አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ እና አፈጻጸሙ

0
1018

ከአንድ ዓመት በፊት በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች መስፋፋቱን ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ ላይ የሕልውና አደጋ ደቅኗል። የጦርነቱ መሰፋፋት እና መባባስ የፈጠረውን ሥጋት ተከትሎ የፌዴራል መንግሥት ችግሩ የከፋ ደረጃ ላይ በመድረሱ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ማወጁ የሚታወስ ነው።

በመላው ኢትዮጵያ ተፈጻሚ ይሆናል የተባለው አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ከታወጀ ዛሬ 25 ቃናት አስቆጥሯል። ዐዋጁ ከታወጀበት ከኅዳር 23/2014 ጀምሮ ለስድስት ወራት የሚዘልቅ ሲሆን፣ ዐዋጁ እሰካሁን ተግባራዊ በሆነባቸው ሦስት ሰምንታት በሽዎች የሚቀጠሩ የተለያዩ የቡድንና የግል ሕግ ወጥ የጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

በተለይ በአዲስ አበባ በአሸባሪነት የተፈረጀው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ(ህወሓት) አስቦት የነበረው የሽበር ተግባር በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ መክሸፉን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መግለጹ የሚታወስ ነው።
አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መታወጁን ተክትሎ ኢትዮጵያ የገጠማትን ጦርነት ሊያባብሱ የሚችሉ ችግሮች ማስቀረት መቻሉን ባለሙዎች ይገልጻሉ። የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ አፈጻጸም በተለይ ለሽብር ተግባር ሊውሉ የሚችሉ ሕግ ወጥ የጦር መሣሪያዎን እና ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለመዋል ጉልህ አስተዋጽዖ እያደረገ መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በአንጻሩ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን መሰረት በማድረግ የሚፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳሉ እየተሰማ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም አዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ የሕግ ባለሙዎች እና ወታደራዊ ባለሙያዎችን አነጋግሮ የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያለው ጦርነት፣ በተለይ ከሐምሌ 2013 ወዲህ፣ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች መስፋፋቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ የገጠማት ቸግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል። ጦርነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ እና እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ የፌዴራል መንግሥት በመላው ኢትዮጵያ ተፈጻሚ የሚሆን አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ማወጁ የሚታወስ ነው።

ህወሓት ከያዘው ዓላማ አንጻር ኢትዮጵያ የሕልውና አደጋ ከጦርነት እንደተጋረጠባት የገለጸው የፌዴራል መንግሥት፣ ችግሩን ለመቀልበስ ለስድስት ወር የሚዘልቅ አስቸኳይ ጊዜ አውጇል። የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ከወጣትበት ጥቅምት 23/2014 ጀምሮ ለስድስት ወራት ተፈጻሚ ይሆናል።

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ፣ “የአገር ሕልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣ ዐዋጅ ቁጥር 5/2014” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ መንግሥት የአገርን ሕልውና፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጠላቶች የመጠበቅ የሕግም ሆነ የሞራል ኃላፊነት እና ግዴታ ያለበት መሆኑን በመገንዘብ፣ ህወሓት ኢትዮጵያን የማዳከም እና ብሎም የማፍረስ ምኞት ካላቸው የውጭ ኃይሎች ጋር በከፍተኛ ቅንጅት እየሠራ እንደሆነ በመገንዘብ፣ የአገር ሕልውና ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም አዳጋች በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መደንገግ እና ተግባራዊ ማድረግ አደጋውን ለመቀልበስ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ መታወጁን አስረድቷል።

በመላው ኢትዮጵያ ተፈጻሚ የሚሆነው አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ፣ የስዓት ዕላፊ ገደብ ሊወሰን እንደሚችል፣ ማንኛውም የሕዝብ መገናኛ እና የሕዝብ መጓጓዥ ዘዴ እንዲዘጋ ወይም እንዲቋረጥ ሊያዝ ይችላል ተብሏል። ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል ብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠረ ማንኛውንም ሰው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር ለማድረግ፣ ይህ ዐዋጅ ተፈጻሚ ሆኖ ባለበት ጊዜ ድረስ ይዞ ለማቆየት ወይም በመደበኛ ሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ይቻላል።

