“ሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ” በዕቅዱ መሠረት ሥራውን ለመጀመር ቅድመ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተሰማ

0
1125

መንግሥት የቴሌኮም ኢንዱስትሪውን ለግል ኢንቨስትመንት ክፍት ካደረገ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በውድድር አሸናፊ ሆኖ ወደ አገር ውስጥ በመግባት ሥራ ለመጀመር ዝግጅት በማድረግ ላይ የሚገኘው “ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ” ቅድመ ዝግጅቶቹን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተገለጸ።
ፈቃድ ሰጪውና ተቆጣጣሪው ተቋም የኢትዮጵያ ኮሚዩኒኬሽን ባለሥልጣን፣ ከኩባንያው ጋር ባካሄደው ውይይት በቅርቡ የኩባንያው ሠራተኞች ከአገር እንደወጡ ተደርጎ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ስለተሰጠው መረጃ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ ማብራሪያ መጠየቃቸው ተሰምቷል።
የኩባንያው ሥራ አስፈጻሚዎችም ለተፈጠረው ሁኔታ ይቅርታ ጠይቀው፣ ኩባንያው ላለፉት 5 ወራት አስፈላጊ በሆኑ የኔትዎርክ ዲዛይን፣ ቦታ የመምረጥ እንዲሁም ከውጪ የሚገቡ መሣሪያዎችን የማስገባትና የሰው ኃይል የማሟላት ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል።
የቅድመ ዝግጅት ሥራዎቹ እንደተጠናቀቁም ኩባንያው ወደ ሥራ እንደሚገባና በፈቃድ ስምምነቱ መሠረት በወቅቱ አገልግሎት መስጠት ለመጀመር እንደሚንቀሳቀስ ተጠቁሟል።
በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች አብዛኞቹ ሥራዎች በታቀደላቸው ጊዜ እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግሯል መባሉን ከባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነትና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኩባንያው ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጋር ተቀራርቦ እንደሚሠራና ዝግጅቱን አጠናቆም በሚያዝያ 2022 አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 160 ሕዳር 18 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here