በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን መካነ-ሠላም ከተማ የሚገኙ ከሰሜን ወሎ አካባቢ የተፈናቀሉ 2 ሺሕ 339 ተፈናቃዮች ችግር ላይ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ አሳወቁ።
ከሰሜን ወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ወደ መካነ-ሠላም ከተማ ካቀናን ከአንድ ወር በላይ አስቆጥረናል የሚሉት ተፈናቃዮቹ፣ መሠረታዊ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ችግር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ተፈናቃዮቹ ከአላማጣ፣ ቆቦ፣ ወልድያ፣ መርሳ እና ሌሎች የሰሜን ወሎ አካባቢዎች የመጡ ሲሆን፣ አሁን ላይ በመካነ-ሠላም ትምህርት ቤት እንደሚገኙ የተፈናቃይ ኮሚቴ አባል የሆኑት አብዱ እንድሪስ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
አብዱ እንድሪስ በጦርነቱ ምክንያት ከአካባቢያቸው ተሰደው ላለፉት ሦስት ወራት በደሴ ከተማ የቆዩ ቢሆንም፣ ከጥቅምት 20/2014 ወዲህ ግን ወደ መካነ-ሠላም ከተማ እንዳቀኑ ነው የገለጹት።
ወደ መካነ-ሠላም ከተማ ካቀናን ከአንድ ወር በላይ አስቆጥረናል የሚሉት አብዱ፣ እስከ አሁን አንድ ጊዜ ብቻ 12.5 ኪሎ ዱቄት እንደተረዱና ከዚያ ወዲህ ግን ድጋፍ ባለማግኘታቸው የምግብ፣ የመኝታ፣ የአልባሳት፣ የውኃና የመብራት ችግር እንዳጋጠማቸው ነው ያመላከቱት።
ከኹሉም በላይ የውኃ ዕጥረት በመኖሩ በተለይም ሴቶችና ሕፃናት ችግር ላይ ናቸው የሚሉት አብዱ እንድሪስ፣ እስካሁን ኹለት ቦቲ መኪና ውኃ ብቻ እንዳገኙና የመጠጥ ውኃ ችግር ቢኖርባቸውም በድጋሚ ማግኘት አለመቻላቸውን ገልጸዋል።
ሰሞኑን ለዕርዳታ ተብሎ አራት መኪና ፍራሽ መጥቷል የሚሉት አብዱ፣ ለተፈናቃዮች እንዳልተሰጠ ነው የተናገሩት። ከተፈናቃዮች መካከል አበበ ሀብታሙ የተባሉ ግለሰብ፣ በርካታ ሰዎች በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ተጠልለው ቢገኙም ውኃና መብራት እንደሌላቸው አመላክተው፣ “መንግሥትም እስካሁን ብቅ ብሎ አላየንም፤ ያለንበት ኹኔታ በጣም ከባድ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የደቡብ ወሎ አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትና ኃላፊ መሳይ ማሩ፣ ተፈናቃዮቹ ያቀረቡት ቅሬታ እውነት መሆኑን አረጋግጠው፣ ችግሩን ለመቅረፍ ምን እየሠሩ እንደሆነ እንደሚከተለው አብራርተዋል።
በተቻለን መጠን ከአማራ ክልል አደጋና ሥጋት መከላከል ያገኘነውን 400 ኩንታል ዱቄት በቦረና ትምህርት ቤት ተጠልለው ለሚገኙ ኹለት ሺሕ 339 ተፈናቃዮች፣ 12.5 ኪሎ ግራም ዱቄት ለመስጠት ሞክረናል ያሉት መሳይ፣ ይህ በቂ ስላልሆ መንግሥት ዕርዳታ እንዲያደርግላቸው ባደረጉት ጥሪ መሠረት፣ ለእያንዳንዱ ሰው 15 ኪ.ግ. ዱቄት በየወሩ ለመስጠት እንደታቀደና ዕርዳታው በቅርቡ እንደሚሰጥ አመላክተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የምግብ ማብሰያ፣ የሳሙና፣ የቤት ዕቃ ዕጥረት እንዳለባቸው ለክልሉ አሳውቀው ድጋፉ በጉዞ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ወረዳ የውኃ ዕጥረት አለ የሚሉት መሳይ፣ ችግሩን ለመቅረፍ ከወረዳው ጋር እንደተወያዩና የውኃ ማጠራቀሚያ ‹ሮቶዎችን› በማመቻቸት ላይ እንደሆኑ አመላክተዋል።
ተፈናቃዮች ያቀረቡት የመብራት ችግር መኖሩን አምነው፣ ይህም የሆነው በጦርነቱ የተነሳ የመብራት አገልግሎት በመቋረጡ ነው ብለዋል።
መሳይ አክለውም፣ የፍራሹን ችግር ለመቅረፍ ባደረጉት ጥረት ሰሞኑን አንድ ሺሕ 500 ፍራሽ፣ ኹለት ሺሕ 500 ብርድ ልብስ እንዳዘጋጁና በለገመራ ትምህርት ቤት ውስጥ ላሉ ተፈናቃዮች መስጠት እንደጀመሩ አመላክተዋል።
ትራንስፖርት በመጓተቱ ምክንያት የሥርጭት ችግር እንደገጠማቸው ያልደበቁት መሳይ፣ “ችግር ደረሶብናል” ላሉት ተፈናቃዮች ሰሞኑን ያላቸውን ቁሳቁስ የማዳረስ ተግባራ እንደጀመሩ ጠቁመዋል።
በመካነ-ሠላም ከተማ በጠቅላላው 10 ሺሕ 171 ተፈናቃዮች እንዳሉና፣ ኹለት ሺ 339 ሰዎች፣ በቦረና በሚገኙ ኹለት ትምህርት ቤቶች፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በዘመድ ቤትና በኪራይ ቤት ይኖራሉ የሚሉት መሳይ፣ ድጋፍ ለማዳረስ ስለተቸገሩ ኹሉም ኢትዮጵያዊ ትብብር እንዲያደርግላቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 161 ሕዳር 25 2014



