ይልቅ ብዙ ብር እየከፈሉ ሕገወጥ የተጭበረበረ ሠነድን የሚገዙ መኖራቸው ተረጋግጧል።
ይህን የምስክር ወረቀት የሚያዘጋጁት ከሕክምና ሙያ ርቀው ሐሰተኛ ሠነድን በማዘጋጀት የሚኖሩ አጭበርባሪዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ በክትባቱ ሒደት ላይ የሚሳተፉ ባለሙያዎች ጭምር በመሆናቸው ከባድ ቅጣት እየተወሰነ መሆኑ ተነግሯል። መከተብ ያልፈለጉ ሰዎች ባለሙያዎችንም ሆነ ሌሎችን በከፍተኛ ገንዘብ እያማለሉ ሳይከተቡ እንደተከተቡ አድርገው ሠነዱን እንዲያዘጋጁላቸው እንደሚያደርጉ የግሪክ ባለሥልጣናት ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።
ሐሰተኛ የክትባት የምስክር ወረቀት ገበያ በመድራቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ጭምር ማስታወቂያ እየተሠራለት ቢገኝም ለማስቆም ማዳገቱን የሚናገሩ አሉ። በእንግሊዝ አገር በ350 ፓውንድ ሠርተፍኬቱን ግዙ ዕያሉ ጥሪ ማቅረባቸውም ተደርሶበታል። እንዲህ ዓይነት አጭበርባሪዎችን ከሕገወጥ ሥራቸው ለማስቆም በመላው አውሮፓ ክትትል መጀመሩን ባለሥልጣናቱ ማሳወቃቸውን ቪ.ኦ.ኤን የማሳሰሉ የሚዲያ ተቋማት አሳውቀዋል።
አየር መንገዶችን በመሳሰሉ በባለሙያዎች የሚከናወኑ ጥብቅ ፍተሻ ባለባቸው ተቋማት እውነተኞቹን የምስክር ወረቀቶች ከተጭበረበሩት ለመለየት አስቸጋሪ ባይሆንም፣ ምግብ ቤቶችንና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በመሳሰሉ ባለሙያና በቂ የሰው ኃይል በሌለባቸው ቦታዎች አጭበርባሪዎቹ ሐሰተኛ የምስክር ወረቀቱን በቀላሉ መጠቀም እንደሚችሉ የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበውታል።
የተጭበረበረ የኮቪድ ክትባት የምስክር ወረቀት መኖሩ ያልተከተቡት ሕግን ጥሰው ሌሎችን ለበሽታ ከማጋለጣቸው ባሻገር፣ለመከተብ ዕቅድ ያላቸውን ገና ያልተከተቡትን በማዘናጋት የምስክር ወረቀት ማሳየት መመሪያዎችን ተቀባይነት እንዲቀንስ ያደርጋሉ ሲሉ በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ሥጋታቸውን ይጠቁማሉ።
የተጭበረበረ ሠነድ የተበራከተባቸው አገራት ክትባቱን በዝቅተኛ መጠን የሰጡ መሆናቸው ይነገራል። ለምሳሌ ያህል ከአውሮፓ አገራት ከዜጎቿ ዝቅተኛውን ቁጥር(18 በመቶ) የከተበችው ዩክሬን፣ ሕገወጥ የየምስክር ወረቀት ንግዱ ስለተበራከተባት ‹ኒው ዮርክ ታይምስ› ሳቀር የጥቁር ገበያውን ተወዳጅነት ጠቅሶ ዘግቦታል። ሒደቱን መገደብ ካልተቻለ አገሪቷ ወደ ውጭ ዜጎቿን ስትልክ ገደብ ሊጣልባት አልያም፣ ከአገሪቱ የሚቀርቡ ሠነዶች ተቀባነት እንዳይኖራቸው ሊያደርግ ይችላል ሲሉ የዘርፉ ኃላፊዎች ሥጋታቸውን መግለፃቸውን ‹አትላንቲክ ካውንስል› ይፋ አድርጓል።
ቅጽ 4 ቁጥር 160 ሕዳር 18 2014