በተጨማሪም ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል ብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠረ ማንኛውንም ሰው ወይም ድርጅት ንብረት የሆነን ማንኛውንም ቤት፣ ሕንፃ፣ ቦታ፣ መጓጓዣ ለመበርበርና እንዲሁም ማንኛውንም ሰው ለማስቆም፣ ማንነቱን ለመጠየቅ፣ ለመፈተሽ፣ በብርበራ ወይም በፍተሻ የተያዙ የጦር መሣሪያዎችን ለመውረስ፣ ለተወሰነ ጊዜ መንገዶችንና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለመዝጋት፣ ሰዎች ለጊዜው በተወሰነ ቦታ እንዲቆዩ፣ ወደ ተወሰነ አካባቢ እንዳይገቡ ወይም ከተወሰነ ቦታ እንዲለቁ ማዘዝ እና ከፍተኛ የጸጥታ ችግር እና ሥጋት በተፈጠረባቸው የአገሪቱ ክፍሎች ያለ የአካባቢ አመራር መዋቅር በከፊልም ሆነ በሙሉ ማገድ፣ መለወጥ እና በሲቪልም ሆነ በወታደራዊ አመራር መተካት እንደሚችል ተደንግጓል።

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ምንድን ነው?
አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ የሚታወጀው ችግሮች ሲገጥሙ በመደበኛ ሕግ መከላከል ሳይቻል ሲቀር መሆኑ ይገለጻል። አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ አገራት በመደበኛ የሕግ አሠራር እና የጸጥታ ማስከበር ሥራ መፈጸም የማይችሉት አስገዳጅ ውይም መሠረታዊ ምክንያቶች ሲኖሩ የሚታወጅ መሆኑን የሕግ ባለሙያው ጥጋቡ ደሳለኝ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጠቁመዋል።

አዲስ ማለዳ ከኢትዮጵያ ፍትሕ ሚኒስቴር ድረ-ገጽ ያገኘችው ስለ አስቸኳይ ገዚ ዐዋጅ ግንዛቤ ለመፍጠር የተሠራጨ ጽሑፍ፣ “ከመደበኛው ለየት ባለ ሁኔታ የአስቸኳይ ጊዜ አደጋ ሲያጋጥም መሠረታዊ የአገር ሠላምና ደኅንነት አደጋ ላይ ስለሚወድቅ መንግሥታዊ ተግባራትን በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት መቋቋምና መቆጣጠር አይቻልም” ይላል። ጽሑፉ መንግሥት በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት መቋቋምና መቆጣጠር የማይቻል አደጋ ሲገጥመው አደጋዉን ለመቋቋም እንዲረዳ የሚያውጀው “ኢ-መደበኛ” የሕግ ማስበር ሥርዓትን የሚፈቅድ ሕግ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ እንደሚባል ያስረዳል።

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ በሕገ-መንግሥት አንቀጽ 93 መሠረት የታወጀ ሲሆን፣ በዚሁ ሕግ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ከሚታወጅባቸው ምክንያቶች መካከል የውጭ ወረራ ሲያጋጥም፣ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ መከሰት እና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ሁኔታውን ማስተካከል የማይቻል ከሆነ፣ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም፣ የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸካይ ጊዜ ዐዋጅን ሊያውጅ እንደሚችል በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 93(1)(ሀ) ተደንግጎ ይገኛል።

በኢትዮጵያ የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ቁጥር 5/2014 ማወጅ ያስፈለገበት መሠረታዊ ምክንያት የአገርን ሕልውና፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጠላቶች ለመጠበቅ መሆኑ ተጠቅሷል።

በኢትዮጵያም የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሲኖር በተወካዮች ምክር ቤት የሚጸድቅ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ማወጅ እንደሚችል በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 93 (1) (ሀ) እና በተከታዮቹ ሥር ተደንግጓል። ዓለም አቀፉ የተባበሩት መንግሥታት የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን ሥምምነት በአንቀጽ 4 መሠረት አገራት ሕልውናቸወን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲያጋጥማቸው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ሊያውጁ እንደሚችሉ ይደነግጋል።

