የጥቅምት ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ34.2 ከመቶ ከፍ ብሏል። የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ40.7 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በተያዘው ወር በእህሎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ በመጠኑ የተረጋጋ ሲሆን ሩዝ፣ ጤፍና ስንዴ አነስተኛ የዋጋ ቅናሽ አሳይተዋል። ይሁን እንጂ የበቆሎ ዋጋ ግን በመጠኑ ጨምሯል።
ሥጋ፣ ወተት፣ አይብና ዕንቁላል፣ ቅመማ ቅመም (በዋናነት ጨውና በርበሬ) መጠነኛ ቅናሽ አሳይተዋል። ከውጭ የሚገባው የምግብ ዘይት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር ዋጋው የጨመረ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ የሚዘጋጀው ዘይትና ቅቤ ዋጋ ትንሽ ቀንሷል፤ የቡና ዋጋ ደግሞ ጭማሪ አሳይቷል።
በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት የጥቅምት ወር 2014 ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ25.2 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። ከምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋና ምክንያቶች ውስጥ በተለይም በአልኮልና ትምባሆ፣ ልብስና ጫማ፣ አነቃቂዎች (ጫት)፣ የቤት እንክብካቤና ኢነርጅ (ማገዶና ከሰል)፣ የቤት መሥሪያ ዕቃዎች (የቤት ኪራይ፣ ሲሚንቶ፣ የቤት ክዳን ቆርቆሮ)፣ የቤት ዕቃዎችና የቤት ማሰጌጫዎች፣ ሕክምና እና ጌጣጌጥ (ወርቅ) ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ነው። በክልል ደረጃ ሲታይ በጥቅምት ወር በአዲሰ አበባ ከተማ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ከሌሎች ክልሎች ጋር ሲነጻጸር የዋጋ መረጋጋት ሁኔታ ታይቷል።
በአጠቃላይ፣ በመስከረም ወር 34.8 በመቶ የደረሰው የዋጋ ግሽበት በጥቅምት 2014 ዓመታዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ወደ 34.2 በመቶ ዝቅ ብሏል።
የጥቅምት 2014 ወርሃዊ የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው መስከረም 2014 ጋር ሲነጻጸር በ1.3 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፣ በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ የዋጋ ግሽበት የተረጋጋ ሲሆን፣ የረዥም ጊዜ ወቅታዊ የዋጋ ግሽበት አዝማሚያ እንደሚያሳየው ከመኸር ወቅት የግብርና ምርት ጋር በተያያዘ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት የምግብ ዋጋ ይቀንሳል ተብሎ ይገመታል። መረጃው ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የተገኘ ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 160 ሕዳር 18 2014