የአስቸካይ ጊዜ ዐዋጅ ምክንያታዊ የሆኑ ችግርች እና በመደበኛ የሕግ አስተዳደር መቀጠል በማይቻልበት ሁኔታ የሚታወጅ ነው የሚሉት የሕግ ባለሙያው ጥጋቡ፣ ዋና ዓላማውም የተፈጠረውን ችግር ወደ መደበኛ ሁኔታ መመለስ እና የተፈጠረውን ችግር አባባሽ የሆኑ ችግሮችን መከላከል መሆኑን ይገልጻሉ።

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ጥቅም እና ጉዳት
አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ በመደበኛ የሕግ አሠራር የማይታለፉ ጊዜያትን ለማለፍ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ኹሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችም እንዳሉት ይገለጻል። የሕግ ባለሙያው ጥጋቡ እንደሚሉት በኢትዮጵያ አሁን የታወጀው አስቸኳይ ገዜ ዐዋጅ ኢትዮጵያ ከገጠማት ችግር አንጻር የአገር ሕልውና ለመታደግ እና የሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚኖረው ሚና ጉልህ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሌላኛው አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ወታደራዊ ባለሙያ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ታመነ አባተ እንደሚሉት፣ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ኢትዮጵያ አሁን ከገባችበት ጦርነት ለመውጣት ለምታደርገው ጥረት ጉልህ ሚና እንዳለው ይጠቅሳሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር ሕዝቡ በአግባቡ እንዲገነዘበው እና በጦርነት ጊዜ በየቦታው የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመከላከል እንደሚረዳ በመግለጽ ነው።

አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ጊዜያዊ ችግሮችን ለመሻገር ሚና ቢኖረውም፣ የጎንዮሽ ጉዳቶች እንዳሉት የሕግ ባለሙያው ይገልጻሉ። የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መሠረታዊ ክፍተት በሰብዓዊ መብቶች ላይ ገደብ መጣሉ መሆኑን ባለሙያው ይገልጻሉ። የሕግ ባለሙያው አክለውም፣ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ጊዜያዊ ችግሮችን ለማለፍ ካለው ጠቀሜታ አንጻር የሚታወጅ እንጂ አስቸኳይ ጊዜ በራሱ ጥሩ ነገር አለመሆኑን ጠቁመዋል።

ዐዋጁ በሚታወጅበት ወቅት አብዛኛዎቹ ሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንደሚገደቡ ባለሙያው ይገልጻሉ። ከሚገደቡት መብቶች ውስጥ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመሰብሰብና የመደራጀት፣ በነፃነት የመንቀሳቀስ፣ ንብረት ማፍራትና ማስተዳደር፣ ተቃውሞ ማሰማትና ሠላማዊ ሰልፍ ማድረግ ገደብ የሚጣልባቸው መብቶች ናቸው።

በኢትዮጵያ አስቸኳይ ጊዜ በሚታወጅበት ጊዜ የማይሻሩ ሕጎች በጣት የሚቆጠሩ መሆናቸውን ባለሙያው ይናገራሉ። አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ የማይሽራቸው ሕጎች የኢትዮጵያ መንግሥት ሥያሜ፣ ኢሰብዓዊ አያያዝ፣ የእኩልነት መብት እና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት መሆናቸውን ባለሙያው ይገልጻሉ።

በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ከማይሻሩ መብቶቸ እና ሕጎች በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 1 ድንጋጌ ዋናው ዓላማ “የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ” የሚለው የኢትዮጵያ መንግሥት ሥያሜ የማይቀየርና የማይጣስ መሆኑን፣ አንቀፅ 18 ሥር የተደነገጉ የሰብዓዊ መብቶች፣ ከእነዚህም መካከል “ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርዱ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት” በአስቸኳይ ገዜ አዋጅ አይሻሩም።

በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ (25) ድንጋጌ መሠረት፣ ስለ እኩልነት መብት ከተዘረዘሩት መካከል “ኹሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው፤ በመካከላቸውም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል። በዚህ ረገድ በዘር፣ በብሔር፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖች፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ኹሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መበት አላቸው” ተብሎ ተደንግጓል።

ሌላኛው በአስቸኳይ ገዚ ዐዋጅ የማይሻረው ሕግ አንቀፅ 39 (1) ላይ የተቀመጠው ሲሆን፣ “የማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እሰከመገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው” የሚለው ይህ ድንጋጌ በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ የማይሻር መሆኑን የሕግ ባለሙያው ጠቁመዋል። በመሆኑም፣ በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ወቅትም ቢሆን የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እሰከመገንጠል ያለው መብቱ ጥያቄ የሚስተናገድ መሆኑን ዋስትና የሚሰጥ ድንጋጌ ነው። በዚሁ አንቀጽ (2) ድንጋጌም የማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ በቋንቋው የመናገር፣ የመፃፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግ እና ባህሉን የመግለፅ የማዳበርና የማስፋፋት፣ እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መበት ያለው መሆኑ ገደብ በማይደረግባቸው መብቶች ውስጥ የሚካት ነው። ይህ መብት በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ሰበብ የማይታገድ መሆኑን ሕገ መንግሥታዊው ድንጋጌው ግልፅ ያደርጋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014 ለማስፈፀም ሥልጣን የተሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መምሪያ ዕዝ በሚያወጣቸው መመሪያዎችም፣ በሚወስናቸው ውሳኔዎች እና በሚወስዳቸው ዕርምጃዎች በሙሉ፣ ከላይ በተጠቀሱት መብቶች ላይ ገደብ መጣል እንደማይችል የፍትሕ ሚኒስቴር ጽሑፍ ያስረዳል።

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ አፈጻጸም
አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ቁጥር 5/2014 ተግባራዊ መሆኑን ተከትሎ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱ ተገልጿል። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ሥራውን በይፋ መጀመሩን መግለጹ የሚታወስ ነው።

ዐዋጁ ጦርነቱን ሊያባብሱ የሚችሉ ችግሮችን እንደቀለበሰ እየተገለጸ ነው። በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ መሠረት በተለያዩ ከተሞች በሚደረጉ ፍተሻዎች፣ በተለይም በአዲስ አበባ፣ በርካታ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች መያዛቸው ሊፈጸሙ የሚችሉ ጥቃቶችን ለማስቀረት ጉልህ ሚና እንዳለው ሻለቃ ታመነ ይገልጻሉ።

በአዲስ አበባ በ15 ቀናት ውስጥ ብቻ 219 ሽጉጥ፣ 13 ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ተቀጣጣይ ፈንጅዎች፣ 41 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፣ 15 የእጅ ቦንቦች፣ ከ10 ሺሕ 500 በላይ የተለያዩ ጥይቶች፣ 37 የጦሮ ሜዳ መነፅሮች፣ 42 የመገናኛ ሬዲዮኖች፣ ኮምፓሶችና ለጦርነት የሚያገለግሉና አካባቢን የሚያሳዩ ካርታዎች ከነተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ውለዋል ተብሏል።

በፍተሻ የሚገኙ የጦር መሣሪያዎች መበራከት ያለው የሕገ ወጥ መሣሪያ ክምችት እና ሊፈጥር የሚችለው ጉዳት ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ወታደራዊ ባለሙያው ሻለቃ ታመነ ይገልጻሉ። ወታደራዊ ባለሙያው እንደሚሉት፣ በጦርነት ወቅት ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ሥርጭት መኖሩ ሽብር ለመፍጠር እንደሚያገልግል ነው።

እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ በተለያዩ ከተሞች የሚገኘው ሕገ ወጥ መሣሪያ ከሚጠበቀው በላይ ቢመስልም ከዚህም በላይ ሊሆን የሚችል ያልተደረሰበት የሕገ ወጥ ጦር መሣሪያ ክምችት እና የሽብር ዝግጅት ሊኖር እንደሚችል ይጠቁሟሉ። በመሆኑም፣ በዚህ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ በሕገ ወጥ መንገድ በግለሰብ እጅ የገባ የጦር መሣሪያን በጥብቅ ክትትል የመፈለጉ ሥራ ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት ጦርነት ለመውጣት የምታድረገውን ጥረት እንደሚደግፍ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል፣ አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን ምክንያት በማድረግ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳሉ እየተገለጸ ነው። ከእነዚህም መካከል በሕገ መንግሥቱ የተደገጉና በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ወቅት የማይሻሩ ስብዓዊ መብቶች ጥሰት አልፎ አልፎ እንደሚፈጸሙ እየተገለጸ ነው።

በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ አፈጻጸም ላይ ክፍተቶች እንደሚታዪ የሚገልጹት የሕግ ባለሙያው ጥጋቡ፣ በተለይ “አይንህ ቀለም አላማረኝም” ብሎ ማሰር እና ማንነትን መሠረት ያደረገ የሚመስል በሥም ብቻ የሚፈጸሙ እስሮች እንዳሉ እየተሰማ ነው ብለዋል። በመሆኑም አፈጻጸሙ ላይ ያሉ ከፍተቶችን በትኩረት ገምግሞ ችግሩ ከተገኘ ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ዐዋጁን መሠረት በማድረግ በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ሰዎች አያያዝ፣ “ማንነትን መሠረት ባደረገ መልኩ በሚመስል መከናወኑ አሳስቦኛል” ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ) መገለጹ የሚታወስ ነው።

ይህ እስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መንገዶችን ሙሉ በሙሉ መዝጋት መቻሉ እና የተወሰኑ ዜጎች እንደየአሰፈላጊነቱ በተወሰነ የማቆያ ቦታ ተገድበው እንዲቆዩ የማድረግ መብት የተሰጠው መሆኑ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ዐዋጆች የተለየ ያደርገዋል ይላሉ የሕግ ባለሙያው። በዚህም በተወሰነ የመቆያ ቦታ ዜጎችን የማየቱ ጉዳይ በዝርዝር የተቀመጠ ነገር ባለመኖሩ ዜጎችን ለእንግልት ሊዳርግ ስለሚችል የጊዜ ገደብ ሊኖር ይገባል ብለዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ዕዝ፣ የዐዋጁን አፈጻጸም መርምሮ ባወጣው መግለጫ በዚህ አጋጣሚ ለመጠቀም የሚፈልጉ ጥቂት የጸጥታ አካላት መኖራቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል። በእነዚህ አካላት ላይ በጠራ መረጃ ላይ በመመሥረት የማያዳግም ዕርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ መሰጠቱ ተመላክቷል።

በጦርነቱ ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን በጊዜያዊነት ተጠልለው በሚገኙባቸው አካባቢዎች የመንቀሳቀስ መብት የሚገድቡ ሁኔታዎችም እየተፈጠሩ ነው። አዲስ ማለዳ ባለፈው ሳምንት ዕትሟ ከጦርነት ሸሽተው ባህር ዳር የሚገኙ ተፈናቃዮች የባህር ዳር ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ ከሌላችሁ በከተማዋ መንቀሳቀስ አትችሉም መባላቸውን ተከትሎ ወደ መጡበት አካባቢ መመለሳቸውን መዘገቧ የሚታወስ ነው።

በተመሳሳይ ባለፈው ኅዳር 15/2014 በደብረ ብርሃን ከተማ፣ የከተማዋ የነዋሪነት መታወቂያ የሌለው ሰው፣ ተፈናቃዮችን ጨምሮ፣ መንቀሳቀስ አይችልም ተብሏል። እነዚህ የእንቅስቃሴ ገደቦች ከሥጋት የመነጩ ቢሆንም መሠረታዊ የሆነውን የመንቀሳቀስ መብት የሚነፍጉ ናቸው።

የሕግ ባለሙያው እንደሚሉት፣ በእንደነዚህ ዓይነት ውሳኔዎች በተፈጥሮው ተንቀሳቃሽ የሆነውን የሰው ልጅ አትንቀሳቀስ ማለት ቀላል ገደብ አለመሆኑን ያወሳሉ። የእንቅስቃሴ ገደብ ከመጣል ይልቅ አጠራጣሪ ነገሮችን በትኩረት መከታተል እና ጊዜያዊ መታወቂያ በመስጠት ተፈናቃዮች እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ እንደሚገባ የሕግ ባለሙያው ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 160 ሕዳር 18 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here